የሕዝብ ቁጥር በማጥናት የሚታወቀው “ዳታሪፖርታል” የተሰኘ ድረ ገጽ በ2022 ባወጣው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ሕዝብ 120 ሚሊዮን ገደማ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ውስጥ 24 በመቶ ያክሉ ከ13 እስካ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።
ድረ ገጹ አክሎም 30 ሚሊዮን ገደማ አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች እንደሆኑም ይጠቁማል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ጋር ያላት ትውውቅ ቅርብ ጊዜ ቢሆንም ለመላመድ ግን ጊዜ አልፈጀባትም፡፡ ባሁኑ ጊዜ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ማህበራዊ ትስስር ገጾች በተለያዩ መንገዶች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ።
በጥር 2025 መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የ8 ነጥብ 30 ሚሊዮን የማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ተጠቃሚዎች መለያዎች ነበሩ። ከእነዚህ ተጠቃሚዎች ውስጥ 67 ነጥብ 7 በመቶ ወንዶች ሲሆኑ 32 ነጥብ 3 በመቶ ሴቶች ናቸው። ታዲያ በዚህ መጠን በወጣቶች የተሞላች ሀገር ላይ የሚከሰት ተፅእኖ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች በዘመናችን እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ የመገናኛ እና የመረጃ ምንጮች ተጠቃሾች ናቸው። በተለይ ወጣቱ ለዚህ ክስተት እጅጉን የተጋለጠበት ሁኔታ ይታያል። ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ጥሩ ዕድሎችን እየፈጠሩ ቢሆንም ጥሩ ያልሆኑ ሁኔታዎችንም መፍጠራቸው አልቀረም። እንደ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ቴሌግራም፤ ዩቱብ እና ኢንስታግራም ያሉ ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ከወጣቶች በዘለለም በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሏቸው አያጠራጥርም፡፡ ግንኙነትን እና ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከራቸው ከጥቅሞቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሰዎች ከጓደኞቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሚያውቋቸው ጋር በቀላሉ ለመገናኘት ይጠቀሙባቸዋል። ርቀት ቢኖርም እንኳን የድምጽ እና የቪዲዮ ጥሪዎችን በማድረግ የቅርብ ግንኙነትን ለማስቀጠል ይረዳሉ። አዳዲስ ጓደኞችን እና ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለማገናኘትም እንደ መድረክ ያገለግላሉ።
ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች መረጃ እና ዜና በፍጥነት ለማግኘትም በእጅጉ ይጠቅማሉ። ከተለያዩ ምንጮች መረጃዎችን በማግኘት ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለመያዝ ይረዳሉ። የተለያዩ አስተያየቶችን እና ትንታኔዎችን ለመከታተል ያስችላሉ።
ይህም ብቻ አይደለም፤ ትምህርትን ለማቀላጠፍ እና ዕውቀትን ለማጎልበት የሚረዱ ይዘቶችን እና መረጃዎችን ለመለዋወጥ ያስችላሉ። በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዕውቀትን ለማስፋት ይረዳሉ። የመስመር ላይ ትምህርቶችን እና ሴሚናሮችን በመከታተል ረገድ ያላቸው ፋይዳም ከፍ ያለ ነው።
ምርቶችን እና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ከደንበኞች ጋር በቀጥታ ለመገናኘት እና ግብረ መልስ ለመሰብሰብ ያግዛሉ። አዳዲስ ገበያዎችን ለመድረስ እና ሽያጭን ለማሳደግም ጠቃሚ መሳሪያዎች ናቸው።
ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችን እና ሌሎች የመዝናኛ ይዘቶችን ለመመልከት እና ለማጋራት ያገለግላሉ። ከጓደኞች ጋር አስቂኝ እና አዝናኝ ይዘቶችን በመለዋወጥ ጊዜን ለማሳለፍ የሚኖራቸው ጠቀሜታም የሚናቅ አይደለም።
ማህበራዊ መነሳሳትን ለመፍጠር እንዲሁም ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገም ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣሉ፡፡ የተቃውሞ እና የድጋፍ እንቅስቃሴዎችን ለማስተባበር ከተፈለገም እነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች ሁነኛ ሚና ይጫዎታሉ። የሕዝብን ድምጽ ለማሰማት እና ለውጥ ለማምጣትም ኃይለኛ መሳሪያ ናቸው።
ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች የሚያስተላልፉት መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ የተቀዳ እና እውነታውን መሠረት ያደረገ ከሆነ የሰዉ ልጆች ቤት ሆነዉ መረጃ እንዲያገኙ፣ ግንዛቤ እንዲጨብጡ፣ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ትምህርታዊ ይዘቶችን፣ ዜናዎችን እና ዓለም አቀፋዊ አመለካከቶችን እንዲያገኙ ይረዳሉ፤ ሰዎች ሳይወጡ ሳይወርዱ ስለ ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲያውቁ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲሳተፉ እና ሀሳብ እንዲለዋወጡ ያስችላሉ። እነዚህ መድረኮች ክስተቶችን ለማደራጀት፣ ልምዶችን ለመለዋወጥ እና ያልተሰሙ ድምፆችን ለማጉላት ይጠቅማሉ። በተጨማሪም የሥራ ፈጠራን ለማሳደግ ይረዳሉ።
ወጣት ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ አውታሮችን በመጠቀም ስለማህበራዊ ጉዳዮች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ ማህበረሰቦችን በማስተባበር እና ለመመካከር እንዲሁም ለለውጥ ይጠቀሙባቸዋል። በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች ብቅ ብቅ ያሉ ይዘት ፈጣሪዎች ለዚህ እንደ ማሳያ ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ አውታሮች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሏቸውን ያህል ካጠቃቀም ጉድለት የተነሳ እያስከተሏቸው ያሉ ጉዳቶችም ቀላል የሚባሉ ኣይደሉም፡፡ ከሚያደርሷቸው ጉዳቶች አንዱ እና ቀዳሚው ለተሳሳተ መረጃ ማጋለጣቸው ነው፡፡ የማህበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች የተሳሳተ መረጃ በፍጥነት እና በስፋት እንዲሰራጭ ያስችላሉ፤ ከትክክለኛ መረጃ በበለጠ ፍጥነት። ወጣቶች ከማይታመኑ ምንጮች ተዓማኒነት ያላቸው ምንጮችን ለመለየት የሚያስችል ክህሎት ስለሚጎድላቸው በእንደዚህ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎች ተገፋፍተው የተሳሳተ ግንዛቤ ሲይዙ እና ለሌሎችም ሲያስይዙ ይታያሉ።
የተሳሳተ መረጃ ከሚተላለፍባቸው ጉዳዮች ውስጥም ጤና ተጠቃሽ ነው፡፡ በክትባት፣ ባመጋገብ እና በሌሎች የጤና ባህርያት ላይ በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ ተጽእኖ በማድረግ ከባድ መዘዝ ሊያስከትሉ ይችላሉ። የተሳሳቱ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መረጃዎችን በማስተላለፍም ላለመ ግባባት እና ግጭት መነሻዎች ሲሆኑ ይስተዋላሉ፡፡
ማህበራዊ የትስስር ገጾች የሌሎችን አስደሳች የሚመስሉ እንቅስቃሴዎችን በቋሚነት በማቅረብ በተመልካ ቾቻቸው ዘንድ ጭንቀት እና የመጥፋት ስሜት እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋላሉ።
ማህበራዊ የትስስር ገጾችን መጠቀም ሱስ ሊያስይዝ ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ ማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ለረዥም ጊዜ ተጥዶ የሚውልን ሰው የእንቅልፍ ጊዜን ሳይቀር በመሻማት የእንቅልፍ መዛባት ያስከትላሉ፡፡ ከመተኛት በፊት ማህበራዊ የትስስር ገጾችን መጠቀም በስክሪኖች በሚወጣው ሰማያዊ መብራት እና በይዘቱ አጓጊ ባህሪ ምክንያት እንቅልፍን ሊነሳ ይችላል፡፡
በዚህ ምክንያት ድብርት፣ የውጤት መቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እጥረት እና ከመጠን በላይ መብላት፣ ጭንቀት እና እንደ ትኩረት ማጣት ያሉ ችግሮች እንዲከሰትባቸው ብሎም እንዲባባስባቸው መንገዱን ያቀናል።
ጭንቀት እና ድብርት በተራው ዝቅተኛ በራስ የመተማመን ስሜትን ይፈጥራል፤ ከማህበራዊ ግንኙነቶች መገለልን እና መራቅን ያስከትላል፤ በትምህርት ውጤት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያስከትላል። ከፎቶ ግራፍ መረጣ ጀምሮ የተሻሉ ሆኖ ለመገኜት በሚደረግ ጥረት ለጭንቀት የመጋለጥ አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ እንደውም አንድ ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ ብዙ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ተከታዮች አልያም ጓደኞች ያሏቸው ወጣቶች በሁሉም ነገር ምርጥ ሆነው ለመታየት ስለሚፈልጉ በስፋት ለጭንቀት የተጋለጡ ናቸው፡፡
ማህበራዊ የትስስር ገጾች እጅግ በጣም ብዙ የግል መረጃዎችን ይሰበስባሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ወጣቶች እነዚህ የግል መረጃዎች እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ፣ እንደሚከማቹ ወይም እንደሚጋሩ ሳይረዱ ይጠቀሙ ባቸዋል፡፡ ይህም ለስርቆት፣ ለመሳደድ እና ለሌሎች አደጋዎች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።
በመስመር ላይ የተጋራ መረጃ፣ ቢሰረዝም አንዳንድ ጊዜ ሊመለስ ወይም በሌሎች ቅርጾች ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህም የወደ ፊት ዕድሎችን ሊጎዳ ይችላል (ለምሳሌ፣ የኮሌጅ መግቢያ፣ የስራ ስምሪት እና የመሳሰሉትን)።
እንዲሁም ወጣቶችን ለባእዳን ባህሎች ወረራ በማጋለጥ፤የፖርኖግራፊ ፊልሞችን እና እንቅስቃሴዎችን ያስፋፋሉ፡፡ ተጠቃሚዎች አላስፈላጊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ በማድረግ የስራ ጊዜን ያባክናሉ፡፡ የመማር ማስተማር ሂደትን ያስተጓጉላሉ፡፡ አሉታዊ ግንኙነቶችን፣ የማጭበረበር እና የሽብር እንቅስቃሴዎችን ያስፋፋሉ፡፡
ያገርን በጎ ገጽታ ጥላሸት ይቀባሉ፤ስም የማጥፋት ዘመቻዎችን ያስፋፋሉ፤በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሚፈጠሩ ስሕተቶች በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ፈጣን አሉታዊ ግብረ- መልስ ለመሰንዘር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ፤ የቅጅ መብቶችን ይጻረራሉ፤ ከቤተሰብ መነጠልን እና ብቸኝነትን ያመጣሉ ወይም ያስፋፋሉ፡፡ አፍራሽ አመለካከቶችን ያሰርጻሉ፡፡ በተጨማሪም ማህበራዊ የትስስር ገጾች ማንነትን ደብቆ ለመስራት በማስቻላቸው የመረጃ ምንጮችን ትክክለኛነት፣ ማንነት እና ተዓማኒነት በቀላሉ ለማረጋገጥ አያስችሉም።
ሕዝቡ እንዲረበሽ፣ መተማመን እንዳይኖር፣ አመጽ እንዲቀሰቀስ፣ የሰዉ ልጅ ሕይዎት እንዲጠፋ እና የንብረት ውድመት እንዲከሰት ምክንያት ይሆናሉ።
እናም ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለማስቀረት ባጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። የማህበራዊ የትስስር ገጾችን የመጠቀም ሱስን ከመከላከል ጀምሮ የአእምሮ ጤና ግንዛቤን እስከ ማስተዋወቅ እና የሳይበር ጉልበተኝነትን ለመዋጋት ወላጆች እና አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን በመደገፍ ረገድ ወሳኝ ሚና መጫዎት ይኖርባቸዋል። ግልጽ ግንኙነትን በማዳበር፣ ስሜታዊ ድጋፍን በመስጠት እና ጤናማ ልምዶችን በማበረታታት፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ለአእምሮ ደኅንነታቸው ቅድሚያ እየሰጡ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ውስብስብ ባህርያትን እንዲገነዘቡ መርዳት ያሻል፡፡ ወጣቶች፣ ወላጆች፣ አስተማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች… እነዚህን ችግሮች እንዲገነዘቡ እና ከማህበራዊ የብዙኃን መገናኛ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚመጡ አደጋዎችን ለመቀነስ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ማድረግ ወሳኝ ነው።
ባጠቃላይ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ጥቅሞች ለመጨመር እና ጉዳቶችን ለመቀነስ ግንዛቤን ማሳደግ እና ኃላፊነት የሚሰማው አጠቃቀምን መከተል ያስፈልጋል።
የክቴ የቆየ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት 2ኛ ዲግሪ ተማሪ
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም