“ችግሮቻችንን በራሳችን እንፍታ::” አቶ አበረ ምህረቴ (የክብር ዶክተር)

0
170

ሰላም ለበኩር የእንግዳችን አምድ አንባቢያን በዛሬው እትማችን የጤና ልማት እና ፀረ ወባ ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ አበረ ምህረቴ ጋር ቆይታ እናደርጋለን፡፡ በሰሩት ታላላቅ ስራ የክብር ዶክተር ማእረግ የተቀብለዋል፡፡ አቶ አበረ ምህረቴ በፈረንሳይኛ ቋንቋ መምህርነት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው፣ የሰባ ዓመት እድሜ ባለፀጋ ሲሆኑ፣ የሁለት ልጆች አባት ናቸው። ትውልዳቸው በምስራቅ በጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ የኑሪ በምትባል ቀበሌ ነው፡፡ የስድስት ወር ጨቅላ እንዳሉ ወደ ደብረ ማርቆስ መጡ፡፡ ከዚያም እስከ 12ኛ ክፍል በደብረ ማርቆስ፣ በሞጣ፣ በፍኖተሰላም ከተሞች ተምረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ 1965 . እስከ 1966 . የፈረንሳይ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ውስጥ ፈረንሳይኛ ለማስተማር እና አማርኛ በሁለተኛ ደረጃ ለማስተማር ተመዝግበው ተምረዋል::

ስራ የጀመሩት የፈረንሳይ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ነው፡፡ ከዚያም በአሊያንስ ፍራንሴዝ (Alliance Française) 12 ዓመት፣ በጣልያን ትምህርት ቤት 5 ዓመት ፈረንሳይኛ አስተምረዋል:: ለበርካታ ዓመታት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ውስጥ ሰራተኞችን ፈረንሳይኛ አስተምረዋል:: የጤና ልማት እና ፀረ ወባ ማህበር መስራች እና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማህበሩ በሚሰራቸው የልማት ስራዎች ዙሪያ ከበኩር ጋዜጣ ዝግት ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ፀረወባ እና ጤና ልማት ማህበርን ለማቋቋም ያነሳሳቸው ዋና ምክንያት ምን ይሆን?

ለዚህ ያነሳሳኝ… ሁልጊዜ አእምሮአችንን የሚኮረኩር፣ አእምሮአችንን የሚያስጨንቅ ወሬዎችን እንሰማ ነበር አዲስ አበባ ሆነን፡፡ ሰው ሞተ በምን ምክንያት ሞተ? በወባ፤ ስንት ሰው ሞተ ሲባል ግን በጣም የሚያሳዝን ቁጥር ነበር የምንሰማው፡፡ የእገሌ ዘመድ ሞተበት ተብሎ ለቅሶ ይቀመጣል እንሄዳለን፤ ስንሄድ ብዙ ሰው  ሞቶ ነው የምናገኘው፡፡

በኋላ ላይ ግን የምሰማው ነገር ዘገነነኝ እና ምንድነው የሰማሁት? በቀን የወጣው ሰው በየቤተክርስቲያኑ የቀብር ሰዓት አለቀ ተብሎ ቤተክርስቲያን ሲዘጋ ብቻ ነው ወደ ቤት የሚመለሰው የሚል በየቦታው እንደዚህ አይነት ወሬዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ ምስክርነት የሚሆኑ ደግሞ አቶ አያሌው መለሰ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡  እሳቸው ደምበጫ ዘመድ ሞቶባቸው ሄደው አንድ ወር ሙሉ ከቤት ጠዋት ይወጣሉ ቤተክርስቲያን ዝግ ሲሆን ይመለሳሉ፡፡ እና ለምን ጥለው መጡ ብዬ ስጠይቃቸው የወሩ መጨረሻ እለት ዝም ብዬ ወጥቼ የመጣሁት አንድ ሰው የቀብር ሰዓት እንዳያልፍበት አፈር ወይም ጠጠር በምናመላልስበት ጋሪ አስከሬን ጥቅል አድርጎ አስሮ  አስሮ ጭኖ ብቻውን እየገፋ ሲመጣ ሳይ ያ ለእኔ ሰቀጠጠኝ እናም ደብረ ማርቆስ አድሬ መጣሁ ሲለኝ… ምን ልበልህ? ተፈርዶበት እንጂ እውነት መንግሥት ያለበት አይመስልም፡፡ የጤና ባለሙያ ባለበት አካባቢ፣ እና በህክምና በሚድን በሽታ እንደዚህ አይነት አሟሟት ሰው ሲሞት ለእኔ ዘገነነኝ፡፡ ትክክል እንዳልነበረ ነው የገባኝ:: እና ምክንያቱም አልገባኝም እና መንግስት ላይ ከፍተኛ የሆነ የጭቃ ጅራፌን ማውረድ ጀመርኩ፡፡ መንግሥት  ምንም አላደረገም በሚል፡፡ ሆን ብሎ ነው የሚልም እምነት እንዲያድርብኝ አድርጎኝ ነበር፡፡  እናም ከባለቤቴ ጋራ ስነጋገር… “አንተ ራስህ ለህዝብ ምን አድርገሃል?” አለችኝ:: እና እኔ እንዲህ ማለቷ ሰቀጠጠኝ፡፡ እናም እስኪ ድገሚው አልኳት፤ ደገመችው፡፡ እኔ ለህዝብ ያደረኩት ሙሉ እድገት በህብረት ዘማች ስለነበርኩ በዚያ በጣም በፍቅር ዘምቼ ብዙ ስራ ብሰራም ተደናቅፎ የቀረ ስራ ነበረኝ እና ብልጭ ያለብኝ እሱ ነው፡፡ በሕዝብ በጣም ተወዳጅ ሆኜ በሕዝቡ በኩል በገበሬው በኩል ብዙ ስራ የሰራሁበት ወቅት ትዝ አለኝ እና “በቃ እንደዛ ማድረግ እችላለሁ” የሚል መጣብኝ:: ወዲያውኑ የማውቃቸውን እና ዘመዶቼን እየደወልኩ እሁድ አራት ሰዓት ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን እንገናኝ እና አንድ ነገር ማድረግ አለብን ብዬ ጥሪ አደረግሁ፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ እየተሰባሰብን የመሰረትነው ማህበር ነው፡፡

በዚያ ወቅት ወባ እንደዚህ ሰውን እስከመጨረስ ያደረሰው ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልታወቀም ነበር?

ይታወቃል ግን ምንድነው ቢባል- አንድ በመንግሥት በኩል የነበረው የአወቃቀር ሁኔታ፣ ሁለት በመንግሥት ተይዞ የነበረው የመድኃኒት ፖሊሲ፣ ሦስት የአየር ንብረት ለውጥ መኖሩ፡፡ እነዚህ በህብረተሰቡ ዘንድ የታወቁ አልነበሩም፡፡ በመንግሥትም  ፈጥኖ የሚወሰዱ እርምጃዎች አልነበሩም፡፡ ህብረተሰቡ ደግሞ ወባ ማለት የበረሃ በሽታ ነው “ይሄ ጠንቋይ ነው፣ ውቃቤ ነው፣ ዛር ነው፣ የቤት ጣጣ ነው” የሚል አይነት አጉል እምነቶች የባዕድ አምልኮ እንዲስፋፋ አደረገ፡፡ እውነቱ ይሄ ነው እኛን አላስቀምጥ ያለን እና እርምጃ መውሰድ አለብን ብለን የተነሳነውም ለዚህ ነው፡፡

እንግዲህ ከተቋቋማችሁ በኋላ ምንድነው የወሰዳችኋቸው እርምጃዎች? ምን ስራዎችን ነው ያከናወናችሁ?

አዎ! እንግዲህ መጀመሪያ ተሰባስበን ምን ማድረግ እንዳለብን ጥናቶችን አጠናን፡፡ ቅድም እንዳልኩት ችግሮቹን ነቅሰን አወጣናቸው:: ለዚህ መፍትሄው ህብረተሰቡን ማስተማር የመጀመሪያው ሆኖ እያለ፣ ከዚያ በፊት ግን ለማስተማር እንዲረዳ ህብረተሰቡ መዳን አለበት:: የታመመው መዳን አለበት፡፡ እና አድኖ ማሳየት አለብን:: አድኖ ለማሳየት ትክክለኛ መድሃኒት ይዘን መቅረብ አለብን:: ይሄን መድሃኒት ይዘን ለመቅረብ ገንዘብ ያስፈልገናል፡፡ ገንዘብ ካስፈለገን ደግሞ ማህበር ያስፈልገናል፡፡ ማህበር ደግሞ ከተቋቋመ በኋላ ሕጋዊ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ማህበር ለማቋቋም ወሰንን። እናም ሕጋዊ አደረግነው፣ ገንዘብ አሰባሰብን፣ መድሃኒት ከመንግሥት ካዝና ገዛን፤ ባለሙያችን አደራጀን፤ በተጓዳኝ ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ እየሄድን ቅስቀሳ ማካሄድ ጀመርን፡፡ ከመንግሥት ጋር ውይይት አደረግን፡፡ በየወረዳው እና በየከተማው በየቀበሌው ኮሚቴዎች በማዋቀር ትምህርት ለማዳረስ እንደምንፈልግ አስታወቅን:: ስለዚህ ለዚህ ያግዛሉ ያልናቸውንም በራሪ ጽሁፎች፣ የኪስ ማስታወሻዎች በብዛት አሳትመን፡፡ የባለሙያም ችግር አለባቸው ባልናቸው ቦታዎች ላይ ባለሙያዎችን አሰማራን፡፡ ገበያ ላይ ሳይቀር ገብተው ህክምና ሰጡ፡፡ ያ እንግዲህ ይዘነው የሄድነው “ፋንሲደር” (Fansidar) የሚባል ፋልሲፈረም ለተባለው የወባ በሽታ ፈውስ ይሰጣል ብለን የገዛነው መድሃኒት ነበረ እንደአልነውም ሆነ፡፡ ያ ህብረተሰቡን ወዲያውኑ እንዲቀበል እና ውጤታማ እንዲሆን በመንግሥትም በህዝብም በኩል አስተዋጽኦ አደረገ:: ከዚያ በየጤና ጣቢያው፣ በየሆስፒታሉ የተደረጉት ርብርቦች ወዲያውኑ ከፍተኛ ውጤት አስመዘገቡ፡፡ ስለሆነም ትምህርት ቤቶችን፣ የግብርና ባለሙያዎችን፣ እድሮችን፣ የሴት ማህበራትን፣ የወጣቶች ማህበራትን በመጠቀም ትምህርቱ በሰፊው እንዲዳረስ የማድረግ ስራ ሰራን:: ይህን ነው እንግዲህ ውጤታማ እንድንሆን ያደረገን፡፡ ህዝቡንም በማዳን የተጫወተው ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ በ920 ቀበሌዎች፣ በ29 ወረዳዎች በኋላ 31 ሆኖ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኮሚቴዎች አዋቅረን 77 አባላት ያሉት የበጎ ፈቃደኛ ኮሚቴ አዋቅረን ትምህርቱ በተከታታይ እንዲሰጥ አደረግን:: እርምጃችን ይሄን ይመስላል::

ማህበሩ በወባ ላይ ባከናዎናቸው የተለያዩ ተግባራት ውጤታማ ነበረ ማለት እንችላለን? ውጤቱን እንዴት እንገልጸዋለን?

ውጤቱ እንዴት ይገለጻል ብትለኝ እነርሱ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ቢገልጹት፡፡ ምክንያቱም ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎች ሲገልጹት ነው ደስ የሚለው፡፡ ወይም ደግሞ የመንግስት አካላት የማህበሩን አስተዋጽኦ የሚገልጹበት መንገድ ሲሰማ ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ አያሌው ጎበዜ ፕሬዝዳንት እያሉ እሳቸው በሰጡት አስተያየት “አይናችንን የገለጸልን ይሄ ማህበር ነው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን ተጨንቀን በነበረበት ወቅት ህብረተሰቡን ያማከለ ጤና ትምህርት በመስጠት ወባን መከላከል ይቻላል ብሎ የመጣ ነው” ብለዋል፡፡ በጤና ባለሙያዎች በኩል ብትሄድ እንደ ዶክተር ዳንኤል ያሉ በወቅቱ የነበሩት የጤና ቢሮ ሃላፊ “አዎ እኛንም በጣም እንድንንቀሳቀስ አድርጎ ተሳትፏችንንም ይበልጥ እንዲሆንና እንቅስቃሴያችን የጠነከረ እንዲሆን ይሄ ማህበር አስተምሮናል” ብለውን ነበር፡፡ ወደታች ወረድ ስትል ደግሞ ብዙ ምስክሮችን ስትሰማ ውጤታማ ነበር ለማለት ትደፍራለህ። እንደዚሁም በሌሎችም የገጠር አካባቢዎች “እንዴ ፀረ-ወባ ማህበር የነፍስ አባታችን ነው” የሚሉም የዳኑ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ይሄን ይሄን ስታይ አዎ ውጤታማ ነበረ የሚል መደምደሚያ ላይ ትደርሳለህ፡፡

እንዲህ ያለ ማህበር አቋቁመው እዚህ በማድረስዎ በግልዎ ምን ይሰማዎታል?

ኩራት፤ በጣም እኮራለሁ ደስ ይለኛል፡፡ እና ህዝብ ማዳን፣ እንዳይሞት መከላከል መቻል ቀላል ነገር አይደለም እ፡፡ አንድ ሀኪም እርግጠኛ ነኝ አንድ ሰው ሲያድን ምን ያህል እንደሚደሰት ሲሞትበት ምን ያህል እንደሚያዝን በጣም በትክክል እረዳዋለሁ፡፡ እኛ ደግሞ መድሃኒቱን ይዘን አስተባብረን መጥተን የደረስንበትን ደረጃ ሳየው በጣም ነው የምኮራው፡፡ በግሌ ብዙ ችግሮች ደርሰውብኛል፡፡ ግን በተቃራኒ የተሰራውን ስራ ስታይ ያ ሁሉ ርብርቦሽ ተደርጎ በእኔ እምነት ከ180 ሺህ በላይ ታሞ የነበረ ድኗል:: እና ይሄ በጣም ያኮራል፣ በጣም ደስ ይላል፣ ይኼ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እና ምን ይሰማሃል ብትለኝ ኩራት እና ኩራት ነው የሚሰማኝ ውስጤ ደስ ይለዋል- በጣም::

ከወባ ውጭ በምን በምን ነው እየተንቀሳቀሳችሁ ያላችሁት? አሁን ማህበሩን በማስፋት ረገድስ ያሉትን ስራዎችስ ማየት እንችላለን?

ይቻላል:: እንግዲህ ማህበሩ የተቋቋመው ፀረ-ወባ ማህበር በሚል ነው፡፡ መተዳደሪያ ደንባችንን ስናዘጋጅ ግን ወባ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ብለን ነበረ ያቋቋምነው፡፡ ስለዚህ የፀረ-ወባ ማህበር ሳቋቁመው ለኔ የመሰለኝ በቃ በክረምት ስራ የለኝም እና አስተዋጽኦ አድርጌ እመለሳለሁ የሚል ነበር፡፡ ማህበሩ ተቋቋመ፣ ያዝኩት “አንተ ምራው” ተባልኩ ተቀበልኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ወባ ላይ ያደረግናቸው ርብርቦች ነበሩ፡፡ በዚህ ውስጥ ግን አንዳንድ የምናያቸው ችግሮች ነበሩ፡፡ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ እና ወባ አቅምን የሚያሳጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ኤች.አይ.ቪ ችግር ያለበት ሰው ወባ እንዳይያዝ የበለጠ ትምህርቱን ማስፋት እንዳለብን ተረዳን፡፡ ይሄን ለማድረግ የተቀናጀ ትምህርት ማዘጋጀት እንዳለብን፣ ወባን ብቻ እያስተማርን ከምንመጣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስንም፣ የግል እና አካባቢ ንጽህናንም ብናቅፍ ብለን ይህንን ጨመርን፡፡ ከዚያ በኋላ ትኩረታችን በእነዚህ ሦስት ነገሮች ላይ መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ እና በዚያ መንገድ የማስፋፋት ስራዎችን ሰራን፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ማህበር ስራውና አላማው ዛሬ ወይም ርዕዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ይሄን እንዴት ያሳካዋል ካልከኝ? አባላትን በማፍራት ነው፡፡ ከእያንዳንዱ በገጠር አካባቢ ያለ የገጠር ነዋሪ በዓመት መቶ ብር ብቻ ነው የምንፈልገው፡፡ ከሌሎች ከተሞች ላይ ወደ አምስት መቶ ብር፡፡ ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር፡፡ ይሄ ዝቅተኛው ነው፡፡ በበጎ ፈቃደኝነት ከዚህ በላይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ የምንሰበስበው ገንዘብ ህብረተሰባችንን ሊጠቅም የሚችል ጉዳይ ላይ መዋል አለበት፡፡

የተጣበበ ሰዓትዎን አብቃቅተው ለሰጡን ቃለ ምልልስ በበኩር ጋዜጣ ዝግጅት ስም ግ አብዝተን እናመሰግናለን፡፡

 

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የታህሳስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here