የትዝብቴ ዋነኛ ጭብጥ ባለንበት ዘመን እየፈተነን ያለው ፖለቲካዊ ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ምስቅልቅል መንስኤው ምንድነው? መፍትሔውስ? የሚል ነው::
የችግሮቻችንን መንስኤ ለይቶ መፍትሔ ለመሻት “ነገርን ከስሩ፥ ውኃን ከጥሩ” ነውና ከዓድዋ ጦርነት መንስኤ እና ድሉ ካስከተለው ዳፋ መነሳት የግድ ሆኖብኛል::
የጦርነቱ መንስኤ አንድ እና አንድ ነው – ቅልጥጥ ያለ! አፍሪካን በቅኝ ግዛት ከወረሯት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አንዷ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ጥሳ አገር ወረረች፤ በ1880ዎቹ መጨረሻ:: ያኔ የንጉሥ ምኒልክን የክተት አዋጅ ተከትሎ መላው ኢትዮጵያዊ ሀገሩን ከወረራ ለመታደግ ወደ ሰሜን ተመመ፤ እናም የካቲት 23/1888 ዓ.ም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀው ወራሪ ፋሽስት ጦር ጋሻ ባነገበ አገር ወዳድ አርበኛ ተደምስሶ ተሸነፈ::
በጥቁር ህዝብ መሸነፋቸው እንደ እግር እሳት ያንገበገባቸው አውሮፓውያን ቅኝ ገዥ ሀገራት ታዲያ ለመላው አፍሪካዊ ድንቅ የነፃነት ተምሳሌት የሆነው የዓድዋ ድል እንቅፋት እንደሆነባቸው ሲረዱ ድሉን ቀልብሰው የቅኝ ግዛት ትልማቸውን ዳግም ለማስቀጠል እንዲያመቻቸው የኢትዮጵያውያኑን የአሸናፊነት ምስጢር የሚያጠኑ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ መኮንኖቻቸውን በ“ሚሸነሪ” ስም የሃይማኖት ሰባኪ መነኩሴ በማስመሰል ቀሚስና ቆብ አልብሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አሰማሩ::
ከበርካታ ዓመታት ጥናት በኋላ ተገኘ የተባለው ውጤትም “የኢትዮጵያውያኑ የአሸናፊነት ምስጢር አንድነታቸው ነው” የሚል ሲሆን ይህንን አንድነት ማጥቃት እና ማጥፋት ደግሞ ኢትዮጵያን ዳግም ወርሮ ቅኝ ለመግዛት ብቸኛው መፍትሄ ነው ተባለ::
ይህንን አንድነት ለማጥቃት ደግሞ የተጠናከረ የፊት ለፊት ጦርነት ማካሄድ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በሚታለሉ ባንዳዎች አማካኝነት በኢትዮጵያ መካከል የርስ በርስ ጦርነት እንዲከፈት በማድረግ አንድነታቸውን ማፍረስና ማጨፋጨፍ ዋነኛ መፍትሄ ነው ሲሉም ደመደሙ::
ፋሽስት ጣሊያን ከፍተኛ ዝግጅት ያደረገችበት እና በተከለከለ የመርዝ ጪስ ህዝብ የመፍጀት ጭካኔን ጨምሮ በርካታ ግፎች የፈፀመችበት ዳግም ወረራዋ ከ1928 -1933 ዓ.ም በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል በኃያላኑ ኢትዮጵያውያን አናብስት አሸናፊነት ተደምድሞ ወረራው ዳግም ሲከሽፍ ኢትዮጵያውያኑን ርስ በርስ የማፋጀቱ ሌላኛው እቅድ ግን እነሆ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን እና የዜጐቿን ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ እየገፋ እዚህ ደርሰናል::
ለዚህ የርስ በርስ ጦርነት መቀስቀሻዎች እንደ መሳሪያ እያገለገሉ ከሚገኙት የግጭት መቀስቀሻዎች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያን ጠል የሆኑ ባንዳዎች እየፈጠሩ የሚያሰራጯቸው ሀሰተኛ ትርክቶች እና የጥላቻ ንግግሮች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው::
እነዚህ ሀሰተኛ ትርክቶች በሬዲዮና በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣና በመጽሔት፣ በድራማና በፊልም፣ በመፅሀፍ እና ሐውልት በማቆም ጭምር እንዲሰራጩ መደረጋቸውን ስናስተውል ደግሞ በእርግጥም ኢትዮጵያውያኑን በብሔር፥ በእምነት፣ በቋንቋ፣ በዘር እና በባህል ጭምር የማጋጨቱ ሴራ ሆን ተብሎ በእቅድ የሚከወን እንጂ በአጋጣሚዎች የሚከሰት አለመሆኑን እንረዳለን::
እንዲህ ርስ በርስ እያፋጀ ሀገራችን ከኋላ ቀርነት እና ድህነት እንዳትላቀቅ የሚያደርገን ሴራ በጊዜ ሂደት ትውልድ ሲቀየር መክሰም ሲገባው እየሆነ ያለው ግን ግልባጩ ነው:: በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተፈጠረው የማህበራዊ ብዙኃን መገናኛ አውታር መስፋፋት ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጐታል::
የሰለጠነው ዓለም ይህንኑ አዲስ የህዝብ መገናኛ ዘዴ ለእድገት እና ስልጣኔ የሚበጁ መረጃዎችን ለመለዋወጥ ሲጠቀምበት እኛ ግን ለርስ በርስ ብጥብጥ እና ሁከት፣ ለባህል ብክለት እና ውድቀት እያዋልነው እንገኛለን:: እርግጥ ነው እኛም ሀገር ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ መረጃ የመለዋወጫ መንገድ፣ የመረዳዳት፣ አዲስ ሃሳብ የማፍለቂያና የገቢ ምንጭ ማግኛ ያደረጉት እየተጠቀሙበት ከራስ አልፎ ሀገርን የሚጠቅምና ትውልድን የሚያድን ስራን እየሰሩበት ይገኛሉ::
በተለይም ሃገርን እንደሀገር እንደ ማገር ካስተሳሰሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ ሃይማኖት ነው፤ እንደሌሎች ጉዳዮች አፋችን ላይ የመጣልንን ሃሳብና ደስ ያለንን ባለመናገርና በማክበር በጥንቃቄ የምንኖረውና የምንይዘው ጉዳይ ነው:: በሃይማኖት የራስን እምነት ሰዎች እንዲቀበሉና እና እንዲያመልኩ መስበክ የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነው:: ከዚህ አልፎ የሌላኛውን እምነት ማንቋሸሽ እና መዝለፍ፤ ከእኔ እምነት ውጪ ሌላ የለም ብሎ መነሳት ግን ከየት ነው የመጣው? እኔ አላውቅም::
የሚታየኝን መናገር ካለብኝ ግን ያለንበት ዘመን እንኳንና ኃይማኖትህን ፓለቲካዊ ርእዮተ ዓለምን እንኳ በማሳመን ካልሆነ በቀር በግዳጅ የምትጭንበት አይደለም:: የሰው ልጅ የጋርዮሽ ስርዓተ ማህበርን ተከትለው የመጡትን የባሪያ አሳዳሪ እና ፊውዳሊዝም የተባሉ ሥርዓተ ማህበሮችን /አገዛዞችን/ ነፍጥ እያነሳ ጭምር አሻፈረኝ እያለ የተፋለማቸውና ያስወገዳቸው ሰው በተፈጥሮው ፍትሕ እና ነፃነት ፈላጊ በመሆኑ ነው:: ያ የሚፈልገው ነፃነት ደግሞ በፖለቲካል ማህበረ – ኢኮኖሚ ብቻ የታጠረ አይደለም፤ በባህል እና ወጉ፣ በአምልኮቱም ጭምር እንጂ!
ታዲያ ማንኛውም ሰው እንዲህ ዓይነት ማንም ሊገስሰው የማይችል ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው እየታወቀ ተንቀሳቃሽ ስልክ ያለው ሰው ሁሉ ሊከታተለው በሚችል ማህበራዊ መገናኛ ላይ ወጥቶ አንዱ አንዱን መዝለፍ ነውር ነው::
ይህ እንዳለ ሆኖ ዋነኛው የምስቅልቅላችን መፍትሄ ግን ፍትህ ነው እላለሁ፤ ፍትሕን ማስፈን!
“አገር የጋራ ነው፣ ኃይማኖት የግል ነው” እያልን ባደግንበት ሀገር የግል ጉዳያችንን ለግል ሊተዉልን ይገባል:: ማንኛውም ሰው የራሱን እምነት ማስተማርና ማስፋፋት እንጂ የሌሎችን እምነት የመቃወምም ሆነ የመዝለፍ ቅንጣት ታህል መብት እንደሌለው ሊያውቅ ይገባል፤ ሕገ መግሥታችንም ሆነ በሽብርተኝነት ላይ የወጣው ሕግ ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳት እና የጥላቻ ንግግር ማድረግ በሽብርተኝነት ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ያትታሉና ያንኑ ህግ ተፈፃሚ በማድረግ በህገ ወጦች ላይ ለመቀጣጫ የሚበቃ ርምጃ በመውሰድ ሀገርን እና ህዝብን ከፍጅት እና መበታተን መታደግ የፍትህ ኃይሎች ኃላፊነት መሆኑን በመጠቆም ትዝብቴን ቋጭቻለሁ::
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ክብር ለሰውልጆች