ወርኃ ጥር

0
153

የግዕዝ እና የባህል ጥናት ድርሳናት እንደሚያስረዱት  ጥር  የሚለው ቃል አመጣጥ ከሁለት ዋና ዋና ፅንሰ ሀሳቦች ጋር ይያያዛል:: አንደኛው “ጠረረ” (ፀሐይ በረታ)  ከሚለው  ግስ የተወሰደ  ነው:: ይህም የክረምት ደመና ተገፎ ፀሐይ የሞቀችበት እና ሰማይ የጠራበት  ወር  መሆኑን  ያመለክታል:: ሁለተኛው  እና  በሊቃውንት  ዘንድ  በስፋት የሚነገረው ደግሞ ጥሩ ወይም ጥሬ ከሚለው ጋር ይያያዛል::

ወሩ እህል በብዛት የሚገኝበት፣ ጥራጥሬ የሚገኝበት፣ የሰው አካል ከጾም በኋላ የሚጠገንበት ወር በመሆኑ ነው:: በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል ጥር የሆድ ወር ተብሎም ይጠራል:: ይህ ስያሜ የመጣው አዝመራው ተሰብስቦ ቤቱ በበረከት ስለሚሞላ ነው:: ብዙ ድግሶች ስለሚደረጉ ነው:: ድግሱን ለመብላት በዓላት በዝተው ቀኑ የሚያንስ የሚመስልበት ነው:: ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች በስፋት ያሉበት ነው:: ጥር ወር በዓላት የሚጋፉበት ወር ነው:: በተለይም በአማራ ክልል በሁለት ግዙፍ የዩኔስኮ ቅርሶች ባሉበት ስፍራ በደማቅ ሁኔታ  በዓላት ይከበራሉ::

ቀደም ብሎ ታህሳስ 29 የሚከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (ገና) በዓል በቅዱስ ላሊበላ ድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚኖረው ድባብ ዓለምን ያስደምማል:: “ቤዛ ኩሉ ዓለም” የሚባለውን ያሬዳዊ ዜማ ለመስማት እና የሌሊቱን ማኅሌት ለመታደም በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ወደ ላስታ ይተማሉ::

ቀጥሎ ጥምቀት እና የጎንደር ልዩ ድባብ ይመጣል:: የጥር ወር ቁንጮ በዓል ጥምቀት ነው:: የአደባባይ በዓልም መሆኑም ልዩ ነው:: በተለይም በጎንደር ፋሲለደስ መዋኛ ገንዳ የሚደረገው የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ እሴቱ ከባህላዊው አልባሳት፣ ከሽበሸባው እንዲሁም ከሆታው ጋር ተዳምሮ የሚቀርብበት ነው:: “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ብሂል ወሩን የፋሽን እና የውበት መገለጫ ያደርገዋል:: ወጣቶች የሚተያዩበት፣ ሎሚ የሚወራወሩበት እና የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ሊያገኙ የሚችሉበት የትውውቅ አውድም ይሆናል:: የሐበሻ ቀሚስ ለብሶ መዘነጥ ጥርን ልዩ ድምቀት ይሰጣታል::

ቱሪስቶች ወደ ጎንደር የሚጎርፉት ታቦታቱ ሲወጡ የሚደረገውን በቀለማት ያሸበረቀ ባህላዊ አልባሳት፣ የካህናቱ ዝማሬ እና የህዝቡን እልልታ ለማየት ነው:: ይህ ክዋኔ ጎንደርን የዓለም የባህል ቱሪዝም መዳረሻ ያደርጋታል:: ሆቴሎች ከወራት በፊት ይያዛሉ:: የአካባቢው ኢኮኖሚም ይነቃቃል::

ውቢቷ ባህርዳር ጥርን በባህርዳር ብላ ከሚያምረው ሐይቅ ጋር ውበቷን ጠብቃ በስፖርታዊ ክዋኔዎችና ዝግጅቶች ትደምቃለች:: በጥር 18 ቀን ሰባሩ ጊዮርጊስን ታከብራለች:: የጀልባ ትርኢት ይደረጋል:: እንጅባራ ከተማ ደግሞ ጥር 23 የአገው ፈረስ ባህልን በደማቅ ሁኔታ ታከብራለች:: ይህ ሁሉ ሲሆን በዓላት በየአካባቢው ታቦታት እየወጡ ይከበራሉ:: ከዘገሊላ እስከ አስተርዮ ማርያም ያሉ ታቦት ከማደሪያው ወጥቶ የሚከብርባቸው ማራኪ በዓላት አሉ::

በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለሚከተለው በተለይም አማራ ማህበረሰብ ጥር ወር ማለት ልክ እንደ ወርሃዊ ደመወዝተኛው የወር መጨረሻ ወይም የደመወዝ ቀን ማለት ነው:: ገበሬው ምርቱን ሰብስቦ ሸጦ ገንዘብ የሚያገኝበት ወቅት ነው:: ገበሬው በክረምት (ከሰኔ እስከ መስከረም) በዝናብ፣ በጭቃ እና በብርድ ሲያርስ፣ ሲዘራ እና ሲያርም የከረመው አዝመራ ጥቅምት እና ህዳር ላይ ታጭዶ፣ በታህሳስ ተወቅቶ፣ በጥር ወር ወደ ጎተራ ይገባል::

ይህ ወቅት ገበሬው የዓመት ቀለቡን አስቀርቶ ትርፍ ምርቱን ወደ ገበያ የሚያወጣበት ጊዜ ነው:: በዚህ ወቅት የገጠር ገበያዎች በእህል ይጥለቀለቃሉ:: ጤፉ፣ ስንዴው፣ በቆሎው እና ጥራጥሬው ተሽጦ የገበሬው ኪስ በጥሬ ገንዘብ የሚሞላው በዚህ ወር ነው:: ይህም የገበሬውን የመግዛት አቅም ይጨምረዋል:: የገንዘብ አቅም ሲዳብር ማህበረሰቡ ልጁን ስለመዳር ማሰብ ይጀምራል:: የሰርግ ሐሳብ ይመጣል::ጥር የሠርግ ወቅት ነው:: በኢትዮጵያ ባህል ሰርግ ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል::

አንድ አባት ለልጁ ሠርግ ለመደገስ ጥሎሽ ለመስጠት (ለሙሽሪት ልብስና ጌጣጌጥ ለመግዛት) ለድግሱ በሬ ለመግዛት የግድ ጥርን መጠበቅ ሊኖርበት ይችላል:: የማህበረሰቡ ማህበራዊ ትስስር የሚጠናከረው በእነዚህ ድግሶች በሠርግ እና ሌሎች ድግሶች ነው:: ለዚህ ሁሉ ማስፈጸሚያ የሚሆነው ገንዘብ የሚገኘው ከጥር ወር የአዝመራ ሽያጭ ነውና::

በኢትዮጵያ የገጠሪቱ ክፍል ጥር የጫጉላ ወር ነው ማለት ይቻላል:: ከጥምቀት መልስ ሠርግ በጣም ይደራል:: ገበሬው ምርቱን ሰብስቦ ሸጦ ገንዘብ የሚያገኝበት ወቅት ይሆናል:: የግብርና ሥራ ተጠናቆ ገበሬው የሚያርፍበት ጊዜ ነው:: ዝናብ የሌለበትና ለድግስ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት አለ:: በጥር ወር በጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ እና በሸዋ አካባቢዎች የፈረስ ጉግስ፣ የሽለላ እና የፉከራ ባህሎች ጎልተው ይታያሉ::

የፈረስ ጉግስ በተለይ በጥምቀት ዕለት የሚደረግ ሲሆን የወንዶች ወኔ እና ጀግንነት መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል:: ጎበዝ ፈረስ ጋላቢ በቆንጆ ሴት ልብ ውስጥ የመግባት እድል ያገኛል:: ይህ ወደ ሠርግ ያመራል::

በአማራ ክልል የገጠሩ ክፍል የሚደረጉ ባህላዊ ሠርጎች ለውጭ ቱሪስቶች እጅግ ይናፍቃሉ:: ሙሽራው በፈረስ ታጅቦ ሲሄድ፣ ሙሽሪት በምርጥ የሀገር ባህል ልብስ ተውባ ስትታይ፣ የዘመድ አዝማድ እስክስታ እና ጭፈራ ለቱሪስቶች ትክክለኛውን ባህል የመቅሰም ዕድል ይሰጣል:: ቱሪስቶች ዘመናዊ ወይም በሆቴል የተዘጋጀ ሠርግ ሳይሆን ትክክለኛውን የህዝብ አኗኗር በዚህ ወር ያገኙታል::

ጥር ለኢትዮጵያ ገበሬ የእህል አዝመራ መሰብሰቢያ ብቻ ሳትሆን ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍም “የብር አዝመራ” የሚሰበሰብባት የዓመቱ የንግሥ ወር ናት:: በተለይም የኢትዮጵያ የቱሪዝም የጀርባ አጥንት በሆነው በአማራ ክልል ጥር ወር ከቀን መቁጠሪያነት አልፋ ህያው የባህል፣ የታሪክ እና የኪነጥበብ ፌስቲቫል ሆና ትገለጣለች::

በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ንግድ ቋንቋ ጥር ወር ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰት ጣራ የሚነካበት ወቅት ተብላ ትታወቃለች:: ለዚህም ሦስት አበይት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ:: አንደኛው የአየር ንብረቱ ምቹነት ነው:: የክረምት ዝናብ እና ጭቃ የሌለበት፣ ፀሐያማ እና ለጉዞ ምቹ የሆነ የአየር ሁኔታ አላት:: ሁለተኛው የአዝመራ ወቅት መሆኑ ነው:: ምድሪቱ አረንጓዴዋን ወደ ወርቃማ ቀለም ቀይራ ተፈጥሮ ምርት የምትሰጥበት ወቅት ነው:: ለፎቶግራፍ እና ለዕይታ የምትመችበት ጊዜ ነው:: ሦስተኛው የበዓላት መደራረብ ነው:: የገና እና የጥምቀት በዓላት መከበር የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር በእጥፍ ይጨምረዋል:: የሀገር ውስጡ ቱርስት ፍሰት በጣም ይጨምራል:: የዓመት ንግሥ በዓላት በስፋት በየአካባቢው ይከበራሉ::

በአማራ ክልል በተለይም በጎጃም (አዊ እና ምዕራብ ጎጃም)፣እንዲሁም በወሎ እና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ጥር ወር የፈረስ ጉግስ ወር ነው:: ቱሪስቶች በካሜራቸው ሊያስቀሩት የሚጓጉት፣ ያጌጠ ፈረስ የጫነውን፣ የነብር ለምድ የለበሰውንና ጦር የሰብቀውን ኢትዮጵያዊ ጀግና ምስል ነው:: ይህ ወታደራዊ የሚመስል ባህላዊ ትርኢት፣ ለቱሪዝሙ ዘርፍ ልዩ የሆነ የክዋኔ ቱሪዝም ገበያ ይፈጥራል:: በእንጅባራ የሚከበረው የአገው ፈረስ ባህል በዚህ ጥሩ ነው:: በጥር 23 ገራሚ የፈረስ ትዕይንት ይታያል::

ጥር ወር በኢትዮጵያ ምድር በተለይም በአማራ ክልል ከወርም በላይ ናት:: የተፈጥሮ ውበት፣ የረቀቀ ሀይማኖታዊ ስርዓት፣ አስደምሚ ታሪካዊ ቅርሶች እና ህያው የማህበረሰብ ትውፊቶች በአንድ ላይ ተሰባጥረው የሚታዩባት ወር ናት::

 

ማረፊያ

አሲና በል አሲና ገናዬ

በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ

በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፡፡

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥግ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here