የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ በርካታ የንብ ዝርያዎች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አናቢዎች ቢኖሩም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ:: ባለሙያዎችም በሀገሪቱ ማርን በብዛት እና በጥራት ለማምረት የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ በበቂ ሁኔታ መቋቋም እንዳለበት፣ እፅዋቶችን በዓይነት እና በብዛት መትከል፣ የንቦችን ጤንነት መጠበቅ፣ አመራረቱን ዘመናዊ ማድረግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂን ማቅረብ እና ማላመድ፣ አሠራሮችን ማዘመን እና የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ምክረ ሐሳቦችን ያቀርባሉ::
የንብ እርባታ ሥራ ብዙ መሬትን እና በርካታ ጉልበትን የማይጠይቅ፣ በአነስተኛ መነሻ ካፒታል (ገንዘብ) ማልማት የሚቻል ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያስገኝ መሆኑን በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ያብራራሉ:: ንቦች ከአበባ ቀስመው የሚያዘጋጁት ማር ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ለመድኃኒትነት ይጠቀሙበታል:: ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ ገበያ በመላክ ምንዛሬ በማስገኘት ለምጣኔ ሀብቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል::
ንብ ለተለያዩ በሽታዎች ለመድኃኒትነት የሚጠቅመውን፣ ለምግብነት የሚውለውን፣ ማዓዛው እና ጥፍጥናው ወደር የሌለውን ማር ማዘጋጀቷ ድንቅ አድርጓታል:: የሲ ኤን ኤን ዘገባ እንዳመላከተው የዓለምን የምግብ ፍላጎት ከሚሸፍኑ 1ሺህ አይነት ምግቦች መካከል 71ዱ የተፈጠሩት በንቦች አማካኝነት ነው:: እንዲሁም የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያዎችን የማዳቀል ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነም ተመላክቷል::
ዘገባው አክሎም ንቦች በሺዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን ተሻግረው ይቀስማሉ፣ አንዱን ከአንዱ ያዳቅላሉ- ያራባሉ::
ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 550 ሺህ ቶን ማር የማምረት አቅም እንዳላት ይነገርላታል:: ይሁንና በኢትዮጵያ እየተመረተ ያለው የማር መጠን ሀገሪቱ አላት ከሚባለው አቅም ከዘጠኝ በመቶ እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ::
በኢትዮጵያ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ ህብር ንብ (የንብ መንጋ) ብዛት እንዳለ በ2010 ዓ.ም የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት (CSA) ይዞት የወጣው መረጃ ያሳያል:: በሀገሪቱ ለንብ ማነብ ተስማሚ ከሆኑት ክፍሎች ደግሞ የአማራ ክልል አንዱ ነው:: የማዕከላዊ ስታስቲክስ በ2016 ዓ.ም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን 742 ሺህ 703 ህብር ንብ (የንብ መንጋ) ይገኛል:: ይህም ከሀገሪቱ ጥቅል የህብር ንብ ብዛት 20 በመቶ ድርሻ አለው::
ክልሉ ለንብ ሀብት ልማት ሥራ አመቺ የሆነ የአየር ፀባይ፣ የመሬት አቀማመጥ እና የተለያዩ የቀሰም እፅዋቶች ያሉበት ምቹ አካባቢ እንደሆነ ይነገርለታል:: በክልሉ ከአራት ሺህ በላይ በተለያዩ ወቅቶች የሚያብቡ የእፅዋት ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 800 የሚሆኑት የማር እፅዋቶች በምርምር የተለዩ መሆናቸውን የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል::
ጥራት ያለው ማር ለማምረት ቆላ እና ወይና ደጋ የአየር ንብረት የበለጠ ተመራጭ ሲሆን 72 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሥነ ምህዳር ደግሞ ቆላ እና ወይና ደጋ መሆኑ ለንብ እርባታ አመቺ መሆኑን ያሳያል:: የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የንብና የሀር ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙሐመድ ጌታሁን ለበኩር ጋዜጣ በሰጡት ማብራሪያ ክልሉ ለንብ ሀብት ልማት ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው እና በርካታ የቀሰም እፅዋቶች የሚገኝበት ነው::
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በ492 ሺህ 800 አናቢ የቤተሰብ ኃላፊዎች፤ በፍሬም ቀፎ 156 ሺህ 846፣ በሽግግር ቀፎ 81 ሺህ 961 እና በባህላዊ ቀፎ አንድ ሚሊዮን 503 ሺህ 896 የንብ መንጋ እንዳለ አብራርተዋል:: በአማራ ክልል በ2015 ዓ.ም 22 ሺህ 54 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 29 ሺህ 333 የተመረተ ሲሆን በ2016 ዓ.ም ደግሞ 30 ሺህ 133 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 22 ሺህ 714 ቶን ማር ተመርቷል:: በተመሳሳይ በ2017 ዓ.ም 31 ሺህ 531 ቶን ማር ለማምረት ታቅዷል:: ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 10 ሺህ 500 ቶን ማር መመረቱን ባለሙያው ተናግረዋል::
ንቦች ለሰብል ምርት እድገት እና ለተፈጥሮ ሀብት ልማት ያላቸው ሚና የላቀ ነው ብለዋል:: ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተግባር በእፅዋት ተራክቦ ሂደት ለከፍተኛ የእፅዋት ዘር ምርት ጭማሪ ያመጣሉ:: በኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ንቦች የሚናቡት ለማር እና ለሰም ምርት ብቻ ተብሎ ነው:: እጅግ በጣም ወሳኝ የሆነው የንቦች ፋይዳ ግን ንቦች በእፅዋት ብዜት ሥርዓት ውስጥ የሚጫወቱት አስደናቂ ሚና ነው:: ይኸውም ንቦች አበባ በሚቀስሙበት ወቅት በሚያካሂዱት የርክበ ብናኝ ተግባራቸው እፅዋቶች ከማንኛውም ቴክኖሎጂ በላይ በብቃት እንዲባዙና ዓለም በአረንጓዴ ተክሎች እንድትሸፈን የማድረግ አቅም አላቸው::
በኢትዮጵያ በተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት መሠረት ንቦች ሰብሎችን በማዳቀል በርክበ ብናኝ እፅዋትን የማዳቀል ተግባር በማፋጠን የሰብሎችን ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ::
ለአብነትም በኢትዮጵያ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ከሆኑት ሰብሎች መካከል አንዱ በሆነው ሰሊጥ ላይ ከ45 እስከ 60 በመቶ፣ በኑግ ሰብል ላይ ከ33 እስከ 66 በመቶ እንዲሁም የስንዴን ምርት ከ50 እስከ 65 በመቶ የሚደርስ የምርት ጭማሪ እንደሚያስገኝ በ2010 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል::
ሆኖም የንቦች መኖር ለሰብል ምርት እድገት የሚያመጣውን ፋይዳ በአግባቡ ተረድቶ የመሥራት ክፍተቶች መኖራቸውን ባለሙያው ያብራራሉ:: ዓለም ንቦችን የሚያንበው በዋነኝነት በሰብል ምርታማነት ላይ በሚጫወቱት ከፍተኛ ሚና ቢሆንም በኢትዮጵያ ግን ይህ ዋነኛ የንቦች ፋይዳ በውል አይታወቅም፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች ለንብ አናቢዎች ግንዛቤ በመፍጠር እና በማስተማር ረገድ ክፍተት በመኖሩ የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በርካታ የህብረ ንቦችን እያጠፋ እንደሚገኝም ተናግረዋል:: በአማራ ክልል ልቅ በሆነ የፀረ አረም እና ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት በዓመት 11,520,000 ብር ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ እየደረሰ መሆኑን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2010 ዓ.ም ባደረገው ጥናት አረጋግጧል:: በንብ ማነብ የሚተዳደሩት አቶ ለጋስ በጥናቱ የተቀመጠውን ሐሳብ የሚያጠናክሩ ግለሰብ ናቸው::
ንብ አናቢው አቶ ለጋስ ቸኮለ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ድሃና ወረዳ ቀበሌ 023 ነዋሪ ናቸው:: የንብ እርባታው እና የማር ምርቱ እንደ ቀደምቱ ባይሆንም አሁንም በዚሁ ዘርፍ እየተዳደሩ ነው:: የእርሻ እና የንብ ማነቢያ ቦታ ባለመለየቱ ለሰብል የሚረጨው ፀረ አረም ኬሚካል በንቦች ቁጥር ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረ ተናግረዋል:: በዚህ ምክንያትም የንቦች ህልዉና እየተመናመነ የማር ምርታቸው በየጊዜው እየቀነሰ መምጣቱን ያስረዳሉ:: በአካባቢው ያሉ ለንቦች የሚያገለግሉ እፅዋቶች መመናመንም ሌላ ተፅዕኖ መፍጠሩን ያስረዳሉ::
በመሆኑም አስፈላጊ እፅዋቶችን መትከል እና መንከባከብ ይገባል ብለዋል:: ካሁን በፊት 25 የሚደርሱ የንብ ቀፎዎች እንደነበሯቸው በስልክ ነግረውናል:: ከዚህም እስከ 150 ኪሎ ግራም ማር አምርተው ለገበያ ያቀርቡ እንደነበር አጫውተውናል:: ከማር ምርት በተጓዳኝ የሰም ምርት በማምረት ገቢ ያገኙ እንደነበር ተናግረዋል:: በሚያገኙት ገቢም ልጆቻቸውን ያስተምራሉ:: ከዓመት ዓመት ግን እየቀነሰ መጥቷል ይላሉ:: በዚህ ዓመት 50 ኪሎ ግራም ማር አገኛለሁ የሚል ተስፋም አላቸው::
ንብ የማነብ ቦታ ሲወሰን ለንብ ቀሰምነት ጠቃሚ የሆኑ በተለያዩ ወቅቶች የሚያብቡ እፅዋቶች በአካባቢው መኖር ወይም ማልማት፣ ንፁህ ውኃ በማነቢያ ስፍራ ማቅረብ፣ መሬቱ ረግረጋማ ያልሆነ፣ በጎርፍ የማይጠቃ፣ ቆሻሻ ከሚጠራቀምበት ቦታ እና ከመኖሪያ አካባቢ የራቀ፣ ኬሚካል ከሚያተንኑ (ከሚለቁ) ፋብሪካዎች የራቀ፣ ተደጋጋሚ የፀረ-ተባይ ኬሚካል ርጭት በብዛት የማይካሄድበት አካባቢ መሆን እንዳለበት ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በመሆኑም ለንቦች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ አርሶ አደሩም ሆነ ባለሙያው በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅበት፤ የራስንም ሆነ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ለማሳደግ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ነው ያደማደሙት::
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም