ይማርልኝ ብዬ ዋሸራ ሰድጄ፣
ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ልጄ::
ይህን ቅኔ የተቀኘችው ልጇን ለቅኔ ትምህርት ዋሸራ ልካ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት አደጋ ከጎጆው ጋር በቃጠሎ የሞተባት እናት ናት::
ቅኔ ማለት ማስታወቅ፣ መተረክ ወይም ሁለመናውን መንገር ማለት ነው:: በቅኔ ታሪክ ይተረካል:: ተጋድሎ ይነገራል:: ምስጋና ይቀርባል:: አገልግሎቱም በዋናነት መንፈሣዊ ነው:: በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን መንፈሣዊ አገልግሎት መሃል እየገባ ይነገራል:: ጥቅሙም ብዙ ነው:: ነገር ግን ግዕዝን ማወቅ ይጠይቃል:: ቅኔ የአዕምሮ ማደሻ፣ የምሥጢር ዋሻ፣ የዕውቀት ማጎልመሻ ናት ሲሉ ሊቃውንት ይገልጻሉ::
ቅኔን የጀመረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ ነው:: በኋላ መልክ አስይዞ በትምህርት ቤት ማስተማር የጀመረው ደግሞ ድህሪም ነው በማልት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ቤተ ክርስቲያን የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ትምህርት ስልጠና ክፍል ኃላፊ መላከጥበብ ስሜነህ አበበ ይናገራሉ። ጊዜውም በአንበሳ ውድም ዘመነ መንግሥት ከ882 እስከ 902 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር ሲሉ መጋቢ ምሥጢር ስማቸው ንጋቱ “ማዕዶት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ያትታሉ:: ድህሪም የተወለደው ጎጃም ደጋ ዳሞት ነው። ድህሪም በአንበሳ ውድም ዘመነ መንግሥት በደጋማው ጎጃም እየተዘዋወረ ወንጌል ይሰብክ ነበር። ድህሪም የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ዕውቀት ያለው ሰባኪ ወንጌል ነበር።
መጋቢ ምሥጢር ስማቸው አክለውም “ድህሪም የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ነው። ከአማራው ነገድ ይወለዳል። ከአማርኛ በተጨማሪም በጊዜው በጎጃም ይነገሩ የነበሩትን ጋፋትኛ፣ ግዕዝ፣ እንዲሁም አገውኛ አቀላጥፎ ይናገር ነበር” ይላሉ። ድህሪም ጻድቅ እና የበቃ ሰው ስለነበር የአካባቢው ሕዝብ በሚናገረው ቋንቋ እየተዘዋወረ ሲያስተምር ትንቢት ይናገራልም።
ወንጌላዊው ድህሪም ሕዝቡን ለማስተማር ከሰከላ ተነስቶ በዳባ ተራራ ላይ ወደ ዋሸራ ሲወርድ ቆሞ አካባቢውን ተመለከተ። ተራራው በደን የተሸፈነ ነበር እና በዱሩ ውስጥ ለውስጥ ሲሄድ ቁራ ገደል እየተባለ በሚጠራው ተራራ አንድ ዋሻ አገኘ። የእግዚአብሄርም መንፈስ መጥቶ በዋሻው ውስጥ ሱባኤ እንዲገባ ነገረው። በጥንት ጊዜ ዋሻው የራጉኤል ዋሻ እየተባለ ይጠራ ነበር። አሁን ሕዝቡ ቁራ ገደል እያለ ይጠራዋል። የዋሸራ ካህናት ግን የራጉኤል ዋሻ በሚለው ስም ይጠሩታል በማለት መጋቢ ምሥጢር ስማቸው አትተዋል።
ድህሪም በዋሻው ውስጥ በሱባኤ ሳለ ቅኔ ተገለጸለት። በዋሻው ውስጥ በሱባኤ እያለ ሁለት ደቀ መዛሙርት አብረውት ነበሩ። ዘርእየ እና ነጸረ ይባላሉ። በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸለትን ቅኔም ለሁለቱ ደቀ መዛሙርት አስተማረ። ቅኔም መቀኘት ጀመሩ። ነጸረ ጉባኤ መስርቶ ቅኔ ስለማስተማሩ መረጃ የለም። ዘርእየ ግን ከድህሪም ያገኘውን ዕውቀት አስቀጥሎ በዋሸራ ቅኔ አንድም ጊዜ ሳይቋረጥ ከእኛ ዘመን ደርሷል። ከ900 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ለ1117 ዓመት ያህል በዋሸራ ቅኔ ምንም ሳይቋረጥ ቆይቷል በማለት መጋቢ ምሥጢር ስማቸው ጽፈዋል።
ዋሸራ ማርያም ገዳም በምዕራብ ጎጃም ጎንጅ ቆለላ ወረዳ የምትገኝ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሠረተችው ቁራ ገደል ከሚባል ቦታ በ900 ዓ.ም በጃን ስዩም ዘመነ መንግሥት ነው:: ቅኔ ለመጀመሪያ ጊዜ በእዝራ ስቱየል /ድህሪም/ የተመሠረተው በዚህ ቦታ ነው::
“ዋሸራ” የሚለው ቃል ሲጠራ በእያንዳንዱ ሰው አዕምሮ ድቅን የሚለው የቅኔ መዝረፊያ /መፍለቂያ/ ሥፍራ መሆኑ ነው:: ዋሸራ የሚለው ቃል የት መጤነት ሲመረመርም የተለያዩ እሳቤዎች አሉት:: ታዲያ አብዛኛውን የሚያስማማው ግን አንድ ንጉሥ በአንድ ወቅት ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብሎ ጦሩን አሰልፎ ይጓዛል:: ከሠራዊቱ ጋር ዋሸራ ደርሶ ለመስፈር ሲሞክር አባቶች “ቢቀርብህ ይሻላል“ ቢሉት ሀሳባቸውን ችላ ብሎ ሰፈረ:: ድንኳንም ተከለ:: ነገር ግን አውሎ ነፋስ መጣ እና ሰፈሩን በታትኖ ድንኳኑን ነቃቅሎ ዘማ ወንዝ አውርዶ ጣለው:: ንጉሡም የንብረቱ መውደም ስላሳዘነው ድንኳኑም ሸራ ስለነበር “ዋሸራ” ብሎ ተናገረ:: “ዋ! ሸራዬ” እንዲህ ሆኖ ቀረ ማለቱ ነው:: አንዳንድ አባቶች ደግሞ ዋሸራ የሚለው ስያሜ ዋሻ ራጉኤል ከሚለው የመጣ ነው ብለው ያምናሉ::
በጥምቀት ደምቆ ወጥቶ የተቀጣጠረ መገናኛው የአስተርእዮ ማርያም ዕለት ነው። አስተርእዮ ማርያም በደማቅ ሁኔታ ከሚከበርባቸው ታሪካዊ ቦታዎች መካከል ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም ተጠቃሽ ናት። አስተርእዮ ማርያም በደብረ ምዕራፍ ዋሸራ በብዙ መልኩ ይለያል። በርካታ ሊቃውንት በደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ይከትማሉ። የቅኔ ምንጩ እዚያው ነውና በሊቃውንት ዜማ እና ዝማሜ ታጅቦ የቅኔ ጥበብ እና ምስጢር ይጎርፍበታል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሰብስበው ቅኔን ሲያመሰጥሩ የከረሙ የዋሸራ የአብነት ተማሪዎች ከመምህራን እና ሊቃውንት ጎን ቆመው የቀሰሙትን ቅኔ ለታዳሚው ይቀኛሉ።
ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ ማርያም የመጀመሪያው የቅኔ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ናት። መገኛዋም ጎጃም ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ውስጥ ነው። ከአዲስ አበባ በ426 ኪሎ ሜትር፣ ከባሕር ዳር ደግሞ በ82 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ የቅኔ ማሕደር ናት። የጎንጅ ቆለላ ወረዳ ቤተ ክህነት መረጃ እንደሚያመለክተው ገዳሟ የተመሠረተችው አሁን ካለችበት ቦታ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት “ቁራ ገደል” በተባለ ቦታ ላይ ነበር። የአሁኗ ደብር ደግሞ አባ ተስፋ ማርያም የሚባሉ አባት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በ1427 ዓ.ም ነው የመሠረቷት።
በዋሸራ ድንጋዩን ቢፈነቅሉት፣ እንጨቱን ቢቆርጡት፣ ውኃውን ቢጠጡት፣ ሳሩን ቢያጭዱት ቅኔ ይዘርፋል ይባላል:: “እነ አለቃ ተክሌ፣ እነ መምህር ቀስሙ፣ እነ አለቃ ደሌ እና ሌሎች ሊቃውንት ሲያስተምሩ የሰማ የጽድ ዛፍ እንኳ ሰዋሰው ይገባዋል” ተብሎም ይነገርላታል- ዋሸራ::
ዋሸራ የሚለውን ቃል በተለያዩ የሀገራችን የጥበብ ሥራዎች ላይ እናውቀዋለን። ከድህሪም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ231 በላይ ሊቃውንት ወንበር ተክለው የቅኔን አመስጥሮ አስተምረዋል። ተተኪ ሊቃውንት ቤተ ክርስቲያንንም አፍርተውበታል። ከዋሸራ የወጡ የቅኔ ሊቃውንትም ወደየአካባቢው በመሄድ ቅኔን አስፋፍተዋል።
ለአብነትም የዋሸራ ፍሬ የሆኑት መምህር ተክለ አብ ያፈሩት ተዋናይ ወደ ጎንጅ ቴዎድሮስ ገዳም ሄዶ ቅኔን በስፋት አስተምሯል። ከብዙ ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ ወደ ሀገራቸው ገብተው ያረፉት አቡነ መርቆርዮስ ፖትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንት በጎንጅ ቴዎድሮስ ገዳም የተማሩ ሲሆን የቅኔ ሊቅነታቸው ከተዋናይ እና ከዋሸራ ጋር የተሰናሰለ ነው።
በዋሸራ አሁንም ቢሆን ከአብነት ተማሪዎች ደሳሳ ጎጆ ምርፋቅ ጥበብ ከጥሩው ይቀዳል። በነተዋናይ ቅኔ እየተዋዛ እንደ ጅረትም ይፈሳል። ዋሸራ የሀገር አንጡራ ሀብት የሆነውን ቅኔ ከደሳሳ ጎጆዎች አውጥታ ከፍ ባለ ሰገነት ላይ ለመሾም ከነችግሮቿም ቢሆን እየታተረች ነበር። በባሕር ዳር፣ ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ እና መተከል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሲኖዶሱ አባል አቡነ አብርሃም የበኩር የሆነ ዘመናዊ የቅኔ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት በ2009 ዓ.ም የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠው ነበር። የተጀመረው የቅኔ ማዕከል ሕንፃ ሲጠናቀቅ የአብነት ተማሪዎች ለቁራሽ እንጀራ የሰው ደጅ ሳያዩ ሁሉንም ነገር እዚያው እንዲያገኙ ይደረጋል ተብሎ ቢታሰብም በወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች እና በበጀት እጥረት ሳቢያ ግንባታው አልቀጠለም።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት “የቅኔ ዩኒቨርሲቲ” የሚል ማዕረግ የተሰጣት ደብረ ምዕራፍ ዋሸራ የወደፊቷ የቱሪዝም ሙሽራ እንድትሆን የተለያዩ አካላትን በጎ ርብርብ ትሻለች። የሀገር ሩቅ ታሪክ ተከትቦ የተያዘበት ቅኔ እንዲልቅ ተጀምሮ የቆመው ቅኔ ዩኒቨርሲቲ አጠናቅቆ ከደሳሳ ጎጆ መውጣት ያስፈልጋል። ዋሸራ በቅኔ ቀደምትነቱ የተነሳ በመንፈሳዊ ዓለም ብቻ ሳይሆን በስጋዊ የጥበብ ዓለም ጭምር በዘፈንም በስነጽሑፍም ተደጋግሞ የሚወሳ ነው። መልክዓ ምድራዊ ገጽታውም ለቱሪዝም መዳረሻነት በእጅጉ ተስማሚ ነው። የዋሸራ የበግ ዝርያም ኢትዮጵያ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ዝርያዎች አንዱ ነው።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የነሐሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም