ሰላም የፍትሕ አምድ አንባቢዎቻችን! በዚህ ዕትም ስለውርስ አፈጻጸም በፍትሕ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከአቶ ስመኘው መንበሩ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚመለከተው አዘጋጅተነዋል::
የሕግ ባለሙያው እንዳብራሩት ውርስ ማለት አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ለወራሾች የሚተላለፍበት መብት እና ግዴታን የያዘ ሀብት እና እዳ ነው:: ይህ ማለት ግን አንድ ሰው በሕይወት እያለ የነበረው እና ያፈራው ሀብት እንዲሁም እዳ ሁሉ ለወረሾች ይተላለፋል ማለት አይደለም::
ውርስ መቼ ይከፈታል?
የኢትዮጵያን የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ አንድ ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ ሞተበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው ይላል:: በዚህ የሕግ ድንጋጌ መሰረት አንድ ሰው መብት የሚኖረው ከውልደቱ እስከ ሞቱ ቀን ድረስ ያለው ጊዜ ብቻ ነው:: ከሞተበት ሴኮንድ አንስቶ ግን ይህ መብቱ ይቋረጣል ማለት ነው:: በዚህ ጊዜ ንብረቱን ማስተዳደር ስለማይችል እና የነበረው መብቱ ስለተቋረጠ ንብረቱን እና መብቱን ብሎም ግዴታውን የሚያስተዳድር ሰው ግድ ይላል ማለት ነው:: ይህን መብትን እና ግዴታን የማስተዳደር ሥልጣን ደግሞ ወደ ወራሾች ይዘዋወራል ማለት ነው::
የሕግ ባለሙያው እንደሚያስረዱት ውርስ ተከፈተ የሚባለውም ሟች በሞተበት ቅጽበት በሕይወት ዘመኑ ያፈራውን ንብረት እና ሃብት የሚያስተዳድርለት ስለማይኖር እና የእርሱ መብት ስለተቋረጠ ይህ ንብረት አስተዳዳሪ እና ጠባቂ አልባ እንዳይሆን በሞተበት ቅጽበት ውርስ ተከፈተ ይባላል:: ይህን ተከትሎም ወራሾች ንብረቱን የማስተዳደር ሥራ ይጀምራሉ::
ውርስ የሚከፈትበት ቦታ ሟች ሲሞት በነበረው ዋና የመኖሪያ ቦታ ይሆናል:: የፍትሃብሄር ሕጉ አንቀጽ 826 ንኡስ ቁጥር አንድ በግልጽ የሚያስቀምጠውም ይህን ፍሬ ነገር ነው::
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የውርስ ሕግ የሚተዳደረው በኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ሕግ ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት ባላቸው ባሕሎች እና እምነቶች ጭምር እንደሆነ የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል:: በዚህም በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 ንኡስ ቁጥር 5 እና 34 ንኡስ ቁጥር 5 የተቀመጡ ድንጋጌዎችን መገንዘብ ይቻላል::
ከዚህ ጠቅለል ያለ ሃሳብ መገንዘብ የሚቻለው የውርስ ሃብትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለወራሾች የሚተላለፈው በወራሾች ፍላጎት መሰረት በባሕላቸው ወይም በሃይማኖታቸው አለዚያም በፍትሃብሄር ሕጉ ድንጋጌዎች መሰረት መሆኑን የዘርፉ ባለሙያ ተናግረዋል::
ነገር ግን ወራሾች በባሕላቸው ወይም በሃይማኖታቸው መሰረት የውርስ ክፍፍል ለማድረግ ከመካከላቸው የተወሰኑት ፈቃዳቸውን ካልሰጡ ክፍፍሉ የሚመራው በኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ሕግ ድንጋጌዎች መሰረት ይሆናል ማለት ነው::
ሕጋዊ ወራሽ የሚባሉት እነማን ናቸው?
በኢትዮጵያ የፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 829 መሰረት ውርስ ከሦስት በአንዱ መንገድ ሊስተናገድ ይችላል:: እነዚህም ሟች በሕይወት ዘመኑ ስለ ውርስ ስርዓት እና ስለ ወራሾች የተወው ኑዛዜ ካለ፣ ወይም ሟች በሕይወት ዘመኑ የተወው የኑዛዜ ቃል የሌለ እንደሆነ በዚህ ጊዜ የሚፈጸም ካልሆነም በከፊል ኑዛዜ እና ከፊሉን ደግሞ ያለ ኑዛዜ ጥሎት በሞተ ጊዜ የሚሉ ናቸው::
በፍትሃብሄር ሕግ አንቀጽ 842 ንኡስ ቁጥር አንድ እንደተቀመጠው የአንድ ሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች የሚሆኑት የሟች ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች /ልጅ፣ የልጅ ልጅ… /መሆናቸውን ነው:: ይህ ማለት ከልጆች ውስጥ በሕይወት የሌለ በሚኖርበት ጊዜ የእርሱ ልጅ ወይም የልጅ ልጅ ወራሽ እንደሚሆን የፍትሃብሄር ሕጉ በአንቀፅ 842 ንኡስ ቁጥር ሦስት ይደነግጋል::
ሟች ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች /ልጆች…/ ከሌሉት የሟች ሁለተኛ ደረጃ ወራሽ የሚሆኑት የሟች እናት እና አባት ናቸው:: ይህም በፍትሃብሄር ሕጉ አንቀጽ 843 ተቀምጧል:: ወላጆች ከሌሉ (በሞቱ ጊዜ) ደግሞ በወላጆች ተተክተው የሚወርሱ የሟቹ እህት ወንድም ይሆናሉ::
እንዲሁም ሟች ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ወይም እናት እና አባት ከሌለው የውርስ ሃብቱ ሦስተኛ ደረጃ ወራሽ ለሚባሉት ለሟች አያቶች ይተላለፋል:: ይህ ሁሉ ሆኖ ሟች የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ፣ ሁለተኛ ደረጃ ወራሽ እንዲሁም ሦስተኛ ደረጃ ወራሽ ከሌለው እና ያልተገኘ እንደሆነ የሟች የውርስ ሃብት ወደ መንግሥት እንደሚተላለፍ የፍትሃብሄር ሕጉ አንቀጽ 852 በግልጽ ይደነግጋል::
አንድ ሰው በሕጉ መሰረት የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ወራሽ ስለሆነ ብቻም የሟችን የውርስ ሃብት ለመውረስ ብቁ ነው ማለት አይቻልም:: አንድ ሰው የሟች ሕጋዊ ወራሽ መሆኑ ቢረጋገጥም ሟች ባደረገው ኑዛዜ ከወራሽነት ከወጣ የሟች የሃብት ተካፋይ አይሆንም ማለት ነው::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም