የስብሰባዉ መሪ አዳራሹን የሞላውን ተሰብሳቢ ቃኘት ቃኘት አደረጉና፣ “ዛሬ ይህን ስብሰባ ማድረግ የፈለግንበት ምክንያት ባገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ተወያይተን በጋራ መፍትሄ ለመሻት ነው:: በዚህ ስብሰባ የተገኛችሁ ያገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞች በመሥሪያ ቤታችሁ ስትሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ወደ ሌላ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ስትሄዱ ደግሞ ተገልጋዮች መሆናችሁ ግልጽ ነው:: ስለሆነም አገልግሎት ፈልጎ ወደ እናንተ የሚመጣውን ተገልጋይ እንዴት እንደምታገለግሉት፣ እናንተም አገልግሎት ፈልጋችሁ ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስትሄዱ እንዴት እንደምትስተናገዱ እንድትገልጹልን ነው የምንፈልገው:: በዚህ መሠረት አስተያየት መስጠት የምትፈልጉ እጃችሁን እያወጣችሁ አሳዩኝ” አሉ:: በዚህ ቅጽበት ከተሰብሳቢው ከግማሽ በላይ የሚሆነው እጆቹን አወጣ::
አንዳንዶች ለመናገር ካደረባቸው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ እጃቸውን እያርገበገቡ፣ “እዚህ!… እኔ!… ሀሳብ፣ አስተያየት አለኝ!…!…” እያሉ ቅድሚያ ዕድል እንዲሰጣቸው ሞገቱ:: ሰብሳቢው አስተያየት መስጠት የሚፈልገው ሰው ቁጥር ከገመቱት በላይ በመሆኑ ዕድል የሚሰጡትን ሰው ለመለየት ተቸግረው በምን መንገድ ዕድል መስጠት እንዳለባቸው እያሰቡ ለደቂቃ ያህል ከቆዩ በኋላ እጆቻቸውን ከፍ አድርገው አውጥተው እያርገበገቡ ካልተናገርን ከሚሉት ውስጥ ላንደኛው የመጀመሪያውን ዕድል ሰጧቸው፤ ይህን ያህል ለመናገር የፈለገው ልንማርበት የምንችል አንዳች ቁም ነገር ቢኖረው ነው ብለው በማሰብ:: በመቀጠልም ከግራ ረድፍ በመጀመር “አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት…” እያሉ ዕድል ሰጡ::
የመጀመሪያው ዕድል የተሰጣቸው ጎልማሳ ከመቀመጫቸው እየተነሱ፣ “እኔ ባለጉዳይ ወደ ቢሮየ ሲመጣ ከመቀመጫየ በመነሳት እንዲቀመጥ ካደረግሁ በኋላ ጉዳዩን በደንብ እንዲያስረዳኝ አደርጋለሁ፤ ከዚያም ጉዳዩ የሚመለከተኝና በእኔ አቅም የሚፈጸም ከሆነ ፈጽሜለት እሸኘዋለሁ፤ ጉዳዩ እኔን የማይመለከተኝ እንዲሁም በእኔ አቅም የማይፈጸም ከሆነም ጉዳዩን ወደ ሚመለከተው ወይም የመፈጸም አቅም ወዳለው ሰው እመራዋለሁ” አሉ:: ጎልማሳው ይህን ሲናገሩ ራስን ለመካብ ይህን ያህል መሽቀዳደም ለምን አስፈለገ በሚል ይመስላል ተሰብሳቢው ያጉረመርም ጀመር:: ጉርምርምታው ቅሬታ የፈጠረባቸው ጎልማሳው አስተያየት ሰጪ፣ “እውነቴን ነው የምላችሁ!… እኔ መሥሪያ ቤት መጥቶ የተጉላላ ሰው ያለ አይመስለኝም” አሉ:: ይሄኔ ጉርምርምታው ወደ ሳቅ ተቀየረ::
ሳቁ ጋብ ሲል፣ “ውሸት! ውሸት! ባለጉዳይን እንደ እሳቸው የሚያጉላላ ሰው አላጋጠመኝም! ከባድ ችግር ነው ያለባቸው” የሚሉ ድምጾች ከዚያም ከዚህም ተሰሙ፤ ድምጾቹን ሌላ ሳቅ አጀባቸው::
ተሰብሳቢዎች ዕድል ሳይሰጣቸው መናገራቸው ቅር ያሰኛቸው ሰብሳቢዉ፣ “እባካችሁ ጎበዝ ዕድል የተሰጣቸው ይናገሩና በሁለተኛው ዙር ወደ እናንተ እመጣለሁ!” በማለት ተናጋሪዎቹን ዝም ሊያሰኙ ሞከሩ:: ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው መናገር ጀምረው ከነበሩት ተሰብሳቢዎች አንደኛው በንግግራቸው ሲቀጥሉ ሌሎቹ እያጉረመረሙ ቁጭ አሉ:: ሰብሳቢው ማሳሰቢያቸውን ከመጤፍ ያልቆጠሩትን አስተያየት ሰጪ በተደጋጋሚ በማሳሰብ ዝም ሊያሰኟቸው ቢሞክሩም ሰውየው አሻፈረኝ ብለው ወቀሳቸውን ቀጠሉ::
“ክቡር ሰብሳቢ ‘እኔ መሥሪያ ቤት መጥቶ ባገልግሎት አሰጣጥ የተጉላላ ሰው ያለ አይመስለኝም’ ያሉት ሰው ላንድ ጉዳይ አንድ ወር ሙሉ ደጅ ሲያስጠኑኝ ነው የኖሩት:: ወር ሙሉ ያጉላሉኝ ደግሞ አንዲት ደብዳቤ ለመምራት ነው:: በብዙ እንግልት አግኝቻቸው ሳነጋግራቸው ‘ጥያቄህን በጽሑፍ አቅርብ፤ ለሚመለከተው አካል እመራልሀለሁ’ አሉኝ፤ አቀረብሁ:: ደብዳቤውን ግን እስከዛሬ አልመሩልኝም:: ባለጉዳይን እንዲህ እያጉላሉ ‘ባለጉዳይን ከመቀመጫየ በመነሳት ነው የማስተናግደው፤ አይጉላላም’ ማለት ተገቢ አይደለም! ሲሉ አጥብቀው ወቀሷቸው::
በመቀጠል ሦስተኛው ተናጋሪ ተነሱና፣ “እኔ ከመጀመሪያው እንዲሁም ሁለተኛው ተናጋሪ መሥሪያ ቤቶች ባለጉዳይ ሆኜ ሄጄ አውቃለሁ፤ ሁለቱም ባለጉዳይ ማስተናገድ ላይ ከባድ ችግር ነው ያለባቸው፤ ከመጀመሪያው ተናጋሪ ቢሮ መመላለስ ከጀመርሁ ይኸው ሁለት ወር ሊሆነኝ ነው:: ብዙ ጊዜ ስኸድ ፀሐፊያቸው ‘የለም!’ ትለኛለች:: ተመላልሼ ተመላልሼ ሳገኛቸው ደግሞ ወይ ነገሩን ግልጽ አድርገው አይነግሩኝ ዝም ብለው ያመላልሱኛል… ይሄ የሚሆነው ለምንድነው?” በማለት ቅሬታ አዘል ጥያቄ ሰነዘሩ::
“የሁለተኛው ተናጋሪ መሥሪያ ቤትም ቢሆን ኃላፊነቱን ባግባቡ እየተወጣ ነው የሚል እምነት የለኝም:: የታክሲ ትራንስፖርት ታሪፍ ታክሲዎች በተመኑት ሕገ ወጥ ታሪፍ እየከፈልን እየተበዘበዝን ነው:: ከዚህ በፊት ታሪፍ በርቀት መጠን ነበር የሚወሰነው:: አሁን ግን በታክሲዎች ተመን ላጭርም ሆነ ለመካከለኛ ርቀት ተመሳሳይ አሥር ብር እየከፈልን እንገኛለን:: ባልጸደቀ ታሪፍ ከፍተኛ ገንዘብ መክፈላችን ሳያንስ ሰው በሰው ላይ እያደራረቡ እየጫኑ እያሰቃዩን ነው:: ተቆጣጣሪዎች የታሪፉን ጉዳይ ጨርሰው ረስተውታል:: ትርፍ የሚጭኑትን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ያዝ ለቀቅ ነው:: የታሪፉን ጉዳይ ለምን ዘነጉት? ትርፍ በሚጭኑትስ ለምን ያልተቋረጠ ቁጥጥር አያደርጉም?” ሁለተኛው ተናጋሪ ሌላ መሥሪያ ቤት ላይ ጣታቸውን ከሚቀስሩ ለምን ወደ ራሳቸው መሥሪያ ቤት አይመለከቱም?” በማለት ጥያቄ አቅርበው ተቀመጡ::
አስተያየት ሰጪው እንደተቀመጡ ሰብሳቢው፣ “በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ይህ ሁሉ ጫጫታ የሚያሳየን በየተሰማራንበት መሥሪያ ቤት ባለጉዳይን በተገቢው መንገድ በማስተናገድ ረገድ ችግሮች ያሉብን መሆኑን ነው:: አገልግሎት ለመስጠት ተቀምጠን አገልግሎት ፈልጎ የመጣን ተገልጋይ ባግባቡ የማናስተናግድ ከሆነ እኛም ወደ ሌሎች መሥሪያ ቤቶች ስንሄድ ሠራተኞች ከመቀመጫቸው ተነስተው፣ አቤት ወዴት ብለው እንዲያስተናግዱን መጠበቅ የለብንም፤ ያልዘራነውን ማጨድ አንችልምና” በማለት ስብሰባውን ለማጠቃለል ሲሞክሩ አንዲት ጠና ያሉ ተሰብሳቢ፣ “እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ! ይፈቀድልኝ!” እያሉ ከመቀመጫቸው ተነሱ:: ሰብሳቢውም፣ “ይቀጥሉ!” በማለት እንዲናገሩ ፈቀዱላቸው::
“አስተያየት መስጠት የፈለግሁት ከትራንስፖርት ጋር ተያይዞ በተነሳው ጉዳይ ላይ ነው:: እንደተባለው ባልጸደቀ ታሪፍ እየከፈልን እየተበዘበዝን ነው፤ ላጭሩም፣ ለመካከለኛውም ለረዥሙም መንገድ ተመሳሳይ ብር ክፈሉ መባላችን ትክክል አይደለም:: ስለዚህ የሚመለከተው አካል ይህንን ማስተካከል አለበት:: ‘ሰው በሰው ላይ እያደራረቡ እየጫኑ እያሰቃዩን ነው’ ለተባለው ግን ጥፋቱ የእኛ የተሳፋሪዎች ጭምር ነው:: እየተጋፋን እንደዕቃ ትርፍ ስንጫንላቸው እነሱ ምን ያድርጉ?! ዕቃ አይደለሁም፤ በትርፍ አልጫንም ማለት ያለብን እኛ ነን! በትርፍነት አንሳፈርም ብንል እየተሸከሙ አያስገቡንም! ዝም ብሎ ሰው ላይ ጣትን መቀሰር አይጠቅምም! ወደ ራሳችንም መመልከት አለብን! በሌላው መሥሪያ ቤት ላይ ጣት ለመቀሰር ይህን ያህል ከምንሽቀዳደም ሰብሳቢው እንዳሉት ባለጉዳይ ወደ ቢሮየ ሲመጣ እንዴት ነው የምቀበለው? እንዴትስ ነው የማስተናግደው? የምሠራበት መሥሪያ ቤትስ ባለጉዳዮችን እንዴት እያስተናገደ ነው?” ብለን መጠየቅ አለብን:: አጥፍተን ላለመጠየቅ ስንል አላጠፋንም በማለት ከምንሟገት ወደ ራሳችን ብንመለከት በመጀመሪያ የምንጠቀመው እኛ ነን፤ ጨርሻለሁ! አመሰግናለሁ!” ብለው ተቀመጡ::
አስተያየት ሰጪዋ እንደተናገሩት ብዙዎቻችን አጥፍተን “ለምን አጠፋችሁ?!” ተብለን ስንጠየቅ ላለመጠየቅ ስንል “አላጠፋንም!” በማለት እንሟገታለን::
አንዳንዶቻችን ደግሞ ጥፋት ፈጽመን “አላጠፋንም” ማለታችን ሳያንስ ሌሎችን ባልፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂዎች ስናደርግ እንስተዋላለን፤ “እኔ አላጠፋሁም፤ ያጠፋው ወይም ያጠፋችው እሱ ወይም እሷ ናት” በማለት::
ጥፋት ፈጽመን “እኛ አላጠፋንም” ከማለታችንም በላይ ሌሎችን ባልፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ ለማድረግ የምንሞክር ሰዎች እዚህ ላይ ሁለት ስህተቶችን መሥራታችንን ልብ ማለት ያሻናል:: አንደኛው ጥፋታችን አጥፊዎች ሆነን ሳለ “አላጠፋንም!” ብለን መዋሸታችን ነው፤ ሁለተኛው ጥፋታችን ደግሞ ሌሎችን ባልፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ ማድረጋችን ነው::
አጥፍተን “አላጠፋንም፤ ያጠፋው እገሌ ነው” በሚል ከመዋሸት እንዲሁም በሌሎች ላይ ጣት ከመቀሰር በዘለለም “ይሄ ነገር ጥፋት አይደለም፤ ትክክለኛ ርምጃ ነው!” በማለት ጥፋተኝነታችንን ላለመቀበል የምንሞግት አንጠፋም::
ይህ ሁሉ ጣት መቀሳሰር ለእኛም ሆነ ለሌሎች የሚጠቅም አይደለም:: እናም ሴትዮዋ እንዳሉት ይህ ወደ ራሳችን ያለመመልከት ችግራችን ለእኛም ሆነ ለሌሎች የማይበጅ መሆኑን ተገንዝበን ወደ ራሳችን ብንመለከት በመጀመሪያ የምንጠቀመው እኛ ነን::
ጥፋተኞች መሆናችንን ልቦናችን እያወቀው ጣታችንን በሌሎች ላይ ብንቀስር ኅሊና የሚባል ነገር አለና መጀመሪያ የምንጣላው ከራሳችን ጋር ነው፤ ‘ምን ዓይነት ሰው ነኝ፤ እንዴት እንዲህ አደርጋለሁ?’ በማለት ከራሳችን ጋር ሙግት መግጠማችን አይቀርም:: ጥፋት ፈጽመን አልፈጸምንም ስንል በመጀመሪያ የዋሸነው ራሳችንን ነውና ራሳችን ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ዝቅ ስለሚል በራስ የመተማመን ስሜታችን ዝቅተኛ ይሆናል:: በራሱ የማይተማመን ሰው ደግሞ ራሱን ችሎ በሁለት እግሩ መራመድ ስለሚሳነው የሚያቅደውም ሆነ የሚፈጽመው ነገር ሁሉ በጥርጣሬ የተሞላ ሊሆን ይችላል:: “ይሄ ነገር ይሳካልኝ ይሆን ባይሳካልኝ ምን አባቴ ሊውጠኝ ነው?…” የምንል ፈሪዎች እና ተጠራጣሪዎች ልንሆን እንችላለን::
ራሳችን ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ዝቅ ማለቱ እና ፈሪዎች እንዲሁም ተጠራጣሪዎች መሆናችን ደግሞ በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገን ነው የምንታየው የሚል የሥነ ልቡና ስብራትን ሊያስከትልብን ይችላል:: ይህ ደግሞ በተራው ከሰዎች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በጥርጣሬ እና በስጋት የተሞላ እንዲሆን ያደርጋል:: ባንጻሩም ወደ ራሳችን ተመልክተን ስህተታችንን ለይተን በጊዜ ካረምን ታላቅነታችንን ራሳችን ለራሳችን እየነገርነው ስለሆነ የሚሰማን የኅሊና ርካታ እንዲሁም በራስ የመተማመን ስሜት ከፍተኛ ይሆናል::
ፈጥነን ወደ ራሳችን ተመልክተን ስህተታችንን አርመናልና ሌሎች ሰዎችም ቢሆኑ ስህተታቸውን ያርሙ ዘንድ ምሳሌዎች ሆነን እንታያለን:: ምናልባትም ሌሎች ወደ ራሳቸው ተመልተው ስሀተታቸውን ሳያርሙ ቢቀሩ እንኳን እኛ ቀድመን ተገኝተናልና ከዚህ ችግራቸው ይወጡ ዘንድ ብንመክርም ያምርብናል፤ ተሰሚነትም እናገኛለን፤ ብዙዎችንም መለወጥ እንችላለን:: መደማመጥን፣ መተሳሰብን፣ አንድነትን፣ ለጋራ ዓላማ በጋራ የመጓዝ ልምድን እናዳብራለን:: እናም ቢያንስ ለራሳችን ስንል ሰዎች ላይ ጣት ከመቀሰር ወደ ራሳችን መመልከትን፣ ተመልክተንም ስህተቶቻችንን ማረምን ልምድ ልናደርግ ይገባናል::
(ቦረቦር ዘዳር አገር)
በኲር የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም