ወርቅ የሚተፋው ተራራ

0
198

በደቡብ ዋልታ ግግር በረዶ ንጣፍ መካከል በሚገኘው ኤርባስ ተራራ አናት የሚንፈቀፈቀው  እሳተ ገሞራ በቀን ስድስት ሺህ ዶላር የሚያወጡ የወርቅ ቅንጣቶችን ወደ ገፀ ምድር እንደሚወረውር ኤን ዲ ቲ ቪ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል::

በበረዶ የተሸፈነው ደቡብ ዋልታ በ2017 እ.አ.አ በተደረገ ጥናት 138 እሳተ ገሞራዎች አሉት:: ከነዚህ መካከል ዘጠኙ ንቁ ማለትም  በፍንዳታ ላይ ያሉ ናቸው:: 3 ሺህ 794 ሜትር ከፍታ  ያለው ኤርባስ ተራራ በፍንዳታ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል::

ኤርባስ ተራራ የሮዝ ደሴቶችን ከፈጠሩት ሦስት እሳተ ገሞራዎች አንዱ ነው:: በ1841 እ.አ.አ በቀጣናው የተንቀሳቀሰው መርከበኛ ጂምስ ክላርክ ሮዝ ደሴትን በማግኘቱ ሮዝ ደሴት በስሙ ተሰይሟል:: ኤርባስም ከመርከቦቹ የአንዱን ስያሜ መያዙ ነው በድረ ገፁ የተሰነደው::

በሮዝ ደሴት አቅራቢያ ባማክሙርዶ ጣቢያ፣ የሰፈሩ የአሜሪካ ተመራማሪዎች በኤርባስ ተራራ አናት የሚንፈቀፈቀውን እሳተ ገሞራ በመከታተል ላይ መሆናቸው ነው የተመላከተው:: እ.አ.አ ከ2013 ጀምሮ የሳተላይት /መንኮራኩር/ ምስሎች የቀለጠ የአለት ሀይቅ ምስል እያሳዩ መሆናቸው ተጠቁሟል:: እሳተ ገሞራው እንፋሎት እና የቀለጠ አለት እንደሚያስወነጭፍ አልፎ አልፎም ቋጥኝ አለት እንደሚወረውርም ነው ድረ ገፁ ያስነበበው::

ከእሳተ ገሞራው አፍ ከሚፈተለከው ቅላጭ መካከል ስብርባሪ መስታዎት መሰል የወርቅ ቅንጣቶችን አስወንጭፎ እንደሚያዘንብም ነው የተረጋገጠው::

እሳተ ገሞራው በቀን እስከ 80 ግራም የወርቅ ስብርባሪ ወይም ብናኞችን እንደሚረጭ ነው ባለሙያዎቹ ያስቀመጡት:: የወርቅ ስብርባሪው ወደ ገንዘብ ሲለወጥ በቀን ስድስት ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ ነው ድረ ገፁ በማጠቃለያነት ያሰፈረው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here