ውርስን ለተንከባካቢ

0
180

ጣሊያናዊቷ የ80 ዓመት አዛውንት አምስት ነጥብ አራት ሚሊዬን ዶላር የሚገመት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን የአልባኒያ ዜግነት ላላት ተንከባካቢያቸው ማውረሳቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በጣሊያን ትሬንቶ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ሮቬርቶ በተሰኘች ከተማ የማዘጋጃ ቤት ሹም እንዲሁም የቬዬና የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል ኘሬዘዳንት ወራሽ ናቸው – ማሪያ ማልፋቲ፡፡ አዛውንቷ ቀደም ብሎ የተለያዩ መኖሪያ ህንፃዎች፣ ታሪካዊ እሴት ያላቸው በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ የተገነቡ ግዙፍ ፎቅ ቤቶች እንዲሁም በርከት ያለ ገንዘብ በባንክ ሂሳብ ደብተራቸው ነበራቸው፡፡

ማሪያ ማልፋቲ አግብተው ቀጥተኛ ወራሽ ልጆች ማፍራት አልቻሉም ነበር፡፡ ይህንን የሚያውቁት የወንድሞቻቸው እና የእህቶቻቸው ልጆች የአዛውንቷን ሀብት ንብረት መውረስ እንደሚችሉ አምነው ይጠባበቁ ነበር፡፡

የልባቸውን በልባቸው፣ የፈቀዱትን በፊርማቸው ያረጋገጡት የአዛውንቷ የኑዛዜ ወረቀት ከአዛውንቷ ዕረፍት በኋላ  ውርሱ ለማን እንደሚተላለፍ ለማወቅ በጉጉት ይጠበቅ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የወንድምና የዕህት ልጆቻቸው በወራሽነታቸው ዕርግጠኛ እንደነበሩ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ጊዜው ደርሶ የማሪያ ማልፋቲ ህጋዊነት ያለው የኑዛዜ ወረቀት ሲነበብ ሙሉ በሙሉ ቋሚ ንብረታቸውምን ሆነ ተንቀሳቃሽ ገንዘባቸውን ለዓመታት ከጐናቸው ለነበረችው አልባናዊዋ ተንከባካቢ ሠራተኛቸው ማውረሳቸውን አብስሯል፡፡

የዕህትና የወንድም ልጆቹ ለተንከባካቢያቸው በኑዛዜ ማውረሳቸውን ሲረዱ ወደ ክስ አምርተው ነበር፡፡ የተከራካሪዎቹ ጠበቃ ለችሎቱ አልባናዊቷ ተንከባካቢያቸው አዛውንቷ ራሳቸውን በሳቱበት ወቅት ኑዛዜውን አስፈርማቸው ሊሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬ  እንዲታገድ ተወስኖ ነበር።  “ንጋት እና ዕውነት…” እንዲሉ  በመጨረሻ ውርሱ ለተንከባካቢያቸው መሆኑ ነው የተረጋገጠው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here