ክትባት እና  ጠቀሜታዎቹ

0
5

ለመጀመሪያ ጊዜ ክትባትን ያስተዋወቁት በ10ኛው ክፍለ ዘመን ቻይናዊያን እንደሆኑ የቢቢሲ መረጃ ያመላክታል፤ በወቅቱ ጤናማ ሰዎችን በሽታ አምጪ ለሆኑ ተህዋሲያን በማጋለጥ በሽታን የመከላከል አቅማቸው እንዲዳብር ያደርጉ እንደነበርም መረጃው ያስረዳል።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ደግሞ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት መከላከል  እና ሊታከሙ በሚችሉ በሽታዎች ይሞታሉ:: ከውልደት ጀምሮ የሚሰጡ ክትባቶች ሕጻናት ጤናቸው ተጠብቆ እንዲያድጉ እና ነጋቸውን እንዲያዩ በማስቻል ረገድ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ባለፉት 50 ዓመታትም ክትባቶች 154 ሚሊዮን ሰዎችን ማዳን ችለዋል::

ክትባት  ሰውነታችን ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ከመጠቃቱ በፊት አስቀድሞ  የመከላከል አቅምን ለማሳደግ  እንደሚሰጥም መረጃው ጠቁሟል::

በመሆኑም ክትባትን በመውሰድ ራስዎን፣ ልጆችዎን እና የወደፊት ትውልድን ከተላላፊ በሽታዎች ጠብቁ ይለናል መረጃዉ። በሌላ አገላለጽም ክትባት ከወሰዱ አሁን እና ወደፊት ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ለማጥፋት ይረዳዎታል።

ክትባት በርካቶችን ከስቃይ ያዳነ፣ በየጊዜው የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን የተከላከለ እና ከሞት የታደገ የሕዝብ የጤና የማዕዘን ድንጋይ ነው።

እርስዎ እና ቤተሰብዎን ሙሉ በሙሉ በማስከተብ የራስዎን ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ተጋላጭ ሰዎችንም እየጠበቁ ነው። የተከተቡ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር  በበሽታ የመያዝ ዕድል እየቀነሰ ይሄዳል:: ይህ ሲሆን ደግሞ  በሽታው በስፋት ሊሰራጭ አይችልም።

በ1950ዎቹ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት እንደ ቴታነስ፣ በጉሮሮ ላይ የሚያጋጥም ሕመም (ዲፍቴሪያ) እና በደረቅ ሳል በሽታዎች ይሞቱ ነበር። ሆኖም በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ በተዋወቁት ዋና ዋና የክትባት መርሃ ግብሮች ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ተላላፊ በሽታዎች የሚሞት ሰው ቁጥሩ ቀንሷል።

 

ክትባቶች እንዴት ይሠራሉ?

ሁሉም ክትባቶች በተመሳሳይ መንገድ ይሠራሉ። ክትባቶች በሚሰጡበት ጊዜ የሰውነት የበሽታ መከላከያ ሥርዓቶች ፀረ እንግዳ አካላትን፣ ህዋሳትን እና ሌሎች የመከላከያ ዘዴዎችን እንዲያመነጩ ያነሳሳሉ። ይህ የመጀመሪያ ደረጃ የበሽታ መከላከያ ምላሽ አንድ ሰው ትክክለኛው በሽታ አምጪ ተህዋስ ካጋጠመው በሽታ የመከላከል ሥርዓቱ በፍጥነት እና በብቃት መቋቋም እንደሚችል ያረጋግጣል::

ከተከተቡ በኋላ ከበሽታ ማገርሸት (ኢንፌክሽን) ጋር ከተገናኙ፣ ሰውነትዎ በሽታው እንዳይከሰት ለመከላከል ይሠራል ወይም ቀላል ሕመም ብቻ ሊያጋጥምዎት ይችላል። ክትባቶች ደኅንነታቸው እና ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ሙከራ ተደርጎባቸው ነው ወደ ሥራ የሚገቡት።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ ክትባት በየዓመቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርስ ሞትን ያስቀራል።

የተለያዩ ገዳይ በሽታዎችን ለማጥፋት ወይም ለመቆጣጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ክትባት  የፈንጣጣ በሽታ በ1980 ሙሉ በሙሉ ከዓለም ላይ እንዲጠፋ አድርጓል:: እንደ የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) እና ኩፍኝ ያሉ እንዲሁም ሌሎች በርካታ በሽታዎች በአሁኑ ጊዜ ሲከሰቱ ብዙ ጉዳት ሳያስከትሉ በቁጥጥር ስር የሚውሉት በክትባት ነው።

ክትባት ሕይወትን ከማዳን በተጨማሪ የሕክምና ወጪዎችን በመከላከል ኢኮኖሚያዊ ጫናን ይቀንሳል። በአጠቃላይ ክትባት ሰዎች ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ፣ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እና ለማኅበረሰባቸው አጠቃላይ ደኅንነት አስተዋጽዖ ያደርጋል።

ያልተከተቡ ግለሰቦች ለከባድ አልፎ ተርፎም ለገዳይ በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ።  ጨቅላ ሕጻናትን እና የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ግለሰቦችን የመሳሰሉ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከበሽታ ይታደጋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በየዓመቱ በክትባት መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። እ.አ.አ በ1960ዎቹ የመጀመሪያው የኩፍኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ከመተዋወቁ በፊት ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው ምክንያት በየዓመቱ ይሞቱ ነበር። በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 2000 እና 2017 መካከል በነበሩት ዓመታት በዓለም ዙሪያ በኩፍኝ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ80 በመቶ ቀንሷል። ለዚህ ባለውለታው ደግሞ ክትባት ነው::

መከተብ  የማይችሉ ሰዎች የትኞቹ ናቸው?

አንዳንድ ሰዎች ባላቸው የጤና ሁኔታ መከተብ አይችሉም። እነሱን መጠበቅ የሚቻለው አብረዋቸው የሚኖሩ  ሰዎችን እና ማኅበረሰቡን በማስከተብ ነው።

ኅብረተሰቡ ሲከተብ የበሽታው ስርጭት ይቀንሳል ወይም ሙሉ በሙሉ ይቆማል። ምክንያቱም በሽታው ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ መሰራጨት አያስችለውም። ሰዎች መረዳት ያለባቸው  95 በመቶ የሚሆነው ክትባት የበሽታ ስርጭትን መቀነሱን ነው።

የትኞቹ በሽታዎች ክትባት አላቸው?

የዓለም ጤና ድርጅት በክትባት መከላከል የሚቻሉ 27 በሽታዎችን ዘርዝሯል። ከነዚህ መካከልም ኮሌራ፣ ኮቪድ-19፣ ዴንጊ፣ ዲፍቴሪያ፣ ሄሞፊለስ ኢንፍሉዌንዛ ዓይነት ቢ፣ ሄፓታይተስ ኤ፣ ሄፓታይተስ ቢ፣ የሳንባ ምች፣ የሳንባ ነቀርሳ (BCG)፣ የማህጸን በር ካንሠር (HPV)፣ ኢንፍሉዌንዛ (ወቅታዊ ጉንፋን)፣ ወባ (አዲስ ክትባት)፣ ቢጫ ወባ፣ ኩፍኝ፣ ታይፎይድ እና የእብድ ውሻ በሽታ(rabbis)… ይገኙበታል::

ክትባት እና የጎንዮሽ ጉዳቶች

አብዛኛዎቹ ክትባቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች ጥቃቅን እና ጊዜያዊ ናቸው። ጉዳቶቹም የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ:: መካከለኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ የተወጉበት አካባቢ መቅላት እና በራሱ የሚጠፋ እብጠት፣ ሊያስከትል ይችላል። ከባድ የሚባለው የጎንዮሽ ጉዳት ደግሞ ማንቀጥቀጥ እና ከላይ የተቀመጡት የጎንዮሽ ጉዳቶች ማስታገሻ ተውስደውባቸውም ከሁለት ቀን በላይ ሳይጠፉ ሲቆዩ ነው::  ታዲያ በዚህ ጊዜ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ ተገቢ ነው።

ጤና አዳም

*የመጀመሪያውን የፖሊዮ ክትባት በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከተቡ ሕጻናት በ45 ቀናቸው ፖሊዮ1 ን መከተብ ይችላሉ፡፡

*ጨቅላ ሕጻናት የፀረ-ሳንባ ነቀርሳ በሽታ ክትባት ከተወለዱ ጀምሮ ባሉት 14 ቀናት ቢከተቡ መልካም ነው፡፡ ሆኖም እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሳይከተቡ መቆየት ይችላሉ፡፡

*ሚዚል ወይም የፀረ-ኩፍኝ  በዘጠኝ ወራቸው ይከተባሉ፡፡ በሽታውን የመከላከል አቅማቸውን ለማጠናከር ደግሞ በድጋሚ አንድ ዓመት ከሦስት ወራቸው ላይ ይሰጣቸዋል፡፡

* የኩፍኝ ወረርሽኝን ለመከላከል ቢያንስ 95 በመቶ የማኅበረሰቡ አባላት መከተብ አለባቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ የኩፍኝ ወረርሽኞች በክትባት መጠን መቀነስ እና ባልተከተቡ ሰዎች ጉዞ ምክንያት አሁንም ሊከሰት ይችላል።

ምንጭ፡ /www.unicef.org/

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here