ኮሌራን እንዴት እንከላከል?

0
97
Vibrio cholerae, Gram-negative bacteria. 3D illustration of bacteria with flagella.

ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት በማስከትል በሰውነት ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽን አሟጦ በማስወጣት አቅምን በማዳከም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። በሽታው በአማራ ክልል በቋራ ወረዳ በበርሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ የፀበል ቦታ ከታሕሳስ 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን  በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎችና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሙያ ሲስተር ሰፊ ደርብ ለበኵር ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ በቋራ ወረዳ የተከሰተው ወረረሽኝ  ከመጋቢት 2/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን በአንዳሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ የፀበል ስፍራ፣በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በጃዊ ወረዳ በፍልዉሃ ብሔራዊ ፀበል፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን በቡሬ ከተማም ተከስቷል፡፡ በዋነኛነት በአራቱ ቦታዎች ላይ ወረርሽኙ ይከሰት እንጂ በሌሎች የክልሉ ክፍሎችም ተሰራጭቶ ይገኛል፡፡ ለአብነትም በሰሜን ወሎ ዞን በዋድላ እና በመቄት፣ በምዕራብ ጐንደር ዞን  በገንዳ ውኃ እና መተማ፣ በማዕከላዊ ጐንደር በአለፋ፣ በምሥራቅ ደምቢያ እና በጐንደር ከተማ ተከስቷል፡፡

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር  ደግሞ በዳንግላ ከተማ፣ ቻግኒ እና እንጅባራ ከተማን ጨምሮ በስምንት ወረዳዎች ተከስቷል፡፡ በደቡብ ጐንደር ዞን ደግሞ በእብናት እና በደራ ወረዳዎች፣ በምዕራብ ጐጃም በቡሬ ከተማ እና በሰከላ ዙሪያ፣ በምሥራቅ ጐጃም ዞን  በእነብሴ ሳር ምድር፣ በእናርጅ እናውጋ፣ በሞጣ ከተማ እንዲሁም በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳዳር ወረርሽኙ መከሰቱ ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ከታሕሳስ 24/2017 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 13/2017 ዓ.ም ድረስ በክልሉ ኮሌራ በ32 ወረዳዎች የተከሰተ ሲሆን 2 ሺህ 66 ሰዎችም በወረርሽኙ ተይዘዋል፡፡ ከተያዙት መካከልም 15 ሰዎች ሕይዎታቸው አልፏል፡፡ በእነዚህ  ቦታዎች ላይ በዋነኝነት ወረርሽኙ ሊከሰት እና ሊስፋፋ የቻለው በርካታ ሕዝብ ሊያስተናግድ የሚችል በቂ የመፀዳጃ ቦታ አለመኖር፣   የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት እጥረት እና የተመቸ ሁሉንም በአግባቡ የሚይዝ ማረፊያ  ቦታ ባለመኖሩ  እንደሆነ ሲስተር ሰፊ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተከሰተውን ኮሌራ ለመቆጣጠር በዋነኝነት ወረርሽኙ በተከሰተባቸው በቋራ ወረዳ በበርሚል ቅዱስ ጊዮርጊስ የፀበል ቦታ እና በአንዳሳ ቅዱስ ጊዮርጊስ የፀበል ስፍራ ጊዜያዊ መታከሚያ ቦታ በማዘጋጀት የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ህክምናውን ከመስጠት  ጐን ለጐንም ህሙማንን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ እንዲሁም ስለወረርሽኙ መንስኤ፣ ምልክቶች እና መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ሲሰተር ሰፊ የተናገሩት፡፡

በተጨማሪም በወረዳ፣ በዞን እና በክልል እንዲሁም በጤና ተቋማት በየጊዜው ወረርሽኙን ከመቆጣጠር አንፃር ሥራዎች የደረሱበትን ሁኔታ በመነጋገር ጠንካራ እና ደካማ ጐኖች ተለይተው ክፍተቶች እየተሞሉ ያለበት  ሁኔታ እንዳለም ገልጸዋል፡፡

ወረርሽኙ በዋናነት በተከሰተባቸው   የፀበል ቦታዎች ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመነጋገር ለጊዜው አገልግሎት እንዲያቋርጡ መደረጉንም ሲስተር ሰፊ ጠቁመዋል፡፡ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቀርቦትን ለማሳፋፋት በተሠራው ሥራም አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር በአንዳሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጸበል ቦታ የውኃ ማጠራቀሚያ (ታንከር) እየተሠራ ነው፡፡ በቋራ  በርሚል የቅዱስ ጊዮርጊስ የጸበል ቦታ ደግሞ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ጥገና እየተደረገላቸው ነው፡፡

ሲስተር ሰፊ ደርብ እንደሚሉት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ላይም የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱ የመከላከል ሥራውን ከባድ አድርጎታል፡፡ በእነዚህ የእርሻ ቦታዎች በርካታ ሰው ሊያስተናግድ የሚችል የንፁህ መጠጥ ውኃ አቀርቦት እና የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት ስለሌለ በተደጋጋሚ ወረርሽኝ እየተከሰተ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል እና ሴክተር መስሪያ ቤት በጋራ ካልሠራ ለጤና ቢሮ ወይም ለውኃ ሀብት ቢሮ ብቻ በመተው ከችግሩ መውጣት አይቻልም፡፡

የኮሌራ ዋነኛ መንስኤ “ቫይብሪዮ” ኮሌራ” የተባለው ባክቴሪያ እንደሆነ ባለሙያዋ ጠቁመዋል፡፡ የኮሌራ በሽታ መተላለፊያ መንገዶችን እና መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ባለሙያዋ ሲያብራሩ  በአብዛኛው በተበከለ ምግብ እና ውኃ ይተላለፋል:: ይህ ባክቴሪያ በሰው አካል ውስጥ ከገባ በኋላ በትንሹ አንጀት ውስጥ ገዳይ መርዝ ያመነጫል። ከዚያ በኋላ መርዙ ብዙ የሰውነት ፈሳሽ እንዲወጣ በማድረግ የሰውነት ድርቀት ያስከትላል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በአካባቢ የሚገኝ ውኃን ለመጠቀም ሲያስብ በመጀመሪያ ደኅንነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ንጽህናው የተጓደለ  ውኃን ለመጠጥ፣ ጥርስን ለማጽዳት( ለመቦረሽ)፣ በረዶ ለመሥራት፣ ፊትን ፣ እጅን እና ገላን ለመታጠብ፣ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ለማጠብ፣ ለምግብ መሥሪያ እና እቃ ለማጠብ መጠቀም እንዲሁም ያልተፈላ ወተት፣ ጥሬ ስጋ፣ አሳ ወይም በደንብ ያልበሰለ ስጋ መመገብ ለኮሌራ በሽታ እንደሚያጋልጥ ሲስተር ሰፊ አስጠንቅቀዋል፡፡

ኮሌራ ተላላፊ ነው፤ ነገር ግን በማስነጠስም ሆነ በማሳል አይተላለፍም። ይሁንና ከኮሌራ በሽተኞች ጋር የቅርብ ግንኙነት መኖር ለበሽታው የመጋለጥ አጋጣሚን ይጨምራል፡፡ ተጠቂው እጁን በሳሙና እና በንጹህ ውኃ ሳይታጠብ ምግብ ካበሰለ፣ ሕጻናትን ከመገበ፣ መጸዳጃ ቤትን በአግባቡ ካልተጠቀመ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፉ ሁኔታው ከፍተኛ ነው፡፡

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ በየመንገዱ የሚሸጡ ምግቦች እና መጠጦች ለኮሌራ በሽታ የተጋለጡ ናቸው። በተለይም እንደ እኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ አብዛኛውን ጊዜ ያልበሰለ ወይም ጥሩ የምግብ ዝግጅት እና የንፅህና አጠባበቅ ሂደቶችን በየመንገዱ የሚሸጡ ምግቦች  አቅራቢዎች(ሰሪዎች) አይከተሉም። በመሆኑም በየመንገዱ የሚሸጡ ምግቦችን ሲመገቡ ኮሌራን ታሳቢ ማድረግ ይገባል፡፡

ኮሌራ በጣም ከባድ የሆኑ ምልክቶቹ  የታዩባቸው ሰዎች   በሰዓታት ውስጥ ሊሞቱ ይችላሉ። ያልበሰለ ማንኛውንም  ሥጋ  ከበሉ በኋላ ወይም ኮሌራ ወደተከሰተበት አካባቢ የሄደ ሰው  ከቆይታ በኋላ ከባድ፣ እንደ ውኃ የቀጠነ ተቅማጥ እና ትውከት  ካጋጠመው  ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት እንደሚገባው ባለሙያዋ አስገንዝበዋል።

ኮሌራ በቀላሉ ሊታከምና ሊድን የሚችል በሽታ ቢሆንም በሰውነት የሚገኝ ፈሳሽን በፍጥነት በተቅማጥ እና በትውከት አስወግዶ ለድርቀት በመዳረግ ሞት ያስከትላል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው በዓለም ላይ በየዓመቱ ከአንድ ነጠብ ሦስት ሚሊዮን እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርሱ የኮሌራ ተጠቂዎች አሉ። በየዓመቱም ከ21ሺህ እስከ 143ሺህ ሰዎች በኮሌራ ይሞታሉ።

ጤና ነክ ጉዳዮችን የሚያቀርበው ዊቢኤም ዲ ድረገጽ /webmd.com/ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ በኮሌራ የተያዘ ሰው በመጀመሪያ ደረጃ  ከሦስት እስከ 12 ሰዓታት የሚቆይ  የሆድ ቁርጠት፣ ትውከት፣ ውኃ መሰል ተቅማጥ እና የውኃ ጥማት  ምልክቶች ሊታዩበት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋም ካልሄደ  ዝቅተኛ የሰውነት ሙቀት እና የደም ግፊት፣በጣም ዝቅተኛና ደካማ የልብ ምት፣ ዐይን ወደ ውስጥ የመግባት፣ ከላይ ከላይ መተንፈስ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ውኃ መጠማትን በማስከተል ለሞት ሊዳረግ ይችላል፡፡  የኮሌራ በሽታ የሚታወቀው በዐይነ ምድር ላይ ናሙና በመውሰድ ነው፡፡ ሲስተር ሰፊ ደርብ እንዳሉት ወረርሽኙ በቀላሉ ሊዛመት እና ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሕዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል።

በመሆኑም የመጸደጃ ቤትን በአግባቡ መጠቀም፣ ሜዳ ላይ አለመጸዳዳት የመመገቢያ፣ የመጠጫ እና የውኃ ማስቀመጫ እቃዎችን በንጹህ ውኃ በማጠብ እና ከድኖ በማስቀመጥ ከዝንቦች እና ከበካይ ነገሮች መጠበቅ፣ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ከቧንቧ፣ ከጉድጓድ፣ ከምንጭ፣ ከወንዝ እና ከመሳሰሉት የተቀዳ ውኃን በውኃ ማከሚያ መድኃኒቶች በማከም ወይም በማፍላት መጠቀም ፤ ምግብን ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ እና ከመመገብ በፊት ከመጸዳጃ ቤት መልስ እና ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሲስተር ሰፊ እንዳሉት ከምልክቶቹ አንዱ በታዬ ጊዜ ወደ ህክምና ተቋም እስክንደረስ ድረስ ቤት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውንም ንጽህናው የተጠበቀ ፈሳሽ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ሕይዎት አድን ንጥረ ነገር (ኦ.አር.ኤስ) በቤት ውስጥ ከሌለ ስድስት የሻይ ማንኪያ ስኳር እና ግማሽ የሻይ ማንኪያ ጨው በአንድ ሊትር ንጹህ ውኃ በመበጥበጥ ባስቀመጠዎትና ባስታወከዎት ቁጥር መጠጣት እንደሚገባ መክረዋል።

ሕይወት አድን ንጥረ ነገር ወይም ኦ.አር.ኤስ በቤት ውስጥ ካለ አንድ ፓኬት ተፈልቶ በቀዘቀዘ አንድ ሊትር ውኃ በመበጥበጥ ይጠጡ፤ ኦ.አር.ኤስን መጠቀም የሚቻለው በተበጠበጠ በ24 ሰዓት ውስጥ ብቻ ነው።

ጡት የሚጠቡ ህፃናት በበሽታው ከተያዙ ጡት ማጥባትን ከወትሮው የበለጠ ጨምሮ ማጥባት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here