ወሳኙ ወቅት …

0
12

ወቅቱ የሰብል እንክብካቤ በስፋት የሚከናወንበት ነው። ከመቼውም ጊዜ በተለየ ስንፍና ተወግዶ፤ ብርታት ተሰንቆ ለተሻለ ምርት የሚተጋበትም ነው፡፡ በአብዛኛው የአረም እና የኩትኳቶ ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ለማግኘት ሙሉ ጊዚያቸውን በማሳቸው (በአዝመራቸው) የሚያሳልፉበት ወቅት ነው። አርሶ አደሮች ሥራን በጋራ እየከወኑ በባሕላዊ የሥራ ዘፈኖች እና በቃል ግጥሞች ጀግናው የሚሞገስበት፣ ሰነፉ ደግሞ የሚወቀስበት ወቅት ነው።

“ያረሰማ ጎበዝ እርፍ የነቀነቀ፣

ወፍጮው እንዳጎራ መስከረም ዘለቀ!”

ሲሉ አራሹ፣ ጎበዙ ገበሬ ይወደሳል፤ ቤቱ ሙሉ መሆኑም ይነገርለታል።

በተቃራኒው በዚህ ወቅት ጊዜውን የሚያባክን፣ ማሳውን ያልተንከባከበ፣ አምርቶ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ቀርቶ ቤተሰቡን መመገብ ያልቻለው ሰነፍ ገበሬ ደግሞ፡-

“ሰነፉ ያረመው ተመልሶ አረም ነው፣

አረምን ከስሩ ነቃቅሎ መጣል ነው!

ያላረሰ ጎበዝ ደፍሮ ያላረመ፣

ከማንም ማዕድ ላይ ሲለምን ከረመ!”

በሚሉ ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ይወቀሳል።

እንዲህ አይነት ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ሰዎች ለሰዎች በቀጥታ መንገር ባይፈልጉም በተዘዋዋሪ ከጎናቸው ያለውን “ንቃ፣ እረስ፣ አርም፣ ኮትኩት ከድህነት ተላቀቅ” ማለታቸው ነውና ሰነፉ ገበሬ ላለመሰደብ፣ ቤተሰቡንም በአግባ እንዲመራ፣ የሚታትረው ገበሬ እንዲበዛ ያደርጋሉ።

አርሶ አደሮች በሥራቸው መሐል የሚሰነዝሯቸው የቃል ግጥሞች  ሙገሳ ወይም ወቀሳ ብቻ አይደሉም፤ መፍትሔ አመላካች ሐሳቦች፣ ልምድ እና ተሞክሮን ጨምሮ መረጃም የሚለዋወጡበት የመመማሪያ መንገድ ነው።

“ሲያርሙ ተው አርም ሲሠሩ ተው ሥራ፣

በግንቦት አይገኝ የሰው ቤት እንጀራ!” በማለት ሰብልን በወቅቱ ማረም፣ መኮትኮት እና መንከባከብ እና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ ሐሳባቸውን ያቀርባሉ።

ከላይ የጠቀስናቸው ሥነ ቃላዊ ግጥሞች ወቅትን ተከትለው በስፋት የሚነገሩ ናቸው፤ ይህ ወቅት ደግሞ አርሶ አደሩ የክረምቱን ዝናብ ተጠቅሞ መሬቱን አለስልሶ፣ የግብርና ግብዓቶችን ተጠቅሞ የሚዘራበት፣ ቀድመው የተዘሩትን ደግሞ የሚኮተኩትበት እና የሚያርምበት ነው፡፡

በዚህ ወቅት በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የእርሻ፣ የዘር፣ የኩትኳቶ፣ የአረም እና የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን እየተከናወኑ ነው፤ በተለያዩ የሚገኙ አርሶ አደሮችም ሐሳባቸውን ለበኩር አጋርተዋል።

ሐሳባቸውን በስልክ ካጋሩን አርሶ አደሮች መካከል ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 03 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መሀመድ ሁሴን አንዱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የመኸር የሰብል ልማት ሥራቸውን እያከናወኑ ነው። በአንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸው ስንዴ፣ ጤፍ እና ማሽላ ዘርተው እየተንከባከቡ መሆኑን በስልክ ነግረውናል። የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ በወቅቱ እና በመጠን መቅረቡ ጥሩ ቢሆንም የዋጋ ጭማሪው ግን ከባለፉት ዓመታት በእጅጉ መወደዱን ነው የነገሩን።

አርሶ አደሩ እንዳሉን ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በመጠቀም ምርታቸውን ለማሳደግ እየሠሩ ነው። አሁን ላይም የሰብሉ ቁመና ጥሩ ነው፤ ወቅቱን ጠብቆ በማረም፣ በየጊዜው የተባይ አሰሳ በማድረግ እና የግብርና ባለሙያዎችን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ለሰብሉ አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋሉ። በአጠቃላይ በምርት ዘመኑ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው።

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ ሸክላ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር መካሻ ሁሴን ናቸው።  በ2017/18 የምርት ዘመን አራት ሄክታር መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን ቀድመው ደጋግመው በማረስ ነው መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች መሸፈን የቻሉት።

አርሶ አደር መካሻ እንዳሉት ምርትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ግብዓቶችን ቀድመው በመግዛት ዝግጅት አድርገዋል።  ለአብነትም ምርጥ ዘር፣ ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችን ቀድመው በእጃቸው አስገብተዋል። በአጠቃላይ በዚህ ወቅት በአራት ሄክታር መሬታቸው ላይ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ በቆሎ እና ማሽላ ዘርተዋል። የአንደኛውን ዙር የሰብል አረም አጠናቀው ለሁለተኛው አረም እየተዘጋጁም ነው። የተዘሩ ሰብሎችን ከመንከባከብ ጎን ለጎን በመስከረም ለሚዘሩት መስኖ ዝግጅት እያደረጉም ነው።

የአርሶ አደር መካሻ ሁሴን እና የአርሶ አደር መሀመድ ሁሴን የመኸር እርሻ ሥራን ተመለከትን እንጂ በአማራ ክልል የሚገኙ ሌሎች አርሶ አደሮችም ማሳቸውን አርሰው አለስልሰው በወቅቱ ዘርተው፣ እየኮተኮቱ፣ እያረሙ፣ ከተባይ እና ከበሽታ እየተከላከሉ ስለመሆኑ ነው የነገሩን።

ከመኸር የእርሻ ሥራ ጋር በተገናኘ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ለ2017/18 የምርት ዘመን የተሻለ ምርት ለማግኘት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውቋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ቡድን መሪ ደጀኔ ከበደ ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ 58 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እንደ ቡድን መሪው ገለፃ የታቀደውን ምርት ለማግኘት ከሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ በበጋ የተዘጋጀ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለአገልግሎት እንዲውል ተደርጓል፡፡ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት (ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም) 58 ሺህ 764 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል አይነቶች በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት። ከዚህ ውስጥ 37 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በማሽላ የተሸፈነ መሆኑን ቡድን መሪው ገልፀዋል። ማሳን በኩታ ገጠም (በክላስተር) የመዝራት ልምዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።

ሰብልን በኩታ ገጠም መዝራት ከእርሻ ዝግጅት እስከ ሰብል ስብሰባ በተመሳሳይ ሰዓት ሥራን በመከወን በአርሶ አደሮች መካከል የልምድ ልውውጥ እና ውድድር እንዲኖር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑንም  አብራርተዋል።

ማሽላ፣ ማሾ፣ በቆሎ እና ጤፍ በስፋት በምርት ዘመኑ የተዘሩ ሰብሎች ናቸው። በዚህ ወቅትም የአረም፣ የኩትኳቶ፣ የተባይ አሰሳ፣ ጥበቃ እና ከበሽታ የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው። ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬት በአንደኛው ዙር አረም ማረም ሲቻል በሁለተኛው ዙርም እስካሁን 20 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሟል። አርሶ አደሩ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን በባሕላዊ እና በዘመናዊ መንገድ እየተከላከሉ ነው።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም የሰብል አይነት ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ነው  ብለዋል። የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ወቅቱ አርሶ አደሮች አረም የሚያርሙበት፣ የተባይ እና በሽታ የማሰስ ሥራ የሚከናውኑበት በመሆኑ የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፋቸውን  ሊያጠናክሩ  እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን በ2017/18 የምርት ዘመን 432 ሺህ 168 ሄክታር መሬት በማረስ 15 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። የታቀደውን ምርት ለማግኘትም ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 424 ሺህ 370 ሄክታር መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች በዘር መሸፈኑን የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል። በስንዴ ዘር ለመሸፈን ከታቀደው 222 ሺህ 243 ሄክታር መሬት ውስጥ 218 ሺህ 210 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን እና ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ከታቀደው 631 ሺህ 476 ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 481 ሺህ 404 ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተሠራጭቶ ጥቅም ላይ ውሏል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) እንዲጠቀም ግንዛቤ በመፈጠሩ ልምዱ እየተሻሻለ መጥቷል።

በተመሳሳይ 28 ሺህ 175 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብ ታቅዶ 17 ሺህ 876 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል። የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የኖራ አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት መዘግየት እና በቂ ዩሪያ አለማቅረብ በግብርና ሥራው ላይ እንቅፋት እንደነበሩ ጠቁመዋል።

ሆኖም በዚህ ወቅት ስንዴ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ባቄላ፣ ቦሎቄ፣ ማሾ እና የቢራ ገብስ በዋናነት ተዘርተው እንክብካቤ እየተደረገላቸው የሚገኙ ሰብሎች መሆናቸውን ነው አቶ ይመር ያብራሩት። አጠቃላይ የዞኑ ሰብል በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ይመር የታቀደው ምርት እንደሚገኝ አመላካች መሆኑንም አንስተዋል።

የሰብል ልማት ቡድን መሪው እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በዞኑ አንደኛ ዙር አረም ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ዙር አረም ተገብቷል። በወረዳ እና በቀበሌ የሚገኙ ባለሙያዎችም በሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በየጊዜው አርሶ አደሩን ሙያዊ እገዛ ማድረግ እና ምክረ ሐሳባቸውን እያካፈሉ ነው።

በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘትም ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት ታቅዶ እስከ አሁን ድረስ ከስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተሠራጭቷል።

በአጠቃላይ በክልሉ በ2017/18 የምርት ዘመን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ አበበ አናጋው ለበኩር ጋዜጣ ተናግረዋል። ባለሙያው እንዳብራሩት የታቀደው ምርት እንዲገኝ የበቀለውን ሰብል በወቅቱ ማረም፣ ከተባይ  እና ከበሽታ መከላከል፣ መጠበቅ፣ መኮትኮት፣ ግብዓት መጨመር እና ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ  እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በሽታ፣ ተባይ፣ አረም፣ … በሰብል ልማት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ተረድቶ በትጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት የነበረውን በጋራ (በደቦ፣ በወንፈል) የመሥራት ባሕሉን በአረም፣ በኩትኳቶ እና በሌሎች ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል። አረም ለሰብሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን እና በውድ ዋጋ የተገዛውን ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በመሻማት ሰብሉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ እንዲሁም እንዳያፈራ ያርገዋል፤ በመሆኑም በወቅቱ አረምን ከሰብሉ ነፃ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከአረም ሥራው ጎን ለጎን የተባይ አሰሳ እና ክትትል እንዲያደርግ መልዕክት ያስተላለፉት የሰብል ልማት ባለሙያው በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ ሙያዊ እገዛቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። አርሶ አደሩ ማሳውን በየቀኑ ማሰስ፣ ሰብሉ በበሽታ እና በተባይ ከተያዘ ጉዳቱን ለመቀነስ ከግብርና ባለሙያ ጋር በመነጋገር የመፍትሔ መንገዶችን መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አረምን በባሕላዊ መንገድ (በእጅ ማረም) ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ምክረ ሐሳባቸውን ያቀረቡት ባለሙያው ነገር ግን የሰው ኃይል እጥረት ሲገጥም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አረምን በፀረ አረም ኬሚካል ርጭት ማስወገድ የመጨረሻ አማራጭ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

መረጃ

ጥምር ግብርና ምንድን ነው?
ጥምር ግብርና ማለት በአንድ ማሳ ላይ የተለያዩ የአትክልት ዝርያዎችን ከሰብል ጋር አሰባጥሮ በመትከል የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ነው። የጥምር ግብርና ዋነኛ ጥቅሙም የተለያዩ ምርቶችን በአንድ ቦታ ከማምረት ባሻገር አንዱ አትከልት ወይም ሰብል ቢጠፋ /ቢደርቅ/ ሌላው ሊለማ ስለሚችል አማራጭ መንገድ ነው፡፡ በክልላችን በስፋት ቅመማ ቅመም በጥምር ግብርና እየተመረተ ይገኛል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here