ወፍ ዋሻ 

0
62

ወፍ ዋሻ ጥብቅ የተፈጥሮ ደን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር፣ ባሶና ወረና እና አንኮበር ወረዳዎች ይገኛል።

16 ሺህ 925 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት የቆዳ ስፋት አለው። ደኑ በውስጡ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ ብርቅዬ አእዋፍት እና እፅዋት የያዘ ነው። በዓለም በየትኛውም ስፍራ የማትገኘው “አንኮበር ሴረን” ወፍ በዚሁ ደን ውስጥ ብቻ የምትታይ ናት።

ከዱር እንስሳት ለጭላዳ ዝንጀሮ፣ ለምኒልክ ድኩላ እና ለወርቃማው ቀይ ቀበሮ መጠለያ የሆነው የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኘውን ግዙፉን ጅብራ ጨምሮ የበርካታ አገር በቀል እፅዋት መገኛም ነው።

በጣርማ በር ወረዳ የሚገኘውን የወፍ ዋሻ ደን፤ ከደብረ ሲና ከተማ 14 ኪሎሜትር በመኪና ከተጓዙ በኋላ ማራኪውን መልከዓ ምድር አየተመለከቱ የሁለት ሰዓት የእግር መንገድ ተጉዘው ያገኙታል።

 

የወፍ ዋሻ ደን ምዕራባዊ ክፍል ገደላማ፤ ምስራቃዊው ደግሞ ወጣገባ እና ሸለቆ የበዛበት ነው። የተራራ ሰንሰለቱ ደግሞ ከደቡብ ምስራቅ ወደ ሰሜን ምዕራብ የተዘረጋ ሆኖ እስከ አዋሽ ተፋሰስ ድረስ ይዘልቃል።

የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ከባህር ወለል በላይ ከሁለት ሺህ እስከ 3700 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል። የአየር ንብረቱ ወይና ደጋ እና ደጋ ሲሆን የመሬት አቀማመጡ ወጣገባ የበዛበት ነው።

 

የአማራ ክልል ቱሪስት መስህብ መፅሔት እንደሚያመለክተው የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደን ከዐፄ ዘርዓያዕቆብ ዘመን ጀምሮ እንደነበር እና በ18ኛው ክፍለዘመን ደጃዝማች አምሃ ኢየሱስ (ከ1744 እስከ 1775) በአንኮበር የሸዋ መናገሻን በመመስረት ለደኑ ለደኑ ጥበቃ በተሰጠው ትኩረት በስፋት የደኑን ማዕከላዊ ክፍል ሸፍኖ የሚገኘውን የሃበሻ ፅድ እሳቸው እንዳስተከሉት ይገለፃል።

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here