ወረርሽኙን ለመከላከል ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ

0
80

የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ፤ ወረርሽኙን መከላከል ላይ ያተኮረ ምክክር ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ  ተካሂዷል።

የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ወረርሽኙን መከላከል ላይ የሚሠሩ ባለድርሻዎች በተሳተፉበት ምክክር የኮሌራ በሽታ አሁናዊ ስርጭት እና ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ቀርቧል።

ለውይይቱ መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል ባለሙያ ጥሩነህ ገነት ናቸው፥ ባለሙያው እንዳሉት በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞች ተከስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ ግን በአጣዳፊነቱ የከፋው የኮሌራ ወረርሽኝ ነው።

ወረርስኙ በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ተከስቶ የበርካቶችን ህይወት ነጥቋል። በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ መከሰቱ ተነግሯል።

የምዕራብ ጎንደር ሀገረ ሥብከት ዋና ሥራ አሥኪያጅ ሊቀ አእላፍ አባ ኃይለ ማርያም ያሳይ እንዳሉት በሽታው በቋራ አካባቢ ተከስቷል። በቂ ውኃ አለመኖር እና የመጸዳጃ ቤት እጥረት ደግሞ ለበሽታው መስፋፋት ዋና መንስዔዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክት በመቅረጽ ጭምር ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት ሊቀ አእላፍ በየአብያተ ክርስቶያናቱም ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን አክለዋል። “መናገር እንደ መተግበር አያስቸግርም” ያሉት ሊቀ አእላፍ አባ ኃይለማርያም በተለይ የመንግሥት አካላት የተግባር ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ በበኩላቸዉ በተለይ የሃይማኖት አባቶች ላደረጉት መልካም ተግባር በማመስገን “ይህ ባይሆን ኖሮ ወረርሽኙ ይከፋ ነበር” ብለዋል።

በሽታውን ለመከላከል እንቅፋት ሆነዋል በሚል የተነሱትን ችግሮች የተጋሩት ዋና ዳይክተሩ ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት የተግባር ምላሽ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። ዋነኛ የበሽታው ምንጭ እና አባባሽ ምክንያቶችን የመለየት እና ለባለሙያዎች የኮሌራ ወረርሽኝ ቅኝት እና ምላሽ ሥልጠና መሰጠቱንም አክለዋል።

(ጌትሽጌትሽ ኃይሌ)

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here