የሰሜኑ ጦርነት ዳፋውን በቀጥታ ካሳረፈባቸው ክልሎች መካከል የአማራ ክልል ይገኝበታል፡፡ በሁለት ዓመቱ ጦርነት በክልሉ ማኅበራዊ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ምጣኔ ሐብታዊ እንቅስቃሴዉ ተቀዛቅዟል፡፡ በገንዘብ ከሚተመነው ሰብዓዊ ጉዳት ውጪ አጠቃላይ የጉዳት መጠኑ 522 ሚሊዮን ብር እንደነበርም የክልሉ መልሶ መቋቋም ፈንድ ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል፡፡
የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰሜኑ ጦርነት ማብቂያ እንዲሆን ምክንያት ቢሆንም ግጭቶች ግን ከ2015 ዓ.ም ጀምረው እንደ አዲስ አገርሽተዋል፡፡ የአማራ ክልልም ጦርነቱ መቋጫውን ካገኘበት 2014 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ (ከሐምሌ 2015 ዓ.ም መጨረሻ) እንደ አዲስ በክልሉ ውስጥ ያገረሸው በትጥቅ የታገዘ ግጭት ክልሉን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል፡፡ የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ ውስጣዊ ግጭቶች እና በሌሎች ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት በክልሉ ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለመመለስ ከ102 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ መንግሥት የካቲት 20 ቀን 2017 ዓ.ም የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ምክክር ባደረገበት ወቅት አስታውቋል፡፡
ሦስተኛ ዓመትን እንዳይሻገር የሚሰጋው የሰላም መናጋት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ አርሶ አደሩ በስፋት አምርቶ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት አንዱ ምክንያት ለሆነው የምርት አቅርቦት ችግር መፍትሄ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ የጸጥታ ችግሩ አርሶ አደሩ ያመረተውን ወደ ገበያ እንዳያቀርብ፤ ግብዓት ገዝቶ በተጠቀመበት ልክ የተሻለ የምርት ዋጋ ባለማግኘቱ ምክንያት ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች በጊዜ ሂደት ምርታማነት እንዲቀንስ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስለሚታመን አርሶ አደሩ የሰላም ያለህ!? ሲል እንዲከርም አድርጎታል፡፡
በተለያዩ የሰላም የውይይት መድረኮች እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው መማር ማስተማሩ በእጅጉ ተስተጓጉሏል፡፡
በእነዚህ ሁለት ዓመታት መምህራን ነጻነት አግኝተው ትውልድ የመቅረጽ ሥራቸውን በሚፈለገው ልክ አላከናወኑም፡፡ በክረምት ወቅት የሚከናወኑ የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት እና የትምህርት ቤት የገጽታ ግንባታ ሥራዎች እንዲዘነጉ አድርጓል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተምረው ቀጣዩን የክፍል ደረጃ መድረስ የነበረባቸው ከስድስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፡፡
የጤና አገልግሎት አሰጣጡ ተፈትኗል፤ እንደ ኮሌራ እና ወባ ያሉ የማኅበረሰብ የጤና ችግሮችን ለመቆጣጠር የጸጥታ መታወኩ በፈተናነት መነሳቱም የሚታወስ ነው፡፡ የሰላም ችግሩ ማኅበራዊ እንቅስቃሴን መገደቡን ተከትሎ ማኅበራዊ መስተጋብሩ ላልቶ ቆይቷል፤ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ ይስተዋላል፡፡
የአማራ ሕዝብ ነባር እሴቶች ተሸርሽረዋል:: ቀድመው ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶች በወቅቱ እንዳይጠናቀቁ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይጀመሩ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡ የክልሉ መንግሥት ግን በየጊዜው የሚገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የልማት ሥራዎችን ጀምሮ እያጠናቀቀ ነው፡፡ ከብዙ የልማት ሥራዎች መካከል የኮሪደር ልማቱ ተጠቃሽ ነው፡፡
ምንም እንኳ የክልሉ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል እየተባለ ባለበት በአሁኑ ወቅትም ስለ ሰላም ውይይቶች እና ምክክሮች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ምከንያቱ ደግሞ የሰላም ሁኔታው የክልሉን ሕዝብ በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ የመሥራት እና ሐብት የማፍራት እንቅስቃሴ ከስጋት ነጻ ማድረግ ቀዳሚው ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ባደረገው ጉባኤ ወቅት ለክልሉ ከግጭት አዙሪት የመውጫ መንገዱ ውይይት እና ድርድር መሆኑን አቅጣጫ በማስቀመጥ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ሁለት መፍትሄዎች ብቸኛ አማራጭ ሆነው ይሰራባቸዋል መባሉም ይታወሳል፡፡ የሰላም ካውንስል ተቋቁሞ እስከ አፍሪካ ሕብረት ድረስ የደረሰ የሰላም መንገድ ፍለጋ ተካሂዷል፡፡ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተጠናክሮ የቀጠለው የሕግ ማስከበር ሥራ ክልሉን ወደተሻለ የሰላም መንገድ እንደመሩት የክልሉ መንግሥት ተደጋጋሚ መግለጫዎች ያረጋግጣሉ፡፡
የክልሉ መንግሥት ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ ሰላማዊ ጥሪዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ የታጠቁ ኀይሎች ሰላማዊ አማራጭን ተቀብለው ወደመደበኛ ኑሯቸው መግባታቸውን የክልሉ መንግሥት በተደጋጋሚ ያስታውቃል፡፡
በየጊዜው እየተሻሻለ የመጣው ሰላም ዳግም እንዳይታወክ የጸጥታ መዋቅሩን ከማጠናከር ጀምሮ ሕዝቡ የሰላም ባለቤት ሆኖ እንዲቆም የሚያደርጉ ውይይቶች ሲደረጉ ከርመዋል፡፡ ሰላማዊ አማራጭን የተቀበሉ የታጠቁ ኀይሎችም ሕዝብ ከዚህ በላይ መጎዳት የለበትም ብለው ከጥፋት መንገድ እንደተመለሱ ተናግረዋል፡፡
አሁንም ክልሉን ወደቀደመ የሰላም ሁኔታው ከመመለስ የበለጠ ጉዳይ አለመኖሩን የአማራ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔው አረጋግጧል፡፡
ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ የምክር ቤት አባላትም የሰላም እና ደኅንነት ችግሩ እያሳደረ ያለውን ጫና ገልጸዋል፤ መፍትሄዎችን እና ለመፍትሄው ስምረት ማን? ምን የሥራ? የሚሉ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡
የሰላም ችግሩ በሰላም፣ በጤና፣ በልማት እና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ የፈጠረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን የምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል፡፡ የሰላም መደፍረስ ችግሩ ሕጻናትን ከትምህርት እንዳራቃቸው ጠቁመዋል፡፡ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ከትምህርት ውጪ ሆነው የከረሙ ሕጻናት መኖራቸው፤ በአንዳንድ አካባቢዎችም ትምህርት ጀምረው ግን ማጠናቀቅ ያልቻሉ ተማሪዎች ለከፋ የሥነ ልቦና ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ የዓመቱን ትምህርት አጠናቀው ለፈተና የደረሱትም ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡
ችግሩ በትውልድ ቅብብሎሽ ላይ ካሳደረው ተጽእኖ ለመላቀቅ አሁንም ሰላምን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ መሥራት እንደሚገባ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡
ያም ሆኖ ክልሉን ከከፋ ጉዳት ለመታደግ ሰላም ላይ የተሠራው ሥራ መልካም ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ይህም ለሰፋፊ የልማት ሥራዎች በር መክፈቱን ጠቁመዋል፡፡ እየተሻሻለ የመጣውን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ሕዝብ የሚፈልገውን በሰላም ወጥቶ የመግባት ፍላጎት ለማሳካት ግን አሁንም በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡ ለዚህም አመራሩ ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
የሕግ፣ ፍትህ እና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አስናቁ ሃይሉ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁት የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ አሁንም በመሠረታዊነት አልተፈታም፡፡
መንግሥት በሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች እና ወረዳዎች መደበኛ መዋቅሩን ዘርግቶ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሰላም ማስፈን ላይ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ አሁንም ከእንቅስቃሴ ገደብ አለመላቀቁ፣ የሕግ ማስከበር ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በራስ አቅም ማከናወን አለመቻሉ በክፍተት አንስተዋል፡፡ የሕግ ማስከበር ሥራውን በውጤታማነት ለመወጣት የጸጥታ መዋቅሩን በትጥቅ እና በሎጀስቲክ ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን መብት እና ጥቅም ማስከበር ዋናው ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የክልሉን ሕዝብ የጸና አንድነት መጠበቅ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ምጣኔ ሐብታዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ክልሉ ለገጠመው የሰላም እጦት ምላሽ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ችግሩንም በሰላማዊ መንገድ መፍታት የክልሉ መንግሥት አቋም መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳይደርስ ችግሩ በሰላም እንዲፈታ በሀገር ሽማግሌዎች እና በሌሎችም አካላት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ሕዝቡ በከፍተኛ ምሬት ላይ መሆኑን የተናገሩት ርእሰ መሥተዳድሩ፣ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አማራጭ የመጀመሪያ አማራጭ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ለችግሩ መፍትሄ ማግኘት ጠንካራ የፖለቲካ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎች መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች መሪዎች በሠሩት ሥራ በርካታ ታጣቂዎች ሰላማዊ መንገድን መርጠው ወደ ሕዝቡ መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሰላም አማራጭ በማይቀበሉ፣ የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት በሚያውኩ አካላት ላይ የሚወሰደው የሕግ ማስከበር ሥራ ግን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ የውስጥ አቅምን ማጠናከር ዋናው የሰላም አማራጭ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳደሩ፣ የክልሉን የጸጥታ እና የፖለቲካ ኃይል ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እና በሕግ ማስከበር እርምጃ ለመቀልበስ እየተሠራ ካለው ሥራ ጎን ለጎን የመልሶ ግንባታ ሥራ በትኩረት እንደሚከናወንም አስታውቀዋል፡፡ ሕዝብ እየተሻሻለ ላለው ሰላም ባለቤት እንዲሆን የሚያስችሉ ሕዝባዊ ውይይቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡ በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የሐምሌ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም