ወይብላ ማርያም

0
99

ከደሴ 82 ኪ/ሜ ላይ በምትገኘው በወረኢሉ ወረዳ ልዬ ስሙ ቀርቀሬ 011 ቀበሌ ትገኛለች፡፡ በአጼ እስክንድር ዘመነ መንግስት ተመሰረተች፡፡ ቤተ-ክርስቲያኗም አጼ ልብነ ድንግል አንደኛዉን ቤተ-መንግስታቸዉን መካነ ስላሴ ላይ የሰሩ ሲሆን ሁለተኛዉን ቤተ-መንግስታቸዉን ወይብላ ማሪያም ላይ ሰርተዋል፡፡ ቦታው 2000 ሜትር ከፍታ ያለዉ በመሆኑ ከጠላት ለመከላከል ምቹ ቦታ ነዉ፡፡ በዚህም በአጼዉ ሊመረጥ ችሏል፡፡የቤተ-መንግስቱ ፍርስራሽ በቦታዉ ይገኛል፡፡ ስፍራዉ የተለያዩ ሀገር በቀል ወይራ፣ ጽድ፣ ግራርና ሌሎችም የሚገኙበት ሲሆን ከእንስሳት አንበሳ፣ ዘንዶ፣ ነብር፣ ጥንቸል፣ ጅብ፣ ቀበሮና ዝንጀሮ ይገኛሉ፡፡ ቤተ-ክርስቲያኑ በግራኝ ጉዳት ሲደርስባት ታቦተ ህጉ በስተምስራቅ 200 ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ይባላል፡፡ ግንቦት 21 ቀን ክብረ በዓሏ በደማቅ ይከበራል፡፡

 

ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በግራኝ አህመድ ከመቃጠሏና ከመውደሟ በፊት “ቀርቀሬ ማርያም” በሚል ስያሜ ትጠራ የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ጦር ሜዳ በሔዱ ጊዜ  ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗ እንደገና ታንፆ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡

 

የወይብላ ማርያም ገዳም በዐፄ እስክንድር ዘመነ መንግሥት በ1475 ዓ.ም የተገነባች ገዳም ናት። ዐፄ ዐፄ ናኦድ በዘመናቸው እየሄዱ ያስቀድሱባት እንደነበር የገዳሟ ታሪክ ዋቢ ነው። በ1500 ዓ.ም አባታቸውን የተኩት ዐፄ ልብነ ድንግል በበኩላቸውም አንደኛውን ቤተመንግሥታቸውን ያስገነቡበት ስፍራ መሆኑን አሁን ድረስ ያሉት ፍርስራሾች ያስረዳሉ።

 

በዘመኑ በተከሰተው የአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት ገዷሟ ጥቃት እንደሚደርስባት አስቀድመው የተረዱት ካህናት እና አባቶች ፅላቱን እና ሌሎች ንብረቶችን አሰባስበው በአቅራቢያ ከሚገኝ ገደል ውስጥ ባለ ዋሻ ደብቀው እንዳተረፉት ወረኢሉ ማህደረ ኢትዮጵያ በተሰኘ መፅሃፉ ከበር ጌታቸው ፅፏል። በወቅቱ ገዷሟ በአህመድ ግራኝ ወታደሮች ስትቃጠል ፅላቱ ወደ 200 ሜትር ርቀት ላይ ባለው ዋሻ ውስጥ ነበርም ይባላል።

በቀድሞ ስሟ ቀርቀሬ ማርያም ስትባል የነበረችው ገዳም በዘመኑ ወደ ጦር ዘመቻ እየሄዱ የነበሩ ወታደሮች “ያገሬ ታቦት ወይ በይኝ፣ ከዚህ ጦርነት በሰላም ከመለሺኝ ስመለስ ስዕለቴን አገባለሁ” ብለው በመሳላቸውና ሥዕለታቸውም በመድረሱ ሲመለሱ “ወይብላ ማርያም” በሚል ስያሜ እንደተጠራች ይነገራል፡፡

 

ወይብላ ማርያም በአህመድ ግራኝ ከተቃጠለች በኋላ እስከ 1990ዎቹ ድረስ ምንም ቤተክርስቲያን ሳይሰራበት ለዘመናት ቆይቷል። ዳግም ለመገንባቷ ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ሸህ ሀሰን ይመር ግንባር ቀደም ናቸው። ሸህ ሁሴን ይመር ከወይብላ ማርያም ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሲሆን ታሪክ ከአያታቸው ይጀምራል። ሸህ ሀሰን ይመር ከአባታቸው የተላለፈ አደራ ነበራቸው።

ይህም “ወይብላ ማርያም ላይ ገና ብዙ ተዓምር ይሰራል  ወደ ፊት ስሟ እጅግ ይገንናል። መኪና ይገባል፣ በርካታ ህዝብ ይመጣል፣ ይህን እኔ አልደርስበትም በእናንተ ጊዜ የሚሆን ነው እና አደራ በክብር ጠብቃችሁ ጊዜው ሲደርስ እና እመቤቴ ስትፈቅድላችሁ ለራሳችሁ ለክርስቲያኖቹ ታሳውቁና እነሱ ራሳቸው ቤቧተክርስቲያን ይቆማል እናንተ ጭምር ትጠቀማላችሁ…” በማለት ከ60 በላይ ዓመት በፊት እንደነገራቸው ሸህ ሀሰን ይመር እናዳጫወቱት ከበር ጌታቸው ፅፎታል።

 

ከአያት ቅድመ አታቸው ጀምሮ በርካታ ተዓምራትን ታደርግላቸው ስለነበር እነ ሸህ  ሀሰን ወይብላ ማርያምን ዓመቷን እየጠበቁ መዘከር ግድ አላቸው። ምንም ቤተክርስቲያን ሳይኖር ነጭ ጊደር ወይም የል አርደው፣ ዳቦ ጋግረው ፣ ጠላ  ጠምቀው ግንቦት 21 ሲዘክሩ ቆይተዋል።

ወይብላ ማርያም ለእነሸህ አሰን እና መሰሎቻቸው ትልቅ ዋጋ ያላት ናት። ግንቦት 21 በየዓመቱ የወይብላ ማርያም በዓልን በየአመቱ እንደ ክርስቲያኖች ያከብሯታል።

 

ሸህ ሁሴን ማርያም አዝዛኛለች በሚል ቤተክርስቲያን ቦታው ላይ እንዲገነባ ወደ ወረዳው ቤተ ክህነት በመሄድ አቤቱታ አቅርበው ታሪኳን በዝርዝር ያስረዳሉ። በወቅቱ የነበረው ቤተክህነትም አቱታውን ተቀብሎ ከወረዳው አመራሮች ጋር በመሆን ወደ ተራራው በመውጣት ቦታውን አይተው ቅድመ ታሪኩን አጣርተው ሸህ ሀሰን ይመር የሰጡትን ምስክርነት አዳምጠው በ1990 ዓ.ም ምህረት ቦታው እንዲካለል መደረጉን የ’ወረኢሉ ማህደረ ኢትዮጵያ ‘ መፅሀፍ ፀሀፊ ተርኮታል።

 

አቶ ከበር እንደፃፈው ሸህ ሁሴሷን በዚህ አላቆሙም፣ ወደ ደቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድ አግኝተው በ2000 ዓ.ም የመጀመሪያዋን መቃኛ ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር ሆነው አሰርተው የወይብላ ቅድስት ድንግል ማሪያም ገዳም በይፋ የህዝበ ክርስቲያ መገልገያ ቅዱስ ቦታ ሆና እንድትቀጥል ተደረገ።

 

እንዲህ ባለው የሙስሊሙ እና ክርስቲያኑ አብሮነት፣አንድነት የሁለቱን ታላላቅ እምነቶች የዘመናት ፍቅር በውል የታየበት ማረጋገጫ ሆኖ ተመዝግቧል። ወይብላ ማርያምም የኢትዮጵያ የባህል እና የታሪክ ማህደር ሆና ቀጥላለች።

በነገራችን ላይ ወይብላ ማርያም የተባሉ ቤተክርስቲያኖች ሰቆጣ፣ ደብረታቦር እና በሌሏሎች አካባቢዎችም እንደሚገኙ ስናነብ ተረድተናል።

 

ምንጭ- የደቡብ ወሎ ኮምኒኬሽን፣ ወረኢሉ ማህደረ ኢትዮጵያ  በከበር ጌታቸው።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የግንቦት 25  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here