ወሳኙ ወቅት

0
58

ወቅቱ የእርሻ ሥራ በስፋት የሚከናወንበት ነው። ከመቼውም ጊዜ በተለየ ስንፍና ተወግዞ፤ ብርታት ተሰንቆ ለተሻለ ምርት ቀን ከለሊት የሚተጋበት ነው፡፡ የእርሻ እና የዘር ወቅት በመሆኑ ማሳዎች አንድም በትራክተር በሌላም በበሬ የሚደምቁበት፣ በሬ እና አርሶ አደሩ ለላቀ ሥራ እና ስኬት ውሎ አዳራቸው ከማሳ የሚሆንበት የአርሶ አደሩ ልዩ ወቅት ነው። አርሶ አደሮች ሥራን በጋራ እየከወኑ በባሕላዊ የሥራ ዘፈኖች፣ በቃል ግጥሞች ጀግናው የሚሞገስበት፣ ሰነፉ የሚወቀስበት ወቅት ነው መኸር።

 

“ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣

ወፍጮው እንዳጎራ መስከረም ዘለቀ!”

ሲሉ አራሹ፣ ጎበዙ ገበሬ ቤቱ ሙሉ መሆኑ ይነገርለታል።

በተቃራኒው ደግሞ አምርቶ ምርቱን  ለገበያ ማቅረብ ቀርቶ ቤተሰቡን መመገብ ያልቻለው ሰነፍ ገበሬ፡-

“በበጋ እንዳያርስ ፀሐይ እየፈራ፣

ክረምት እንዳይሠራ ዝናብ እየፈራ፣

ልጁ እንጀራ ቢለው በጅብ አስፈራራ!”

በሚሉ ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ሰነፍ ገበሬ ይወቀሳል።

 

እንዲህ አይነት ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ሰዎች ለሰዎች በቀጥታ መንገር ባይፈልጉም በተዘዋዋሪ ከጎናቸው ያለውን “ንቃ እረስ፣ ከድህነት ተላቀቅ” ማለታቸው ነውና ላለመሰደብ የሚታትረው እንዲበዛ ያደርጋሉ። አርሶ አደሮች በሥራቸው መሐል የሚሰነዝሯቸው የቃል ግጥሞች  ሙገሳ ወይም ወቀሳ ብቻ አይደለም፤ ታሪክ የሚተረክበት፣ መፍትሔ አመላካች ሐሳቦች፣ ልምድ እና ተሞክሮን ጨምሮ መረጃም የሚለዋወጡበት የመመማሪያ መንገድ ነው።

“ጎበዝ እርሻ እረሱ እርሻ ነው ሞገሱ፣

ቡና ሲፈላ እንኳን ይቸግራል ቁርሱ!” በማለት መሬትን በወቅቱ አርሶ ማዝመርን ያበረታታሉ።

የእርሻ ሥራውን ለማቀላጠፍ ግንባር ቀደም የሆነው የገበሬው የእርሻ በሬም

“አያበሬ ሆይ፣ አያበሬ ማሩ፣

“ኑርልኝ በርታልኝ ብላልኝ ከሳሩ!” እየተባለ ይገጠምለታል።

 

ከላይ ያነሳናቸው ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ወቅትን ተከትለው በስፋት የሚነገሩ ናቸው፤ ይህ ወቅት ደግሞ አርሶ አደሩ የክረምቱን ዝናብ ተጠቅሞ መሬቱን አለስልሶ፣ የግብርና ግብዓቶችን ተጠቅሞ የሚዘራበት፣ ቀድመው ለተዘሩት ደግሞ የሚኮተኩትበት እና የሚያርምበት ነው፡፡

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ወቅት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የአፈር ማዳበሪያ መሰራጨቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። አርሶ አደሮቹም የዋጋ ውድነቱ በአፈር ማዳበሪያ አጠቃቅማቸው ላይ ጫና ቢፈጥርባቸውም በወቅቱ እየገዙ ዘራቸውን እየዘሩ ይገኛሉ። ለአብነትም በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ ጣራ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ዲያቆን ግርማው አዱኛ ለበኩር እንደተናገሩት የክረምት እርሻ ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። ከራሳቸው የእርሻ መሬት ባሻገር ከሌሎች መሬት በመከራየት ሰብል እያለሙ መሆኑን ነግረውናል። አሁን ላይም ጤፍ እና ማሽላ ዘርተው እየተንከባከቡ መሆኑን በስልክ ነግረውናል። የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ ጥሩ ቢሆንም የዋጋ ጭማሪው ግን አቅምን የሚፈታተን ነው ብለውታል።

 

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ ደንቡን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ልጃለም ደመላሽ ናቸው። አርሶ አደሩ የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፤ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ። አለፍ ሲልም ለገበያ ያቀርባሉ። በ2017/18 የምርት ዘመን ሁለት ሄክታር መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ቀድመው ደጋግመው በማረስ መሬታቸውን በሚገባ አለስልሰዋል።

 

አቶ ልጃለም ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚያገለግል አራት ኩንታል ዳፕ እና አራት ኩንታል ዩሪያ በመግዛት ጥቅም ላይ እያዋሉ ነው። በቆሎ፣ በርበሬ፣ ስንዴ፣ ዳጉሳ እና ገብስ ዘርተዋል። የሰብሉ ቡቃያው ያማረ ነው ብለዋል።

እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ እየተሻሻለ ቢመጣም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የምርት ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በአፈር ማዳበሪያ ላይ መደረጉ በአርሶ አደሮች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል፤ በተመሳሳይ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።

 

የአርሶ አደር ዲያቆን ግርማውን እና የአርሶ አደር ልጃለምን የመኸር እርሻ ሥራን ተመለከትን እንጂ በአማራ ክልል የሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮችም ማሳቸውን አርሰው አለስልሰው በወቅቱ በዘር በመሸፈን እየተንከባከቡ ይገኛሉ።

 

የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ዮሐንስ ይግዛው ለ2017/18 የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለማግኘት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። ከቅድመ ዝግጅቶች መካከልም በየወረዳው የሚገኙትን የግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮችን ለማገዝ የሚያስችል ስልጠና መስጠት፣ የሚታረስ መሬት መለየት እና ለሥራው የሚውል ግብዓት ማቅረብ ተጠቃሽ ናቸው።

 

ምክትል ኃላፊው ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት 120 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እስካሁንም 118 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥ 97 ሺህ 850 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት። ገብስ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ባቄላ እና ሽምብራ በዋናነት የተዘሩ ሰብሎች መሆናቸውን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል። ቀሪ በዘር ያልተሸፈኑ ማሳዎች እስከ ሐምሌ መጨረሻ በዘር ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

 

እንደ ምክትል ኃላፊው ማብራሪያ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ አፈር ማዳበሪያ ለማሰራጨት ታቅዷል። እስካሁን 54 ሺህ ኩንታል ወደ ዞኑ ገብቷል። ከባለፈው ዓመት የከረመን ጨምሮ 49 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። 12 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል።

 

ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ ከአንድ ነጥብ 8 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ በላይ በበጋ የተዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለአገልግሎት እንዲውል መደረጉን አብራርተዋል፡፡ ዞኑ በምርት ዘመኑ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሠብሠብ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

 

በተመሳሳይ የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ለ2017/18 የመኸር ወቅት ለአርሶ አደሩ የዘር ወቅት ሳያልፍበት የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አጉማሴ አንተነህ እንዳሉት በዞኑ በ2017/18 የመኸር ምርት ዘመን 305 ሺህ 271 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን እስካሁን 305 ሺህ 656 ሄክታር መሬት ታርሷል። ከታረሰው መሬት ውስጥ 218 ሺህ 898 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል። አሁን ላይ በቆሎ፣ ገብስ፣ አኩሪ አተር፣ ስንዴ፣ ዳጉሳ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ፣ ድንች እና በርበሬ የተዘሩ ዋና ዋና ሰብሎች ናቸው።

 

በምርት ዘመኑ ለዞኑ ከሚያስፈልገው አንድ ሚሊዮን 76 ሺህ 756  ኩንታል የአፈር ሚዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 590 ሺህ 26 ኩንታል በዞኑ ማዕከላት ገብቷል። ከዚህ ውስጥ 545 ሺህ 15 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል። ከዞኑ አርሶ አደር ፍላጎት አኳያ በቂ የአፈር ማዳበሪያ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ አጉማሴ በተለይ ዩሪያ መዘግየት እና እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።

 

ምክትል መምሪያ ኃላፊው አክለውም 30 ሺህ 879 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 30 ሺህ 590 ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን አስረድተዋል። በ2017/2018 የምርት ዘመን 17 ሚሊዮን 43 ሺህ 894 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለበኩር ጋዜጣ እንደተናገሩት ክልሉ ለ2017/18 የምርት ዘመን የመኸር እርሻ የዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

 

በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ በዋናነት ለኩታ ገጠም እርሻ ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ዳይሬክተሩ በአጠቃላይ በክልሉ በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ከታቀደው አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታሩ በኩታ ገጠም እርሻ የሚለማ ነው ብለዋል፡፡

በኩታ ገጠም ከሚታረሰው መሬት ውስጥም ሁለት ሚሊዮን ሄክታሩ ታርሷል። 300 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።

 

ወቅቱ የእርሻ ሥራ የሚሠራበት እና የታረሰውንም በዘር የመሸፈን ሥራ የሚከናወንበት ነው፤ በዕቅድ ከተያዘው  አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክተር መሬት  ውስጥ አምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መታረሱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ከታረሰው መሬት ውስጥ  ሦስት ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት በተለያዩ ሰብሎች  በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡

በክልሉ ከመኸር እርሻ ለማግኘት ከታሰበው 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት 116 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው በኩታ ገጠም ከሚታረሰው ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡

 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሽራ ሲሳይ ለበኩር እንደተናገሩት ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው። አዳዲስ አሠራሮች፣ ቴክኖሎጂዎች እና የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች የምርታማነት መሠረት ናቸው፡፡

ወ/ሮ ሙሽራ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ግዥ ከተፈፀመው ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታሉ ወደብ ደርሷል። ከዚህ ውስጥ አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ወደ ክልሉ ገብቷል።

 

በበጋ መስኖ እና በመኸር የሰብል ልማት አምስት ሚሊዮን 249 ሺህ 657 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል። ቀሪው የአፈር ማዳበሪያ ፈጥኖ ወደ ክልሉ ገብቶ በወቅቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ከትራንስፖርት እና ከፀጥታ ዘርፉ ጋር በቅንጅት እየተሠራም ነው።

በዚህ ዓመት ወደ ክልሉ ለማስገባት የታቀደው የአፈር ማዳበሪያ ከባለፈው ዓመት የ742 ሺህ ኩንታል ብልጫ እንዳለው ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በአቅርቦቱ በኩል መጠነኛ መዘግየት ቢታይበትም ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ወ/ሮ ሙሽራ ገልፀዋል። ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የፌደራል መንግሥት ከ84 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉንም አክለዋል።

 

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ በምርት ዘመኑ 200 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ታቅዶ 145 ሺህ 495 ኩንታል ምርጥ ዘር ተሰራጭቷል። በዋናነት በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር፣ ባቄላ፣ ሽምብራ እና ሩዝ ተሰራጭተዋል። በቀጣይም የጥራጥሬ ምርጥ ዘር በስፋት ይሰራጫል።

 

ግብዓት ሲባል የአፈር ማዳበሪያ ብቻ አለመሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ የተሻሻለ ምርጥ ዘር፣ የአሲዳማ አፈር ማከሚያ ኖራ፣ ኬሚካል፣ ቴክኖሎጂ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።

 

ሌላው የአርሶ አደሩን ጉልበት፣ ጊዜ እና ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የምርት ብክነትን ለመከላከል ቴክኖሎጂን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል። በዚህ ዓመትም 201 ትራክተር፣ 22 የምርት መሰብሰቢያ ማሽን (ኮምባይነር) እና 180 አነስተኛ የሰብል መውቂያ (ትሬሸር) ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል።

የታለመው ዕቅድ እንዲሳካ ማሳን ደጋግሞ ማረስ፣ ግብዓትን በወቅቱ ማቅረብ፣ አረምን በአግባቡ ማረም፣ የእርሻ ሜካናይዜሽንን መጠቀም፣ ሰብልን መንከባከብ፣ ዕለታዊ የተባይ አሰሳ ማድረግ እና ሌሎች ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወን ይገባል። ግብዓት በወቅቱ እና በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

መረጃ

ግብርና ማለት በእንስሳት እና ዓሳ፣ በሰብል (እህል፣ አትክልት፣ በፍራፍሬ፣ ቡና፣ ሻይ እና ቅመማቅመም)፣ በደን ምርት ማምረትን፣ የምርት አሰባሰብን፣ ድህረ ምርት አያያዝን፣ ዕሴት መጨመርን፣ ግብይት እና እስከ አጠቃቀም ያለውን ሂደት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ አጠባበቅ እና አጠቃቀምን የሚያካትት ዘርፍ ነው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሐምሌ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here