ኳታር – የበርሃዋ ገነት

0
45
Impressive sunset over Doha's City Center

 በመካከለኛው ምስራቅ ክልል አረብ ባሕረ ሰላጤው የተቀለች ባህረ ገብ መሬት ናት። ሀገሪቱን ከዳር እስከ ዳር ሲዳስሱ ቢውሉ አንድም ወንዝ አያገኙም። የሚጠጣ ውሃ እንኳን የሚያገኙት ከውቂያኖስ ጨዋማውን ውሃ ከጨው አጣርተው በመጠቀም ነው። ሰፊው ክፍሏ በርሃማ ነው። በ11ሺህ 600 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ላይ ያለችው በዓለም ትንሿ ነገር ግን ባለ ግዙፍ ስሟ እና ሀብታሟ አረባዊት ሀገር- ኳታርን የሽርሽር አምዳችን ርእስ አድርገናታል፣ መልካም ንባብ።

በዓለማችን ድሃ ሕዝብ የሌለባት ብቸኛ ሀገር ኳታር ከፍተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ባለቤት ስትሆን በዓለም ሶስተኛ ነዳጅ አቅራቢ ናት። በኳታር እያንዳንዱ ዜጋ ሚሊኒየነር ነው ማለት ይቻላል። ዜጎች ስራ ባይሰሩ እንኳ የካታር መንግሥት  በየወሩ እስከ 2000 ዶላር ይከፍላቸዋል። ትዳር የመሰረቱ ከሆነ ደግሞ እስከ 200ሺህ ዶላር እና የቤት መስሪያ መሬት በነፃ በመስጠት ጎጆ ያወጣቸዋል።

ኳታር በደቡብ ምእራብ የአረብ ባህረ ሰላጤ የምትገኝ ባህረ ገብ መሬት ናት። በደቡብ በኩል ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ትዋሰናለች፣ ብቸኛዋ በመሬት የምትዋሰናት ሀገር መሆኗ ነው። አብዛኛው ወሰኗ በውቂያኖስ የተከበበ ነው። ካታር በስፋት ትንሽ ሀገር ብትሆንም አስደናቂ መልከአምድራዊ አቀማመጥ አላት። በሦሥት አቅጣጫ 563 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የባህር ዳርቻ አላት። ኳታር አንደኛው ክፍሏ ሰፊ በርሃ፣ ሌላው ክፍሏ ደግሞ ሰፊ ውቅያኖስ ነው።

የኳታር መሬት አብዛኛው ለጥ ያለ ሜዳ ሲሆን ከፍታማ የሚባለው ስፍራ 103 ሜትር ይደርሳል። በምእራብ ዳርቻዋ ሰፊ የተንጣለለ የኖራማ አፈር መሬት አለ። ይህ አንዱ የሀገሪቱ የተለየ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ ያለው ስፍራ የሚባል ብቻ ሳይሆን ዋነኛ የነዳጅ ክምችት ስፍራም ነው። ባዶ ምድረበዳ ይምሰል እንጂ የኳታርን የብልፅግና ታሪክ አዲስ ምእራፍ የከፈተ ባለውለታም ነው።

የኳታር ጠቅላላ ሕዝብ እስከ ሦስት ሚሊየን ሲሆን ከዚህ ውስጥ የኳታር ዜጎች 15 በመቶውን ይሸፍናሉ፣ የተቀረው 85 በመቶው ግን የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው። በኳታር ጎዳናዎች የሚዘዋወሩትን ሰዎች የተለያየ የቆዳ ቀለም፣ የተለያየ ቃንቋ ተናጋሪዎች እና የተለያየ የአለባበስ ዘይቤ ይመለከታሉ፤ ይህም የተለያየ ባህል መነሀሪያ አስብሏታል። በኳታር የሚገኙት የውጭ ሀገር ሰዎች አብዛኛውን ቁጥር ሕንዳውያንን የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ከፓኪስታን፣ ከአፍሪካ እና ከሌሎች የእስያ ሀገራት የመጡ ናቸው።

የኳታር ታሪክ ረጅም እና ትንታዊ መነሻ ያለው ነው። ቀደም ባለው ዘመን የተለያዩ ጎሳዎች የሆኑ የተወሰኑ አርብቶ አደሮች ይኖሩባት ነበር። አሳ በማጥመድ እና እርሻ በማከናወን ሕይወታቸውን ይመሩ ነበር።

በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ካታር የአረብ ግዛት አካል በመሆን እስልምናን እንደጀመረች ይነገራል። በ1509 ዓ.ም ፖርቹጋሎች ድንገት አካባቢውን በማጥቃት ከተሞችን አቃጥለው አደፍርሰውታል። በ1547 ዓ.ም ላይ ኳታር እንደገና በኦቶማን ቱርኮች እጅ ወድቃ ከ200 ዓመታት በላይ ተገዝታለች። በ1838 ዓ.ም ሸክ ሙሃመድ ቢን አል ታኒ የኳታራውያን አስተዳደርን መሰረተና የነፃነት ጉዞውን ጀመረ። የኳታር ዘመናዊው ታሪክ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው፤ ሁሉም ነገዶች በአል ታኒ ቤተሰብ አገዛዝ ስር አንድ ላይ በተሰባሰቡበት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ነው። ይህ በሀገሪቱ የተሻለ መረጋጋት እንዲኖር፣ ከጎረቤት ሀገራት ነፃነቷን እንድትቀዳጅ እና በክልሉ ካሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወገኖች ጋር ሚዛናዊ የሆነ ግንኙነት ትፈጥር ዘንድ መንገድ ከፍቷል።

በ1860 ዓ.ም  ሸክ ሙሀመድ ቢን ታኒ በባህረ ሰላጤው ከነበሩት የእንግሊዝ ባለስልጣናት ጋር አንድ ወሳኝ ስምምነት ተፈራረመ። በስምምነቱም እንግሊዝ ኳታርን እንደ አንድ ራሷን የቻለች አካል እውቅና ሰጥቷል። በስምምነቱ መሰረት እንግሊዝ ኳታርን ከማናቸውም የውጭ ትንኮሳዎች ወይም ወረራዎች ለመጠበቅ ቃል ገብታ ነበር። የሆነ ሆኖ በአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ ሩብ ዓመታት ላይ ከወቅቱ ኃያላን ኦቶማን ቱርኮች ግዛት ስር ከመሆን የታደጋት አንድም ኃይል አልነበረም። ስለሆነም የወቅቱ የኳታር አስተዳዳሪ ሸክ ጃሲም ቢን ሙሀመድ፣ ምንም እንኳ እስከ መጀመሪያው የአለም ጦርነት ድረስ የአመለካከት እና የአቋም ልዩነት ቢኖረውም  አል ታኒ ካታርን ከካሊፌት አስተዳደሩ ጋር ትስስሯን ማጠንከር ነበረበት። ነገር ግን ኦቶማን ቱርኮች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በመሸነፋቸው መላው የአረቡ ዓለም ነፃነቱን ሲያገኝ ኳታርም የራሷን እርምጃ ወሰደች። በ1963 ዓ.ም በሸክ ካሊፋ ቢን ሃማድ አል ታኒ አመራር ስር ኳታር ነፃነቷን አወጀች። እናም አዲስ የታሪክ ምእራፍ ተከፈተ።

የኳታር ኢኮኖሚ ታሪክ ከ1931 ዓ.ም በተገኘው ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ተቀየረ። ኳታር በዓለም የነዳጅ አቅራቢነት ሩሲያን ተከትላ በ3ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች። ከነዳጅ ባለፈ ከፍተኛ የተፈጥሮ ጋዝም ሌላው የገቢ ምንጯ ሆነ። እናም ኳታር በዓለም ቢጠሯት የማትሰማ ሀብታም ሀገር ለመሆን ቻለች። በአማካይ የሀገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ 84ሺ440 ዶላር ነው።

ኳታር ዋና የአቪዬሽን ማዕከል ስትሆን በመንግስት ባለቤትነት የተያዘው የኳታር አየር መንገድ ከ170 በላይ መዳረሻዎች እና ከ200 በላይ አውሮፕላኖችን ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል።  ኳታር ኢኮኖሚዋን እያሰፋች፣ የአገልግሎት ኢንዱስትሪዎችን እያሳደገች እና ራሷን የፋይናንስ፣ የትምህርት እና የስፖርት ማዕከል አድርጋለች።

ኢኮኖሚዋ በተለይ  በነዳጅ እና በተፈጥሮ ጋዝ ሀብት የተመሰረተ ቢሆንም ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋን በራሱ እግር ለማቆም የተለያዩ ዘርፎችን እየጨመረች ይገኛል። ፋይናንስ፣ ሪል-ስቴት፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት፣ ህክምና እና ሎጂስቲክስ ተለይተው ማበረታቻ የሚደረግላቸው ዘርፎች ናቸው። እነሱም ሀገሪቱን ከነዳጅ እና ከጋዝ ጥገኛነት ያላቅቃሉ ተብሎ ይታመናል።

ቱሪዝም በኳታር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኝ ዋና ዘርፍ ሆኗል። በዶሃ ያሉ ዘመናዊ ህንፃዎች፣ የባህር ዳርቻ ውብ ቦታዎች፣ የምድረ በዳ ጉብኝት፣ ባህላዊ ገበያዎች እና ባህላዊ ሙዚየሞች ብዙ የዓለም ቱሪስቶችን እየሳቡ ይገኛል። በተጨማሪም የስፖርት ቱሪዝም በካታር እጅግ የተወደደ ሲሆን የፎርሙላ ዋን ውድድሮች፣ የቴኒስ እና ሌሎች ብዙ የዓለማቀፍ ውድድሮችን በማዘጋጀት ከኢኮኖሚዋ ጋር እንዲተሳሰር አድርጋለች። እነዚህ ሁሉ ለኢኮኖሚው ሀብት ወይም ገቢ የሚጨምሩ የወደፊት ተስፋዎቿ ናቸው።

በአጠቃላይ የኳታር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሀብት ሆኖም ይበልጥ እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል፣ ቱሪዝሟም በቅርቡ ሀገር የሚቀይር ዋና የገቢ ምንጭ መሆን እየቻለ ይገኛል። ዜጎቿ ነፃ ትምህርት እና ነፃ ሕክምና የሚያገኙባት እጅግ የናጠጠች ሀብታም ሀገር ናት። ዋና ከተማዋ ዶሃ እጅግ የሚያስደምሙ ዘመናዊ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች የተሞላች ድንቅ አለማቀፍ ከተማ ናት። 80 በመቶ የሀገሪቱ ሕዝብ መኖሪያም ናት።

 

አጭር እውነታ

 

  • ዋና ከተማ: ዶሃ (Doha)
  • ቋንቋ: ዓረብኛ
  • መንግስት ዓይነት: ንጉሳዊ አስተዳደር
  • ገንዘብ: ኳታር ሪያል (QAR)
  • በምብራቅ ሜዲትሬኒያን ባሕር ዳርቻ ላይ እና በዋሽንት እንቅስቃሴ አቅራቢያ፣ በአረብ ባሕር ውስጥ ከፍ ብሏል።
  • መንግስትና ህዝብ
  • ኳታር በትንሽ መሬት ወሰን ነገር ግን በነዳጅ እና በጋዝ ሀብት በጣም የተባለ ነው።
  • የኳታር ህዝብ ብዛት ብዙውን የውጭ ዜጎች ነው።
  • ኢኮኖሚዋ፣ ዋና ገቢዋ በ ነዳጅ እና በተፈጥሯዊ ጋዝ ላይ የተመሰረተ ነው።
  • በዓለም ላይ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ያላት ሀገር ናት።
  • ኳታር ብዙ ዓለም አቀፍ የስፖርት ዝግጅቶች የምታደርግ መሆኑ ይታወቃል።
  • ባህል እና ልማዷ በአረብ ባህል ላይ የተመሰረተ ነው።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የህዳር 15  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here