ወጣቶች እና ሰላም

0
51

ሰላም የማንኛውም ሀገር መሠረት ነው:: ያለ ሰላም ልማት፣ ዕድገት እና መረጋጋት ማምጣት አይቻልም:: በዚህ ረገድ ወጣቶች የሀገርን ሰላም በመጠበቅና ማጠናከር ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው::

ወጣቶች በኃይል፣ በፈጠራና በእውቀት የተሞሉ ሲሆኑ፣ ማኅበረሰብን ወደ አዎንታዊ አቅጣጫ ለመመራት ትልቅ ችሎታ ይኖራቸዋል:: በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በትምህርት ተቋማት እና በማኅበረሰብ መድረኮች ላይ የፍቅር፣ የአንድነትና የመተባበር መልእክት በማስፋፋት ሰላምን እንደሚያጠናክሩ የተባበሩት መንግሥታት ዲቨሎፕመንት ፕሮግራም ላይ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል::

በማኅበረሰብ ውስጥ ግጭት ሲነሳ ወጣቶች በውይይትና በመግባባት መንገድ መፍትሄ ለመፈለግ እንዲሞክሩ ማድረግ ትልቅ ውጤት ያስገኛል:: ከአመፅና ከጥላቻ እንዲርቁ ማድረግ ሌሎችንም ወደ ሰላማዊ መንገድ እነዲመጡ ይጋብዛል:: ይህም በሀገር መረጋጋት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል::

በተጨማሪም ወጣቶችን በትምህርት ማሳደግ አስፈላጊ ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል:: ስለ መብት፣ ስለ ዴሞክራሲና ስለ ሰላም በመማር እና በማስተማር ግጭትን የሚያስከትሉ አመለካከቶችን ያስወግዳሉ:: በበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች ውስጥ መሳተፋቸውም  ኃላፊነት እንዲሰማቸው ያደርጋል::  የማኅበረሰብ ድጋፍና የልማት ሥራዎች በመሥራት መተማመንን ያጠናክራሉ፣ ፍቅርን ያስፋፋሉ::

በዘመናችን የሰላም ግንባታ ከመንግሥታት ብቻ የሚጠበቅ አይደለም:: በተለይ ወጣቶች በግጭት መከላከል፣ በእርቅና በመረጋጋት ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው:: የተለያዩ ሀገራት ልምድም ይህንን በግልፅ ያሳያል::

ለአብነትም በጎርጎሮሳዊያኑ 1994  ከባድ የዘር ጭፍጨፋ ያስተናገደችው ሩዋንዳ ግጭት ውስጥ የነበሩ የሁቱ እና ቱትሲ ማሕበረሰቦች በእርቅና በማቀራረብ ሂደት ውስጥ ወጣቶችን በስፋት አካታለች:: በዚህም ወጣቶች በሰላም ክለቦች፣ በማሕበራዊ ፕሮግራሞችና በየአካባቢው የእርቅ ሥራዎች በመሳተፋቸው ታሪካዊ ቁስሎችን ለመፈወስ ረድተዋል:: ዛሬ ሩዋንዳ ከአፍሪካ የተረጋጉ ሀገራት መካከል መገኘቷ ይህንን ሚና ያረጋግጣል::

ሴራሊዮን ከ1991 እስከ 2002 (እ.አ.አ) ድረስ የቆየ የእርስ በርስ ጦርነት ከተፈጸመ በኋላ ወጣቶቿን  በሰላም ሂደቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጋለች:: ውጤቱም የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማሕበረሰቡ እንዲመለሱ በሥራና በትምህርት እንዲሳተፉ በማድረጓ ሀገሪቱን ወደ መረጋጋት እንድትመለስ አግዟታል::

በላቲን አሜሪካ የምትገኘው ኮሎምቢያም ለበርካታ ዘመን የቆየ የውስጥ ግጭት አሳልፋ ነበር:: እ.አ.አ በ2016  የተፈረመው የሰላም ስምምነት ውጤታማ እንዲሆን ወጣቶቿ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል:: በማሕበራዊ ሚዲያ፣ በሰላም ዘመቻዎችና በሕብረተሰብ ሥራዎች በመሳተፍ የሰላም ሂደቱን አጠናክረዋል::

ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ (Apartheid) ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር  እንድትመጣ ያስቻላት ወጣቶቿ በሰላማዊ ሰልፎችና በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ስለነበሩ ነው:: የእነሱ ትጋት በሀገሪቱ የዴሞክራሲ መሠረትን ለማጠናከር አግዟል::

ከእነዚህ ሀገራት ልምድ የምንማረው ወጣቶች ሲካተቱ ሰላም ይጸናል፤ ትምህርትና ሥራ ግጭትን ይቀንሳሉ፤ውይይትና እርቅ መፍትሄ ያመጣሉ፤ መንግሥታት ወጣቶችን ሲደግፉ ውጤት ይገኛል:: የዓለም ልምድ በግልፅ የሚሳየውም ይህንኑ ነው::  ወጣቶች ተመልካቾች ሳይሆኑ የሰላም ገንቢዎች ናቸው:: እነሱ ሲታመኑ፣ ሲሰለጥኑና ሲደገፉ ሀገራት ከግጭት ወደ መረጋጋት መሻገር ይችላሉ:: ስለዚህ የወጣቶችን ተሳትፎ ማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መሠረታዊ መንገድ ነው::

ከሰሞኑም የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮም በሰላም ግንባታ ዙሪያ “የወጣቶች ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ መልእክት ክልላዊ  የወጣቶች ኮንፈረንስ በባሕር ዳር አካሂዷል::

የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ  ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ኮንፈረንሱ ላይ እንደተናገሩት ወጣቶች ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና የፈጠራ አቅማቸውን ለሀገር ግንባታ ካላዋሉ በስተቀር የሚታለመውን እድገት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት ለማምጣት እንደሚያስቸግር ነው የተናገሩት::

አሁን ላይ ወጣቶች የሰላምን አስፈላጊነት በመገንዘብ  የሰላም እሴቶችን በትምህርት ቤት፣ በማኅበረሰብ እና በሚዲያ በማስተላለፍ የሰላም በር ከፋች እንዲኾኑም ጠይቀዋል:: በአመፅና ጥላቻ ጎራ የቆሙትን አቻዎቻቸውን መክረው መመለስ፣ ውይይትና መተባበርን መምረጥ እና መልካም ምሳሌ መኾን እንደሚገባም አስገንዝበዋል:: ወጣቶች በሰላም ግንባታ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ብቻ ሳይኾን ባለቤት ሊሆኑም እንደሚገባ ነው የጠቆሙት::

የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎችም  በሀገሪቱ የቆዩ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ የእርቅ እሴቶችን ለወጣቱ በማሳወቅ እና በማጋራት በሰላም ሂደቶች ተሳታፊ እንዲያደርጓቸው አሳስበዋል:: የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደጀኔ ልመንህ በበኩላቸው ባለፋ  ጥቂት ዓመታት  በክልሉ ፀጥታ መደፍረስ ያልተጎዳ የኅብረተሰብ ክፍል እንደሌለ ጠቁመው የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ወንድምና እህቶችን አቅም የሚያጎለብቱ ሥልጠናዎችን እና በዘላቂነት የማቋቋም ተግባር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል:: ኃላፊው በክልሉ ሙሉ በሙሉ ሰላም እንዲመጣ ከመንግሥት ባሻገር ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ተፎካካሪ ፖርቲዎች እና ሚዲያዎች ሰፊ ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባም ነው የጠቀሱት::

በአጠቃላይ ወጣቶች የሰላም ዋና መሠረት ናቸው:: በአመለካከታቸው፣ በተግባራቸውና በኃላፊነታቸው ሀገርን ወደ ዘላቂ ሰላም መምራት ይችላሉ::  ስለዚህ ወጣቶችን ማበረታታትና ማጎልበት ለሰላማዊ ኢትዮጵያ መገንባት አስፈላጊ ነው::

 

መረጃ

*ግማሹ የዓለም ሕዝብ ከ30 ዓመት በታች ሲሆን እ.አ.አ በ2030 መጨረሻ ወደ 57 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል::

*በአፍሪካ ከጠቅላላው ሕዝብ 60 በመቶ እድሜው ከ 25 በታች ነው:: ይህም በዓለም ላይ በዕድሜ ትንሽ ሕዝብ ያለበት አህጉር ያደርገዋል::

*በሰላማዊ ድርድር እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ የወጣቶችን  ድምጽ ማካተት ተገቢ ነው::

*ታሪካዊ እውቀትን ለማስተላለፍ እና በትውልዶች መካከል ድልድይ ለመገንባት ወጣቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው::

*ለወጣቶች ሀሳባቸውን የሚገልጹበት እና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር የሚገናኙበት መድረኮችን ማመቻቸት ይገባል::

*ወጣቶች፣ ሰላም እና ደኅንነት የማይነጣጠሉ ናቸው:: ወጣቶች ሲገለሉ እና እድሎችን ሲከለከሉ ማሕበረሰቦች ለግጭት እና አለመረጋጋት የበለጠ ተጋላጭ ይሆናሉ:: በአንፃሩ ወጣቶች ስልጣን ሲይዙ እና ኃላፊነት ሲሰጣቸው ዋና የሰላም እና የእድገት አንቀሳቃሾች ይሆናሉ::

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here