ውሎህ ከማን ጋር ነው?

0
188

“ባርዬ  ይህቺ  ልጅ እኮ ትወድሃለች፤ አብራችሁ እየተቀመጣችሁ ለምን አትጠብሳትም?” ጓደኛዬ ባሪያው ነበር ሚለኝ። የምወደው ባዮሎጂ መምህሬ ነበር ስሙን ያወጣልኝ። በወቅቱ 11ኛ ክፍል ነበርሁ። ጓደኛዬ አንድ ክፍል፤ አንድ ወንበር አብራኝ የምትቀመጠውን ቆንጆ  ልጅ ነበር እንድጠብሳት የጋበዘኝ። እሱ ጓደኛዋን ጠብሷል። እሱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ቢሆንም እንኳን እኔ ከምማርበት ማህበራዊ ሳይንስ 11ኛ ኤ ክፍል በረፍት ሰዓት ይመጣል። ጥሩ ወዳጆች ነን። በየጊዜው እየተገናኘን እናወራለን፤ ምስጢር እንጋራለን። ልጅቱ ጋር አብረን እንቀመጣለን፤ ጥሩ ወዳጅነት አለን። ምንም የፍቅር ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር። “ተው ባክህ እኔ ትምህርቴን ነው መማር ምፈልገው፤ ትቅርብኝ” አልሁት። ቀለል አድርጎ ዝም አለኝ።

ከቀናት በኋላ ክፍል ስትገባ ሳያት ማፈር ጀመርሁ፤ ከሰዓት ከክላስ ስትቀር ይጨንቀኝ ጀመር። ቀይ ናት፤ ፈገግታዋ፤ ርጋታዋ፤ የምትቀባው ቅባት፤ ሰላም ስትለኝ እጇ መለስለሱ… በቃ ፎንቃዋ ገብቶልኛል። በውል ያላስተዋልሁት ውበት ለካንስ ከጎኔ አብሮኝ ተቀምጦ ይውል ኖሯል። በጣም ወደድኋት። ጓደኛዬ ሳቀብኝ። እንደቀልድ የለኮሰብኝ የፍቅር እሳት ውስጤን እያነደደው ነበር። ደብዳቤ ጽፌ አንተ ስጣት አልሁት። ሰጣት። “እንደ ወንድሜ ነበር ማየው፤ ከእሱ ይሄን አልጠብቅም ነበር” ብላ መልሱን ላከችብኝ። ብዙ ነገሬ ተዛባ።

የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ከክፍል ሦስተኛ ደረጃ ወጣሁ። በሁለተኛው መንፈቅ ደግሞ 11ኛ ደረጃ ላይ ተገኘሁ። 10ኛ ደረጃ የወጣው ልጅ በእኔ ቦታ ተተክቷል። ለካንስ ደብተሩን ብገልጠውም እያነበብሁ አልነበረም። ውስጤን ፍቅር ይሉት ስሜት ሰልቦት ኖሯል። ጓደኛዬ ሊያግባባን ሞክሮ አልተሳካም። እሱ ጋር መራራቅ ጀመርን። ክፍል ውስጥ ሌሎች ጓደኞች አፈራሁ። አማን የምለው ጓደኛዬ ጋር አብረን ባከል ገብርኤል ለምለም መስክ ሄደን በማንበብ አብረን እንውል ነበር። በተለይ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ እየመከረኝ እናጠና ነበር። የሰኔ ወር ውጤት እንደዚህ መውረድ ከእኔ ይልቅ  ያበሳጨው   እሱን   ነበር። ክረምቱ አልፎ መስከረም 12ኛ ክፍል ስንገባ “ስማ ዘንድሮም እንዘላዘላለሁ ብትል አንተ ጋር ግንኙነቴን አቆማለሁ፤ በቃ ተዋት አትረባም፤ ባለጌ ናት፤ ወንድ ጋር በተደጋጋሚ አይቻታለሁ፤ ዩንቨርሲቲ የሚማር ፍቅረኛ አላት” እያለ እንድተዋት መከረኝ። እንዲቆርጥልኝ፤ እንድጠላት ያልሰደባት ቃል፤ ያላንቋሸሸበት መጠን አልነበረም። ልክ ነህ እለውና ተመልሼ እሷን በማሰብ እጠመዳለሁ። አማን ስፖርት መስራትን ባህሉ ያደረገ ልጅ ነው። እኔንም ስፖርት መስራት አለማመደኝ። ጡንቻዬ ጨመረ። መንቀባረር ጀመርሁ። በራስ መተማመኔ ሲያድግ ይታወቀኝ ነበር። ክብደት ስለማነሳ ሰውነቴ ሁሉ ቀለለኝ። የድብርት ስሜት ወጣልኝ። (የዘንድሮ ሴት ባሉን ፈትቶ ጂም ቤት ሚሄደው ለካ ያለ ምክንያት አይደለም።)

ልጅቱ ጋር አንድ ክፍል አብረን መማራችን ፍቅሬን ክፉኛ ውስብስብ አድርጎታል። ጠዋት፣ ቀን እና ከሰዓት አያታለሁ። አማን ክፍል ውስጥ መኖሩ እሷን በማየት እንዳልወሰድ ብዙ ረድቶኛል። ወደ ጥናት እና ስፖርት ስራችን በስፋት ገባን። ሙዚቃ መስማትህን ቀንስ አለኝ። እሷን እንዳላስታውስ መሆኑ ነው። ያለኝን ነገር መስማት ጀመርሁ። 12ኛ ክፍል ሁለቱንም መንፈቅ ዓመታት 3ኛ ደረጃ በመሆን፤ ውጤቴንም በማሻሻል አጠናቀቅሁ።

በተደጋጋሚ ስለ አቻ ግፊት አሉታዊነት ሰምተናል። “ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር እንትን ተምራ ትመጣለች” ከሚለው ጀምሮ ጓደኛ በሕይወት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ ልብ እንድንልን ተደርገናል። “ጓደኛህን ንገረኝ እና ማንነትህን እነግርሃለሁ” ስንባልም አድገናል። ጓደኞቻችን ሊጠቅሙንም ሊጎዱንም ይችላሉ። አንደኛው ያላሰብኋትን ልጅ ትወድሃለች ብሎ ከመንገድ አዘግይቶኛል፤ ሌላኛው ደግሞ መንገዴን በተነቃቃ ጉልበት እንድቀጥል ረድቶኛል።

በእኔ ልክ ፈሪ ሰው አልነበረም። ሲበዛ ዓይነ ሰባራ እና አቀርቅሬ የምሄድ ነበርሁ። በትምህርት ቤታችን ሚኒሚዲያ መስራት እየፈለግሁ ሦስት ዓመታትን ለመጠየቅ፤ ለመቅረብ ፈርቼ ቆይቻለሁ። 11ኛ ክፍል ስገባ ሸዊት የሚባል ጓደኛዬ የፍርሀት ቆፈኔን አውልቆልኛል። መድረክ ላይ ድራማ የምሰራ፤ ሚኒ ሚዲያ የራሴን ጽሑፍ ትረካ ማቀርብ፤ የትምህርት ቤት ሙዚቃ ውድድር ምሳተፍ ሰው ያደረገኝ ሸዊት ነው። ሸዊትን ባላገኝ ኖሮ በዚህ ሙያ ውስጥ አልገኝም ነበር። እንድደፋፈር፤ እንዳውቅ፤ እንድሞክር ዕድል ሰጥቶኛል።

የሰው ልጅ ማህበራዊ ተፈጥሮ በተፅእኖ ውስጥ እንዲያልፍ ያስገድደዋል። የሰው ልጅ ሐሳቦች፣ ስሜቶች፣ ባሕሪዎች የሚያደርሱበትን አሉታዊ እና አዎንታዊ ጫና ተቋቁሞ የግል መንገድና ግቡን ሳይለቅ ለመድረስ ብዙ ፈተናዎችን ይጋፈጣል። እነዚህ ፈተናዎች እና መንገዶች ማንነቱን ይሰሩታል። ኤልዛቤት ሀርትኒ ቬሪ ዌል ማይንድ ድረገጽ ላይ ባሰፈረችው ሐተታ “ወላጆች ብዙውን ጊዜ ልጆቻቸው የሚውሉበትን እና ጓደኞቻቸውን በመከታተል ጊዜ ያጠፋሉ። እነሱ በልጆቻቸው ላይ ያላቸውን ጫና ግን አይገነዘቡም” ትላለች። በዚህም “ወላጆች የሚያደርጉትን ያያሉ፤ የሚያወሩትን ይሰማሉ። የወላጅ ተፅዕኖ በልጅ ላይ ከፍተኛ ነው” በማለት ትቀጥላለች።

በፔንሲልቫኒያ ዩንቨርሲቲ ዶክተር ኤምሊ ፋልክ የሰዎች ማሕበራዊ ትስስር በውሳኔ ላይ ያለውን ጫና አጥንታለች። በዚህም ታዳጊ ልጆች የበለጠ ለአቻ ግፊት ተጋላጭ መሆናቸውን ትናገራለች። አዕምሯቸው በፈጣን አስተውሎት ውስጥ ስለሚያልፍና ለነገሮች ልዩ ትኩረት ስለሚሰጥ  ነውም ትላለች። በሚያዩት፣ በሚሰሙት፣ በሚደረጉ ማህበራዊ ክዋኔዎች የበለጠ ይሳባሉ። ነገሮችን ለማየት ዝግጁ ይሆናሉ።

አሜሪካዊው የስራ እና  ስኬት አሰልጣኙ እንዲሁም ተመራማሪው ጂም ሮን “አሁን ያለህ ማንነት እንዴት እንደተገነባ ማወቅ ምትፈልግ ከሆነ፤ በቅርብህ የነበሩ ሰዎች እና ሐሳቦች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ” ይላል። “በዙሪያህ አምስት ሰዎች ካሉ አንተ የእነሱ ውጤት ነህ” በሚለው ሐሳቡም በስፋት ይታወቃል። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በእኛነታችን ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ችላ ልንለው አይገባም። አካባቢያችን እንዴት እንደሚገነባን በሚገባ አልተገነዘብንም የሚለው ሮን “ገንዘብ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር የምትውሉ ከሆነ እናንተም ገንዘብ ትሰራላችሁ፤ ወደ ጨዋታ እና ኮንሰርቶች የሚያዘወትሩ ጋር የምትውሉ ከሆነም እንዲሁ እነሱን የመምሰል እድላችሁ ትልቅ ነው” በማለት ያብራራል። የማያነቡ ሰዎች ጋር ከዋላችሁ እናንተም አታነቡም የሚለው ጂም ሮን ሰዎች ሦስት ጥያቄዎችን ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው ይላል። “እነማን ጋር ነው ያለሁት፤ በዙሪያዬ ካሉት ሰዎች ምን ጥቅም አገኛለሁ እና እነዚህ ሰዎች ጋር መሆኔ ትክክል ነው ወይ?” በማለት መርምሩ ይለናል።

ግንኙነቶች ጎጂ ሆነው ሲገኙ ደግሞ እንዴት መፍትሔ ማምጣት እንደሚገባ ጅም ሮን ይመክራል። እነዚህ ሰዎች አልጠቀሙኝም የምትሉ ከሆነ ራሳችሁን አርቁ ይላል። በአሉታዊ ሕይወት ከመቀጠል መራራውን ጽዋ ጠጥቶ መገላገል ያስፈልጋል ይልና መነጠል ግን ቀላል እንዳልሆነ ይመክራል። በመቀጠልም ምጥን ግንኙነት ማድረግን ይመክራል። ይህም በጣም ከሚጠቅሟችሁ ሰዎች ጋር ብዙ ሰዓት፤ ትንሽ ከሚጠቅሟችሁ ሰዎች ጋር ደግሞ ውስን ሰዓትን ማሰሳለፍ ይገባል ይላል። ሮን ይቀጥልና “ሌሎች በጣም ስኬታማ ሰዎችን ፈልጉና እነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት መስርቱ፤ የስኬታቸውን ምስጢር ጠይቋቸው፤ እንዴት እንዳሳኩትም ተሞክሮ ተቀበሉ” ይላል። እነዚህ ሰዎች ስለ ጥሩ ቤተሰባቸው፤ ትዳራቸው፤ ስለ ጤንነታቸው እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው መልካም ተሞክሮን ሊነግሯችሁ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉም ይላል ጂም ሮን። ጂም ሮን ይህንን ሒደት በምክንያት ከሰዎች ጋር ሕብረት ማድረግ ይለዋል። ትክክለኛ ሰዎች ጋር በትክክለኛ ምክንያት ጓደኝነትን መመስረት የሕይወት አቅጣጫን የተቃና ያደርገዋል ይላል።

ኪሊኒካል ሳይኮሎጂስቷ  ዶክተር ማሬ የቬቲ በጓደኝነት ምርጫ ላይ እ.ኤ.አ በ2012   እና 2017 የተደረጉ ሁለት ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ትክክለኛ ጓደኛ ማለት ምንድን ነው የሚለውን ጽፋለች። በዚህም መሰረት በኀዘን እና በደስታ ከጎን የሚቆም፤ ለወዳጁ ጊዜውን የሚሰጥ፤ ማንነትህን የሚቀበል፤ እውነቱን የሚናገር፤ በአንተ የሚተማመን እና ሕልምህን እንድታሳካ የሚደግፍህ፤ ደስታህን እና ስኬትህን የሚያከብር ጥሩ ጓደኛ ነው ስትል ዘርዝራለች።

ሰዎች፤ በሚያበረቷቸው ሰዎች ዙሪያ ሲሆኑ እንደሚጠነክሩት ሁሉ በአሉታዊ ሐሳቦች ደግሞ ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ ከጉዟቸው ይዘገያሉ። የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰባዊ ስነልቦና አጥኚ ዶክተር ዴቪድ ማክሴሊላንድ “95% በመቶ የሚሆነው ስኬትህ ወይም ውድቀትህ በዙሪያህ ባሉት ሰዎች ማንነት ይወሰናል” በማለት አጥንተዋል። የሰው ልጅ የትኛውንም ያህል ጥሩ ስራ ቢሰራ ፤ በዙሪያው እና በቅርቡ ያሉት ሰዎች ጎትተው እንደሚያወርዱት የጥናት ውጤቱ ያሳያል። ወዳጅነት እና ግንኙነት ከአጋጣሚዎች ትውውቅ ይልቅ ዓላማን እና የሕይወት ግብን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ይመክራሉ። “እነሱን መሆን እፈልጋለሁ የምትሏቸውን ሰዎች ቅረቡ፤ ያለፉበትን የስኬት ልምድ እና አመለካከት ያጋቡባችኋል” ሲሉ ይመክራሉ።

ጎልስ ኮሊንግ ድረገጽ በዙሪያችሁ ማን አለ? በሚል ይዞት በወጣ ሐተታ “እንዲሳካልህ የምትፈልግ ከሆነ ከአንተ ዓላማ እና ሐሳብ ጋር ተቀራራቢ መረዳት ያላቸው ሰዎች ጋር ጊዜህን አሳልፍ ይላል። ሕልምህን እንድታሳካ ወደ ፊት ጉልበት ሆነው የሚገፋህን ሰዎች መምረጥ አለብህም ይላል። ጓደኝነት በሀገራችን ትልቅ ሚና አለው። የድሮ ትምህርት ጓደኞቻችንን አርጅተንም ቢሆን እንናፍቃለን። እናገኛለንም። ጎልስ ኮሊንግ ግን “የድሮ ነገር ሁሉ ጥሩ አይደለም። የግንኙነት እና ወዳጅነት መሰረት መሆን ያለበት የረጂም ጊዜ መተዋወቅ አይደለም፤ ይልቁንስ ዓላማ ነው” ይላል። “ከቢዮንሴ ወይም ኦፍራ ጋር ወዳጆች ብትሆኑ ምን ልታስቡ ትችላላችሁ?” ሲል የሚጠይቀው ድረገጹ ውሏችን ዛሬ ላለንበት አኗኗር መሰረቱን ስለመጣሉ ያብራራል።

ከጓደኞቻችሁ ጋር ምን በማድረግ ነው የምታሳልፉት የሚለውን ሐሳብ አጉልቶ በማንሳት፤ ወዳጅነት ምንም መልካም ቢሆን ለጭፈራ፣ ሐሜት፣ ሱስ፣ ቁማር እና ሌሎች መሰል ፍሬ አልባ ተግባራት ማድመቂያ ከሆነ አይጠቅምም ባይ ነው። ከጓደኞች ጋር ጊዜዬን የማሳልፈው ምን በማድረግ ነው የሚለው መሰረታዊ ነጥብ ነው። አዳዲስ ነገሮችን በመሞከር፣ በምርምር፣ ጉዞዎችን በማድረግ እና ራስን ለማሻሻል ሲውል ያልባከነ ጊዜ ነው። የምቾት ቀጠና እና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር መሆን ወደ ኋላ የሚጎትት ምርጫ ነው። ሁልጊዜ ነገሮችን በጥርጣሬ እና በአሉታዊ መልኩ የሚቀበሉ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች አዕምሮን ይበርዛሉና ራቋቸው ይላል። እችላለሁ ስትሏቸው ቢቀርብህ የሚሉ ሰዎችን ከዙሪያ ማራቅ ተገቢ ነው። የትኛውም ስኬታማ ሰው ሐሳብህ ቅዠት ነው ከሚለው ጓደኛው ጋር ሆኖ እንዳልተሳካለት ማሰብ ይገባል። መልካም ጓደኞች በተግባሮችህ ስትደክም፤ በችግሮች ስትደናቀፍ፤ በሐሳብህ ስትናወጥ በርታ ብለው ወደ ፊት እንድትቀጥል ወኔ የሚሰጡህ ናቸው። አሉታዊ መጠራጠር ሲገጥምህ ሕልምህ እውነት ነው፤ ይቻላል የሚሉህ መሆን አለባቸው።

በመጨረሻም ጎልስ ኮሊንግ ድረገጽ በዙሪያህ ያሉ ሰዎችን መምረጥ የአንተ ድርሻ ነው ይላል። በመጥፎ ሰዎች ዙሪያ ከሆንክ ሌሎች መልካም ጓደኝነቶችን በመመስረት አሉታዊዎችን አራግፋቸው ይላል። በሕይወትህ መልካም ውጤት እንድታመጣ በሚያግዙህ ሰዎች ራስህን መክበብ አለብህ። “የቀድሞ ጓደኞችህ መልካም ሰዎች ናቸው ማለትም ትክክለኛ ናቸው ማለት አይደለም” ይላል ጎልስ ኮሊንግ ድረገጽ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here