ወቅቶች በሥነ ምግባር ለውጥ

0
155

ሰዎች የስነ ምግባር (የሞራል) እሴቶችን የማክበር እና የመፈፀም ደረጃቸው ከወቅቶች እና ከዓየር ንብረት ሁነት ጋር ሊለዋወጥ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ  ለንባብ አብቅቶታል፡፡

የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከሩብ ሚሊዬን የሚበልጡ ሰዎችን በመጠይቅ አሳትፈው ውጤቱን ተንትነዋል፡፡ በዚሁ የትንታኔ ማጠቃለያቸው የሞራል እሴቶች አፈፃፀም እና ድጋፍ ከበጋ እና ከክረምት የበለጠ  በፀደይ እና በመፀው ወቅቶች ጠንከር ብለው መታየታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ለዚህም የወቅቶች ግርዶሽ ወይም መጨናነቅ ለለውጡ ምክንያት መሆኑን ነው ያሰፈሩት – ተመራማሪዎቹ፡፡

ተመራማሪዎቹ ለ”ሞራል” ወይም ስነ ምግባር ወይም በጐ የመስራት፣ የማሰብ ሁነት – ታዛዥነት፣ ሀላፊነት፣ ገለልተኝነት፣ ነፃ መሆን፣ እንክብካቤ እና ፍትሀዊነት በእሴትነት መካተታቸውን አብራርተዋል፡፡

የጥናት ቡድኑ ለአስር ዓመታት በተከታታይ መረጃ መሰብሰቡ የተጠቆመ ሲሆን  በበጋ እና በክረምት የተሰጡ ምላሾች በእጅጉ ለሞራል እሴቶች የቀነሱ ሆነው መስተዋላቸው ነው የተሰመረበት፡፡ የመልካምድራዊ አቀማመጥ ልዩነት ሳይኖር በተመሣሣይ ቀጣናም የዓየር ንብረት መለዋወጥ በእሴቶች ላይ ያለን አመለካከት ሊያራርቀው እንደሚችል ነው የተጠቆመው –  በአጥኚዎቹ፡፡

አጥኚዎቹ በወቅታዊ የሞራል ለውጦች እና በጭንቀት ደረጃዎች መካከል ግንኙነት ያለ መሆኑን የሚጠቁሙ እውነታዎችን ከተሰበሰበው መረጃ ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ በሰጡት ማብራሪያ በአንድ ቀጠና ወይም ክልል አንድን ተግባር መከወን ሲታሰብ የወቅቶቹን ሁኔታ ታሳቢ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥተው  የገለጹት።

ለአብነት ባለፈው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የተከሰተውን የቡድን ኃላፊነት፣ ታማኝነትን አለማክበር እና መዘናጋት ያስከተለውን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በአብነት አንስተዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here