ያለ እግር የተወለደችው የ33 ዓመቷ አሜሪካዊት በባለ ጐማ መንሸራተቻ (skatebord) ላይ በእጆቿ በመቆም ስሟን በዓለም የድንቃ ድንቅ የክብረወሰን መዝገብ ለማስፈር መቻሏን ዴይሊ ሜይል ድረ ገጽ አስነብቧል::
በ2022 እ.አ.አ በ31 ዓመት እድሜዋ ካንያ ሴሰር “በፓራ አትሌት” በሴቶች ውድድር ሁለተኛ ደረጃን ነበር ያገኘችው:: በ2024 እ.አ.አ እግር አልባዋ እንዲሁም የእጅ ጣቶቿ በቆዳ ተጣብቀው ብትወለድም መንሸራተቻው ላይ ዐሥራ ዘጠኝ ሰኮንድ ከስልሳ አምስት ማይክሮ ሰኮንድ በእጆቿ በመቆም ክብረ ወሰን ማስመዝገብ ችላለች::
“ማንኛውም ሳር አረንጓዴ አይደለም” የሚል መልዕክት ያስተላለፈችው ካንያ የማይቻል የሚመስለውን በተግባር በማሳየት መጪውን ትውልድ ለማነሳሳት አልማ በፅናት መፈፀሟን ነው የተናገረችው::
ካንያ ሴሰር ለዚህ የላቀ ክብር እና ውጤት ለመብቃት ረዢም ወጣ ገባ የሕይወት ጐዳና ማሳለፏን ተናግራለች:: ቅንጭብ የሕይወት ታሪኳን ያሰፈረው ድረ ገጹ በታይላንድ የሦስት ወር ሕፃን ሳለች ጐዳና ላይ ተጥላ መንገደኛ ሴት እንዳገኘቻትም ነው ያስነበበው::
በጉዲፈቻ /ማደጐ/ ለአሳዳጊዎች ተሰጥታ ወደ አሜሪካ ፖርትላንድ ኦሪጐን መወሰዷን ድረ ገጹ አስነብቧል:: ካንያ በአሳዳጊዎቿ የቤተሰብ አባል ሆና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች:: ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ሳለች ነበር በባለጐማ መንሸራተቻ “skate board’’ የተለያዩ የአካል እንቅስቃሴዎችን መለማመድ የተያያዘችው::
የእጅ ጣቶቿ በቆዳ የተጣበቁ እግር አልባ ሆና ብትወለድም ባላሰለሰ ጥረቷ አና በይቻላል ፅናቷ በእጆቿ ባለጐማ መንሸራተቻ (ስኬት ቦርድ) ላይ ለ19 ሰኮንድ ከስልሳ አምስት ማይክሮ ሰኮንድ በመቆም የዓለም ክብረ ወሰንን መስበር ችላለች::
ካንያ ሴሰር “እግር አልባነት ከምንም አይገድብም” ስትል የፅናት፣ የመንፈስ ጠንካራነት መልእክቷን ማስተላለፏን ድረ ገጹ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም