ክብረ በዓላት እና ቱሪዝሙ

0
140

ቪዚት ኢትዮጵያ (Visit Ethiopia) ከተሰኘ ድረ ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ የጉብኚት መዳረሻዎች ቀዳሚውን ሥፍራ ይዛለች። መረጃው አክሎም በዓለም ቅርስነት ባስመዘገበቻቸው ቅርሶች የአፍሪካ ሀገራትን እየመራች እንደሆነ ያነሳል። ካላት የቅርስ እና ፀጋዎች ብዛት አንጻር ግን በዩኔስኮ ያስመዘገበችው ጥቂቶቹን እንደሆነ ይነገራል። የሀገሪቱ የዘርፉ ተጠቃሚነትም ዝቅተኛ ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ፀጋዎቿ በዓለም የቅርሶች መዝገብ (ዩኔስኮ) በማስመዝገብ የጎብኚዎችን ቀልብ ስባለች። የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን የመሳብ ውብ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድራዊ ገፅታዎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ ትልልቅ ሐይቆች እና ወንዞች፣ የላልይበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ የታሪክ አምባ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናት እና ዋሻዎች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ ክብረ በዓላት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ጸጋዎች ያላት ሀገር ናት።

የበርካታ ፀጋዎች ባለቤቷ ኢትዮጵያ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የፋሲል አብያተ መንግሥታት ህንፃዎች፣ የጣና ሐይቅ ደሴቶች እና ገዳማት፣ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የአክሱም ሐውልት፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ሌሎች የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች መገኛ ናት። እነዚህን ጸጋዎች ለአብነት ያነሳው ቪዚት ኢትዮጵያ “በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ባለ ጸጋ ነገር ግን በጸጋዋ ልክ ተጠቃሚ ያልሆነች” ሲል ነው የገለጻት።

ከዓለም የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) የቱሪስት ማዕከላት መካከል ስሟ ተደጋግሞ የሰፈረው ኢትዮጵያ ስሟ ደጋግሞ እንዲሰፍር ያደረጓት ዋና ዋናዎቹ መዳረሻዎች መካከል በርካቶቹ በአማራ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ልዩ ተፈጥሮ፣ ሰፊ ባሕል እና የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው  የአማራ ክልል በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ፀጋዎቹ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ነው። ክልሉ ከታኅሳስ እስከ የካቲት ባሉት ወራት ደግሞ ጎብኚዎችን የመሳብ አቅሙ ከፍ ያለ ነዉ።

ክልሉ ከላልይበላ እስከ ስሜን ሰንሰለታማ ተራሮች፣ ከግሸን ደብረ ከርቤ እስከ ጎንደር አብያተ መንግሥታት ሕንጻዎች፣ ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ እስከ ጣና ሐይቅ ገዳማት፣ ከጭስ ዓባይ ፏፏቴ እስከ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከጎርጎራ እስከ ጉና፣ ከዓባይ ሰከላ እስከ ሰቆጣ ሰሃላ በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ መዳረሻዎች አሉት።

የቱሪዝም ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የሀገርን የውጭ ምንዛሬ ችግርን በማቃለል ግንባር ቀደም የምጣኔ ሀብት ምንጭ እንደሆነም የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በ2015 ዓ.ም ለሕትመት ካበቃው ዓመታዊ መፅሔት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። መፅሔቱ እንዳስነበበው ቱሪዝም ማሕበራዊ ትሥሥርን፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን በማጎልበት  በኩል ትልቅ አበርክቶ አለው።

በክልሉ የሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች እና ከተሞች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የነዋሪዎቻቸው ህይወት የተመሠረተው ከቱሪዝም በሚገኝ ገቢ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት ተጎድቶ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ያገግማል ተብሎ ሲጠበቅ እንደገና በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ዘርፉን ከድጡ ወደ ማጡ አስገብቶት ቆይቷል። ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ  ደግሞ በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም እጦት እና በትጥቅ የታገዘ ግጭት የዘርፉን እንቅስቃሴ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶታል።

ይህም ሀገሪቱን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማትን እና ግለሰቦችን ክፉኛ ከጎዳቸው ውሎ አድሯል። በኩር ጋዜጣ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳውን ቱሪዝም እንዲነቃቃ በዘርፉ የተሰማሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እና ባለሙያዎችን አነጋግራ መፍትሄ አመላካች ዘገባዎችን በተለያዩ ጊዚያት ለንባብ አብቅታለች። ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የሚባለው ቱሪዝም በሠው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የጎብኚዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ መምጣቱንም ዘግባለች። ሆኖም የሰላም እጦቱ እልባት ባለማግኘቱ ችግሩ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ መሆኑን  ነው በዘገባዎቿ ያመላከተችው።

ችግሩም የቱሪዝም ቤተሰቦችን (አስጎብኚ ግለሰቦችን፣ ባለሆቴሎችን፣ በቅሎ አከራዮችን፣ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ፎቶ አንሺዎችን፣ አስጎብኚ ድርጅቶችን፣  ምግብ አብሳዮችን፣ ባለታክሲዎችን) ለከፍተኛ ችግር አጋልጧል። ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለው ለጥገኝነት መዳረጋቸውንም ጋዜጣዋ በተደጋጋሚ አስነብባለች። በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በገቢ አሰባሰቡ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖም ከፍተኛ ነው። ለአብነትም ከ2012 ዓ.ም በፊት 207 ሺህ  የውጭ ሀገር ጎብኚዎች የአማራ ክልልን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ጎብኚተው ነበር።  በ2016 ዓ.ም ደግሞ የጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ 20 ሺህ መድረሱን የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያሳያል። ከዘርፉ የተገኘው ገቢም መቀነሱን መረጃው አክሏል።

ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ታዲያ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል። ከታኅሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የሚከበሩትን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት መሠረት በማድረግ የተቀዛቀዘውን ዘርፍ ለማነቃቃት የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።

ለአብነትም በየዓመቱ ታኅሳስ 29 ቀን የሚከበረውን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (የገና በዓል) ላልይበላ ከተማ በድምቀት ለማክበር እና እንግዶቿን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅቷን አጠናቃለች። በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ያሉት የላሊይበላ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ ናቸው። የልደት በዓልን በድምቀት ለማክበር ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።

የሚመጡ እንግዶችን የከተማዋ ወጣቶች እግር በማጠብ ወደሚያርፉበት ቦታ ማድረስ፣ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች በቂ ዝግጅት በማድረግ እንግዶችን መቀበል እና እንግዶች ወደ ከተማዋ የሚመጡባቸው ተጨማሪ የአየር በረራ መዘጋጀቱ ከተግባራቱ መካከል መሆናቸውን ጠቁመዋል። ‘‘የሚመጡ እንግዶች የማረፊያ ችግር አይገጥማቸውም ነው’’ ያሉት ኃላፊዉ። በዓሉ በከፍተኛ ደረጃ ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

የእንግዶች የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ነዋሪው ማኅበረሰብ በተለመደ ውብ የእንግዳ አቀባበል ባሕሉ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ትክክለኛ መረጃ መስጠት እና መንከባከብ እንደሚገባው አብራርተዋል። በዓሉን በሰላም እንዲያከብሩም ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ ጥምቀትን በጎንደር ለማክበር የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የፀጥታ ማስከበርን ጨምሮ በርካታ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል። አንፃራዊ ሰላሙን በመጠቀም የከተማዋን ቱሪዝም ለማነቃቃት የቅርስ ጥገና እና የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥን የማሻሻል እንዲሁም አዳዲስ መዳረሻዎችን ማልማትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የመምሪያው ተወካይ ኃላፊ አቶ ልዕልና አበበ ለአሚኮ በስልክ ገልፀዋል። ከጥምቀት በተጨማሪ ሌሎች ሁነቶችም በሰላም እንዲከበሩ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ መምሪያው ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም ለበኩር ጋዜጣ እንዳስታወቁት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች ቱሪዝሙን ክፉኛ ጎድተውታል። የቱሪዝም እንቅስቃሴው መቀዛቀዝ በተለይም ህልውናቸው ሙሉ በሙሉ በቱሪዝም ገቢ ላይ ለተመሠረተ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ አደጋ ሆኖ ቆይቷል ያሉት አቶ መልካሙ ቱሪዝሙን ለማነቃቃት የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

ቱሪዝም የሥራ እድል በመፍጠር፣ ምጣኔ ሀብትን በማሳደግ እና የአካባቢን ባሕል እና ወግ በማስተዋወቅ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ አማራ ክልል በርካታ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ክብረ በዓላትን ያስተናግዳል። እነዚህ ክዋኔዎች ታዲያ የተዳከመውን የክልሉ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ያላቸው አበርክቶ ጉልህ ነው።

በክልሉ እስካሁን በጥናት የተለዩ 300 የሚሆኑ ዓመታዊ ክብረ በዓላት በድምቀት እንደሚከበሩ አቶ መልካሙ ተናግረዋል። ለአብነትም የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላልይበላ፣ የጥምቀት በዓል በጎንደር እና በምንጃር ሸንኮራ (ኢራንቡቲ)፣ ጥርን በባሕር ዳር፣ የቃና ዘገሊላ፣ አስተሪዮ ማርያም በመርጦ ለማሪያም፣ በግሸን ደብረ ከርቤ እና በደረስጌ ማርያም፣ የአገው ፈረሰኞች በዓል በአዊ ብሔረሰብ፣ የግሽ ዓባይ (ሰከላ) ዓመታዊ ክብረ በዓል፣ የመርቆሪዮስ ዓመታዊ በዓል በደብረ ታቦር እና በእስቴ መካነ ኢየሱስ በድምቀት  የሚከበሩ በዓላት ሲሆኑ ለቱሪዝሙ መነቃቃት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ናቸው።

እነዚህ በዓላት ከታኅሳስ ወር ጀምሮ እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ በድምቀት የሚከበሩ እና ጎብኚዎችን የሚስቡ ታላላቅ ሁነቶች ናቸው። በዓላቱ በሚከበርባቸው አካባቢዎች በተለይም በላልይበላ እና በጎንደር የዝግጅት ሥራዎችን የሚከውን ኮሚቴ ተደራጅቶ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል። በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ታሳቢ ያደረገ በቂ የመኝታ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ዝግጁ  አድርገዋል። እንግዶቻቸውንም መቀበል ጀምረዋል።

የበዓሉን ተጓዦች ብዛት እና ፍላጎት መሠረት በማድረግም ከየብስ ትራንስፖርት በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመደበኛው በተጨማሪ በረራዎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ መልካሙ አስረድተዋል። የቱሪስት አስጎብኚ እና የሆቴል ማኅበራትም እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የቅዱስ ላልይበላ ሆቴሎች ከሰው ኃይል ጀምሮ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19)፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ሁለተኛ ዓመቱን በያዘው የአማራ ክልል ግጭት የከፋ ዳፋ ያሳደሩበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲያንሰራራ ለማድረግ በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ ነው በአፅንኦት ያሳሰቡት።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የታኅሳስ 28  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here