ወደ ቀደመዉ ስልጣኔያችን ለመመለስ እንትጋ!

0
190
በዚህ ዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የተቀዳጁ፤ ያልተጠሩበት ሁሉ አቤት የሚሉ፤ ያልተጋበዙበት ሁሉ የሚታደሙ፤ አያገባቸው እየገቡ ፈላጭ ቆራጮች፣ ግዙፉን ኢኮኖሚ የገነቡ፤ በሁሉም ዘርፍ የአስተማማኝ ሀይል ባለቤቶች ፤የዓለም የኅይል ሚዛን ወሳኞቹ እነሱ ጥቂቶቹ ኅያላን ሀገራት ትናንትናቸው የማይታመን ዛሬያቸው አስደማሚ፤ ነጋቸው የማይገመት ነው
“ሰዎች ራሳቸውን ለማረምና ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲሉ በስጋና በመንፈስ ያፈሩት ከመጀመሪያ ጀምሮ አሁን ድረስ የተከማቸው የሥራ ፍሬ ስልጣኔ ይባላል” ይላሉ ታላቁ ከበደ ሚካኤል።
ይህንን በተግባር የገለጡ የዓለም ሀገራት ግን ጥቂቶች ናቸው። መሠልጠን ከትናንንቱ በልጦ ነገን የተሻለ በማድረግ ጎዳና ታላቅ ሀገርን፤ የሠለጠነ ህዝብን ብሎም ጠንካራ ሀገር መንግስት መመስረት ነው።
በዓለም ላይ በአራቱም ማዕዘን የነበሩ ህዝቦች በየበኩላቸው ኑሮን በማሻሻል ትልቅ ርምጃ አድርገዋል።በእስያ ውስጥ የሺን እና የህንድ ህዝቦች በሕንፃ አሠራር በሀይማኖት በእርሻና የእጅ ጥበብ ሥራ ሠልጥነዋል። በተለይም በሳይንስ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ከፍ ካለ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። ሱሜሪያና ግብፅ ፋርስና ሜድ ከለዳውያንና ባቢሎናውያን አስደናቂ ሥልጣኔ ላይ ነበሩ። በደቡብ አሜሪካ አዝየቲክ ማያ እና ኢንካ ሥልጣኔያቸው የሚደነቅ ነበር።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የገነኑት የምድሩ አልበቃ ቢላቸው በሌላውም የዓለም ክፍል መራቀቅ ላይ ያሉት እነሱ ስለመፈጠራቸው እንኳን ሳይታወቅ ቀደምት የስልጣኔ እና የሁሉም ነገር መፍለቂያ ነበረች።
ነበረች ይባላል እንደዋዛ። ከሁሉ ቀደምት አሁን ግን ስሟ የሚነሳ በኋላ ቀርነት። ለዚህም የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የስልጣን ሽኩቻ፤ ድርቅ እና ረሀብ፤ የሴራ ፖለቲካ እና ሌሎችንም በምክንያትነት ልንጠቅስ እንችላለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ያን ጊዜ በዓለም ህዝቦች ዘንድ ተፈርታ እና ተከብራ ትኖር ነበር። ያን ጊዜ እና ነበር ለማለት የምንገደደው አሁን አሁን በሁሉ የደረጁ እነሱ በተለያዩ የእኛ ጉዳዮች ካልወሰንን በሚል የሚዳዳቸው መብዛታቸውን በማየት ነው።
አንድ ሀገር፣ ሀገር የሚባለው ህዝቡ እና የአኗኗር ዘይቤው ያለው መልከዓምድርና ህዝባዊ ሥርዐተ ማህበር ነው። በርግጥ በዚህ ረገድ ሀገራችን የመላው አፍሪካ የኩራት ምንጭ ናት። አፍሪካ የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት እሽቅድምድም ሰለባ በነበረችበት ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ነፃነቷን እንደያዘች መቀጠሏ መላው አፍሪካ ለነፃነቱ፣ ለባህሉ፣ ለሉዓላዊነቱ፣ ለማንነቱ እና ሰብዓዊነቱ መከበር ላለው ህልም መነሻ እና ሀሁ የተቆጠረባት እንቁ ናት።
እዚህ ላይ የሀገር ፍቅርን ከነኩራ፤ ጀግንነትን ከነክብሩ፤ ፊደልን ከነቁጥሩ፤ ዘመንን ከነቀመሩ ያሻገሩልን የቀደሙት እነዚያ ታላላቆቻችን ውለታቸው የበዛ እና የከበረ ነው። በየትኛውም የዓለም ክፍል የገዘፈ ተፅዕኖ ፈጣሪነትን የተቀዳጁት ኀያላን ከሁሉ በላይ ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን በመመስረታቸው ነው። ሀገርም ሆነ ህዝብ ያለ ጠንካራ መንግሥት ምንም ናቸው። በሚፈጠር ሁከት እና ትርምስ ታሪክ ሆነው የቀሩ ከተሞች በዚሁ መዘዝ መንግስሥት አልባ የሆኑ ሀገራት የደረሰባቸው ፈተና እና መከራ ከቃልም በላይ ነው።
ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት እና ለማፅናት የሠለጠነ እና ጠንካራ ህዝብ፣ ጠንካራ ተቋማት እና የመልካም ስነምግባር ባለቤት ዜጋ የግድ ነው። መልካም ዜጋ ሀገሩን የሚወድ የሙስና ጥፋትን የሚጠየፍ በስነምግባር የታነፀ ክፉን የሚጠላ ነው ።
በዘመናዊት ቱርክ ግንባታ አበርክቶው ኀያል የሆነው እና እ.ኤ.አ ከ1923 ህይወቱ እስካለፈበት ህዳር 1938 ቱርክን የመራውን ሙስጠፋ ከማል ቱርክን የሚያህል አገር ያቀና የፖለቲካ ሰው የላቸውም ቱርካውያን። እንደውም የቱርክ ህዝብ በእርሱም ልክ ሰው የላቸው።
ታዲያ ከዚህ የተከበረ ጀግናቸው በማስከተል ቱርክ ላይ ትልቅ አሻራ ያኖሩት ሰው ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ሆነዋል። እኚህ ሰው ላለፉት 20 ዓመታት አገሪቱ ን መርተዋል። ሀገሪቱን ወደ ቀደመው እና ገናናው የኦቶማን ዘመነ መንግሥት ለመመለስ የሚጥሩ ታላቁ ሰው በመባልም ይወደሳሉ፤ መልካም ዜጋነት ይሄ ነው።
በርግጥ በሌሎችም ኀያላን በሚባሉት ሀገራት የዜጎች የሥልጣኔ ደረጃ ከፍ ማለት እና የመሪዎች የአመራር ጥበብ፤ የሀገር ፍቅር ስሜት፤ ሀገራቱ የመሰረቱት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት፤ ስማቸው በዓላም መድረክ ሲነሳ በአኩሪነቱ ነው።
ሕንድ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። በኛ ሀገርም ቢሆን ቀደምት ነገሥታቱ የሀገር ፍቅር ስሜት እና የሰንደቅ አላማ ክብር በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ታትሞ እንዲኖር ጥረዋል። የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና ክብር ለማስጠበቅ መሪዎቹ ራሳቸው ሳይቀሩ መስዋዕትነትን በመክፈል ለሀገሩ አጥንቱን የሚከሰክስ ደሙን የሚያፈስ ነፍሱን የማይሰስት ጀግና ትውልድን ፈጥረዋል። ኢትዮጵያዊ ባህል እንዲዳብር የራሳችን ቋንቋ ሳይበረዝ እንዲቀጥል፤ ኢትዮጵያዊነት ክብርና ኩራታችን መቼም እንዳይናድ በተግባር አስተምረዋል።
የሩቁን ትተነው ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ የአፄ ቲዎድሮስ በአንድ መንግሥት ስር የምትተዳደር ሀገር ህልም እና ጥረት፤ በአፄ ዮሀንስ እና አፄ ምንሊክ ተጠናክሮ እና ተግባር ላይ ውሎ ዛሬ ላይ በኩራት ኢትዮጵያ የምንላት ጥንታዊት ሀገር ቀጥላለች።
ወደ አፄ ኀይለ ሥላሴ የተሸጋገረው ዘውዳዊ ሥርዓት ሀገራችንን ወደ ልማት እና እድገት ጎዳና ለመውሰድ የነበረው ጥረት፤ ኢትዮጵያን በዓለም መንግሥታት ሕብረት መስራች ያደረገ፤ በአፍሪካ ሕብረት ጀማሪነት ከፍተኛውን ሚና እንድትጫወት ያስቻለ፤ በዓለም የሰብዓዊ መብት ሰነድ የመጀመሪያዋ ፈራሚ በመሆን ስመ ገናና እና ቀደምትነቷን ያስመሰከሩበት ሁነት የሚዘነጋ አይሆንም።
ከዚያም በኋላ ቢሆን በሀገራችን በየዘመናቸው የነበሩ እና ያሉ መሪዎች ታፍራ የተከበረች ሀገር እንድትኖረን የየራሳቸውን አሻራ አኑረዋል፤ እያኖሩም ነው። ጠንካራ ሀገር እና ሀገረ መንግሥት በመገንባት ሒደት የሀገር ፍቅር ስሜቱ የጠነከረ፣ ኢትዮጵያዊ ባህል እና እሴትን የተላበሰ ዜጋን መፍጠር፣ ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት እና ወሳኝ አቅም ያላቸውና ግብረ ገብን የሚያፀኑ መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ ተቋማት መፍጠር የግድ ነው። ተሳካላቸው የምንላቸው ሀገራት መነሻቸው ይህ ነውና።
በዚህ ረገድ በአመክንዮ የሚያምን፣ በስሜት የበሰለ ወጣት፣ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸው የጎላ ነው። በዚህ ረገድ ሆደ ሰፊነት፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት እና ከሁሉ የምትበልጠውን መተኪያ የሌላትን እናት ሀገርን ብቻ ማስቀደም ተገቢ ነው። እኔነት ቀርቶ እኛነት ሲቀድም በርግጥም ሁሉም ቀላል ይሆናል።
ታላቁ ከበደ ሚካኤል የሥልጣኔ ጠባይ በሁለት አይነት ሁኔታ ይገለጣል ይላሉ ይሄውም በሰው ባህሪ እና በግዙፍ አካሎች ሥራ ነው። ሰው ብልህ ደግ ትልቅ ሲሆን የሠለጠነ ሰው ይሰኛል። እንደዚሁም ስሜቱ ደብዛዛ፣ ክፉ፣ ጨካኝ፣ ትዕቢተኛ፣ ነጭናጫ፣ ባለጌ፣ ህገወጥ፣ መንፈሰ ጠባብ፣ ምኞተ ወራዳ ሲሆን በዚያው መጠን ያልሠለጠነ አውሬ እንስሳ ያሰኘዋል። እንግሊዞቹ “እኛ የቆምነው በታላላቆቻችን ትከሻ ላይ ነው” እንደሚሉ፣ እኛም ብንሆን የተከፈለልንን አይተኬ ዋጋ በማሰብ ለቀጣዩ ትውልድ ታላቅ፣ በልባችን የምንመኛት ኀያል እና መሠረቷ የፀና ሀገርን ለማስቀጠል የሠለጠንን ሆነን መገኘት የግድ ይለናል።
(ዮናስ ታደሰ)
በኲር መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ዕት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here