የስያሜ መነሻው በዙሪያው በብዛት የሚገኝ ዛፍ ነው፣ የኮሶ ዛፍ ሲሆን ይህም ኮሶዬ የሚል ስያሜን እንዲሰጠው አድርጓል። ከስያሜው ባለፈ ግን ዙሪያ ገባው ዕይታን በማያስለቅቁ ማራኪ የተፈጥሮ ስጦታዎች የታደለ መሆኑ ለጉብኝት ቀልብን ይገዛል። በዛሬው ጽሑፋችን ስለዚህ ድንቅ የተፈጥሮ ውብ ስፍራ በሐሳብ አስጉዘን እናስነብባችኋለን።
ኮሶዬ ከጎንደር ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ፣ 3ዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የሚገኝ ቀበሌ ነው። ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የጉብኝት መዳረሻ ስናደርግ በቅድሚያ ለዕይታችን የሚበረከት ቦታ ነው። ቦታው ከባሕር ወለል በላይ ሦስት ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል።
የአካባቢው ዙሪያ ገባ ለአንዳች ምክክር በሥርዓት የተቀመጡ በሚመስሉ ተራሮች የተከበበ ነው። ይህም የጉብኝት ማዕከል እንዲሆን ካስቻሉት ማራኪ ገጽታዎቹ መካከል አንደኛው ነው።
የኮሶ ዛፍ በብዛት ከመገኘቱ ባሻገር በተራሮች መከበቡ ተጨማሪ መጠሪያን አስገኝቶለታል። ይህም “ኮሶዬ አምባራስ” የሚል መጠሪያ ስለመሆኑ ነው ከወገራ ወረዳ ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ የሚያመላክተው።
ቦታው በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጋር የተያያዘ ሰንሰለታማ ውብ፣ ለዓይን የሚማርኩ የመሬት ገጽታዎች፣ ዋሻዎች፣ ተራሮች፣ ሸለቆዎች እና ኮረብታዎች መገኛም ነው። እንደ ጅብ፣ አቦ ሸማኔ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛ እና የመሳሰሉ የዱር እንስሳት አና አዕዋትም ይገኙበታል።
ሰንሰለታማ ተራሮቹን ጨምሮ በውስጡ የሚገኙት እንስሳት እና ማራኪ የተፈጥሮ ገጽታው በብዙዎች ዘንድ የጉብኝት ማዕከል እንዲሆን አስችሎታል።
አካባቢውን አጼ ኃይለሥላሴ፣ አጼ ፋሲል፣ አጼ ይሳቅ፣ አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ተክለሃይማኖት፣ አጼ ተክለጊዮርጊስ እና ከውጪ ደግሞ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ እንደጎበኙት ድርሳናት እና ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማሉ።
አጼ ኃይለ ሥላሴ የእንግሊዟ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤጥ ጥር 11 ቀን 1957 ዓ.ም ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ ካስጎበኞቸው ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ጭስ ዓባይ እና ኮሶዬ ይገኙበታል።
ንግሥቲቱ ኮሶዬ ከመጡበት ሀገር የአየር ንብረት ጋር ተመሳሳይ እና ምቹ ሆኖ እንዳገኙት ለንጉሡ መግለጻቸው ይነገራል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴም በቦታው ተፈጥሯዊ ውበት ከመማረካቸው የተነሳ ወደ ጎንደር ከተማ በሄዱ ቁጥር ሳይጎበኙት አይመለሱም ነበር።
በሌላ በኩል በኮሶዬ ጅብ ዋሻ በተባለ አካባቢ ቀይ አፈር በብዛት ይገኛል፤ የጎንደር አቢያተ መንግሥታት ሕንፃዎች ሲገነቡም ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ቀይ አፈር በብዛት ይጓጓዝበት ነበር።
አካባቢው በጣልያን ወረራ ጊዜ ለአባት አርበኞች እንደ መጠለያ ሆኖ ማገልገሉም ይጠቀሳል። በደርግ ዘመነ መንግሥት ደግሞ የሎጀስቲክስ ማከማቻ እና የመምሪያ ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር።
የወገራ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አረፈዓይኔ ካሴ ቦታውን ለማስተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ነግረውናል። አቶ አረፈዓይኔ አክለውም ሁለት የእንግዳ ማረፊያ ሎጂዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ከ28 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ወጤቶችን በማስተባበር እና የስካውት ቡድን (የጥበቃ አገልግሎት) በማቋቋም አካባቢውን ለማስተዋወቅ እና ለመጠበቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቦታው ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ መሆኑ በጎብኚዎች ዘንድ ተመራጭ እንደሚያደርገው በማንሳት ከ35 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙኃን፣ በሃገር ውስጥ እና ውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ቦታውን ለማስተዋወቅ እና ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉም ጠይቀዋል።
ማረፊያ
ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ
በ1969 ዓ.ም ተመሠረተ።
በ1978 በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ተመዘገበ።
ከጎንደር ከተማ በሰሜን-ምሥራቅ አቅጣጫ በ122 ኪሎ ሜትር፣ ከደባርቅ ከተማ ደግሞ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ትልቁ ተራራ ራስ ደጀን (4,550 ሜትር) በፓርኩ ክልል ይገኛል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ዋሊያ አይቤክስ (Walia Ibex) – ብቸኛ መገኛው ይህ ፓርክ ነው።
ቀይ ቀበሮ፣ ዝንጀሮ፣ የምኒልክ ድኩላ እና ተኩላ (Ethiopian Wolf) በፓርኩ ከሚገኙ እንስሳት መካካል ናቸው።
በርካታ የተፈጥሮ እፅዋት እና አበቦችም ይገኛሉ።
ከባሕር ወለል በላይ ከሦስት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው በርካታ ሰንሰለታማ ተራሮች ያሉት ፓርኩ የአፍሪካ ጣሪያ በመባልም ይታወቃል።
(ደረጀ ጀርበው)
በኲር የጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


