ወደ ሰላም ደጅ ለመቅረብ ሀቀኛ ውይይት አሁኑኑ ይጀመር!!

0
178

በአንድ ሀገር ቀውስ፣ ግጭት እና ጦርነት ሊፈጠር የሚችለው ተቋማት ሲሟሽሹ፣
ፍትሕ ሲጓደል፣ የሕግ የበላይነት በትክክል ሳይረጋገጥ ሲቀር፣ የመንግሥት የቅቡልነት
እና የመፈፀም አቅም ሲዳከም መሆኑ ግልፅ ነው።
በግጭት እና በጦርነት አዙሪት ውስጥ የገባችው ሀገራችን አሁንም ስለልማት፣
ዕድገት እና ስልጣኔ ለማውራት ዜጎቿ ዕድል አላገኙም። ዜጎች ወጥቶ ለመግባት፣
ውሎ ለማደር፣ አቅዶ ለመስራት እርግጠኛ የሚሆኑበት አስተማማኝ የሰላም ዋስትና
የለም። መንገዶች ከሚፈለገው ቦታ አያደርሱም:: የሰላም እንቅልፍ መተኛት
አይቻልም። ታሞ ለመታከም ሁኔታው ከባድ ነው። ጥርጣሬው፣ መፈራረጁ፣
ውጋው ደብልቀው የሚለው ክፉ ዜማ አየሩን ይዞታል። ተፋላሚ ሀይሎች ለሕዝብ
ሲሉ ለመነጋገር፣ ተኩስ ለማቆም እና በሀቀኛ ውይይት ችግሩን ለመፍታት እስካሁን
ቁርጠኛ ፍላጎት እያሳዩ አይደለም። በሁሉም ዘንድ እልህ፣ እኔ ብቻ አሸንፋለሁ፣
አጠፋዋለሁ፣ እደመስሰዋለሁ የሚል ነጋሪት እየተጎሰመ ነው።
ይሄ መንገድ የጋራ አሸናፊነትን አይፈጥርም፣ የጋራ ሰላምን በዘላቂነት
አያረጋግጥም። ዘላቂ ሰላም የሚመጣው በፖለቲካ ውሳኔ፣ በሀቀኛ ውይይት እና
ንግግር፣ በድርድር፣ በፍትሕ፣ ሕዝብን ማዕከል ባደረገ ተቋማዊ ጥንካሬ ነው።
በየትኛውም ዓለም እና ሁኔታ የዕርስ በዕርስ ጦርነት በፍጥነት እና ቅድመ ሁኔታ
ሳይኖር በአስቸኳይ በውይይት ካልተፈታ የታሪክ ጠባሳን፣ ዘላቂ ዕዳን፣ ዛሬያዊ
ኪሳራን በጠቅላላው ከባድ ውድቀትን ያስከትላል።
በመሆኑም ሁሉም ወገኖች በፍጥነት እና በእውነት ከፖለቲካዊ ሴራ ርቆ የሕዝብን
ሰቆቃ በማሰብ ወደ ሰላም ደጅ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ወደ ሰላም ደጅ ለመቅረብ
ደግሞ ሀቀኛ ውይይት፣ ተኩስ ማቆም፣ ሰጥቶ መቀበልን መርሕ ያደረገ ድርድር
እውነተኛ ፍትሕ ማዳረሻ መንገዶች ናቸው። ሰላም በምኞት፣ በዜማ፣ በስብከት
አይመጣም። ሰላም የሚመጣው በውይይት፣ በንግግር፣ በድርድር፣ በፍትሃዊነት፣
የሕዝብን ጥያቄ በመመለስ፣ በእርቅ፣ በጋራ በመስራት እና የጋራ ተዓማኒ ተቋም
በማዋለድ ነው።
ጥያቄ ያነሳ አካልን ጥያቄውን ትቶ ጠያቂውን በማሰር፣ የፖለቲካ ሐሳብን እና
መፍትሄን በአፈ ሙዝ መመለስ፣ የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት አዛብቶ በራስ ፖለቲካዊ
ትርጓሜ መመንዘር ለሰላማዊ ሁኔታ አያቀርብም። ችግሩን ለአንድ ወገን ብቻ
ከመስጠት፣ ራስንም በመገምገም እና የግጭቶችን ተፈጥሮ በሀቀኛ ትንታኔ በማየት
ለእውነተኛ ሰላም መቆም ቀጠሮ የለሽ ተግባር መሆን ይገባዋል።
ሀገራችን በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች በዕርስ በዕርስ
ጦርነት አይተኬ ሕይዎታቸውን ያጡበት፣ የሀገራችን አንጡራ ሐብት የወደመበት፣
አሁንም ይሄ አውዳሚ መንገድ ያልተገታበት ማህበረ ፖለቲካ ተፈጥሯል። ሁኔታው
በዚህ ከቀጠለ የመንነት፣ ሶሪያነት፣ ሊቢያነት፣ ዩጎዝላቢያነት የሩቅ ምሳሌዎች
ሳይሆኑ የሀገራችን አምሳሎች መሆናቸው አይቀርም። አሁንም ችግሩ እየከፋ እና
እየተወሳሰበ ከመሄዱ በፊት የሰላም እጆች ይዘርጉ፣ ተፋላሚ ወገኖች ወደ መሃል
መንገዱ ይቀራረቡ፣ አስታራቂዎች ይትጉ፣ ሕዝባችን የናፈቀውን ሰላም ያግኝ!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here