የቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ፣ በካሪቢያን የባህር ጠረፍ አቅራቢያ በሚገኝ ተራራማ ሸለቆ ውስጥ በጓይሬ ወንዝ ዳርቻ ላይ የምትገኝ ደማቅ ከተማ ናት። በ1559 ዓ.ም በስፔን ድል አድራጊዎች “ሳንቲያጎ ዴ ሊዮን ዴ ካራካስ” በሚል ስም የተመሰረተችው ይህች መዲና፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ፣ የባህል እና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆን ታገለግላለች።
ከተማዋ በሁሉም አቅጣጫዎች በተራራዎች የተከበበች ስትሆን ፣ በተለይም በሰሜን በኩል የሚገኘውና ከ8,600 ጫማ በላይ ከፍታ ያለው የአቪላ ተራራ ለከተማዋ ልዩ ውበትን ሰጥቷታል። ነዋሪዎች እና ጎብኚዎች በኬብል ካር ወይም በእግር ጉዞ ወደ ተራራው ጫፍ በመውጣት የከተማዋንና የካሪቢያን ባህርን አስደናቂ እይታ መመልከት ይችላሉ ። ይሁን እንጂ ከተማዋ በመሬት መንቀጥቀጥ ቀጠና ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ፣ በታሪኳ ከሶስት የማያንሱ አስከፊ የመሬት ርዕደ መሬት አስተናግዳለች።
ካራካስ የጥንታዊ እና የዘመናዊ ስነ-ህንጻዎች መገኛ ናት። በከተማዋ “ካስኮ ሴንትራል” በተሰኘው ታሪካዊ ክፍል ውስጥ በ “ኮብልስቶን” የተነጠፉ መንገዶች እና ባለቀለም የቅኝ ግዛት ዘመን ህንጻዎችን ማግኘት ይቻላል። በፕላዛ ቦሊቫር ዙሪያ ያሉ እንደ ካራካስ ካቴድራል እና የሲሞን ቦሊቫር የልደት ቦታ ያሉ ታሪካዊ ስፍራዎች የከተማዋን ያለፈ ታሪክ ይዘክራሉ ። በአንጻሩ ደግሞ 725 ጫማ ከፍታ ያላቸው እና በላቲን አሜሪካ ረጅም ከሚባሉት ተርታ የሚመደቡት ዘመናዊ መንትያ ህንጻዎች የከተማዋን አዲስ ገጽታ ያሳያሉ።
ካራካስ የቬንዙዌላ ብቻ አይደለም የብዙ ላቲን አሜሪካ ሀገራት ነፃነት ጀግና ሲሞን ቦሊቫር የትውልድ ቦታ መሆኗ በታሪክ ታላቅ ስፍራ እንዲኖራት አድርጓል። ልዩ ልዩ የቦሊቫር መታሰቢያዎች በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ይታያሉ፤ አደባባይ፣ ብሔራዊ የመቃብር ስፍራ፣ ሐውልቶችና ታሪካዊ ሕንፃዎች፣ ሙዚየም፣ ዩኒቨርሲቲ ፣ አየር ማረፊያ እና በሌሎችም የዚሁ ጀግና ስም በከተማዋ ውስጥ ይዘከራል።
የቦሊቫር አደባባይ
ከከተማው አዳራሽ በስተሰሜን ምስራቅ የሚገኘው የቦሊቫር አደባባይ የቬንዙዌላ ነፃነት የታወጀበት እና ሕገ መንግሥቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነበበበት ታሪካዊ ጉልህ ቦታ ነው። በአደባባዩ መሃል የሲሞን ቦሊቫር ታዋቂ የፈረስ ሐውልት ቆሞ ይታያል።
ሲሞን ቦሊቫር በተወለደባት በካራካስ የሚገኝ አንድ አነስተኛ መኖሪያ ቤትም የጀግናቸው መታሰቢያ ሆና እስከዛሬ በክብር ይጎበኛል። ቤቱ ትንሽ ቢሆንም፣ ግቢ እና በረንዳ ያለው ሲሆን ለነፃ ጉብኝት ክፍት ነው። በውስጡም የቦሊቫርን የቤት ዕቃዎች፣ የቁም ሥዕሎች እና ታሪካዊ ቅርሶች ማየት ይችላሉ።
ከቦሊቫር የትውልድ ቦታ አጠገብ የቦሊቫር ሙዚየም ይገኛል። ይህ ሙዚየም የደቡብ አሜሪካ ሀገሮችን ወደ ነፃነት የመራውን ብሔራዊ ጀግና ትሩፋት ለመጠበቅ ሲባል ለክብሩ የተሰየመ ነው። በስዕሎችና በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች አማካኝነት ጎብኚዎች የቦሊቫርን ሀሳቦችና ታሪካዊ ተጽዕኖ መረዳት ይችላሉ።
በካራካስ የሚገኘው ሌላው የቬንዙዌላ ብሔራዊ ፓንቴዮን የሚባለው የመቃብር ስፍራ ደግሞ የከተማዋ ውበት ነው። በ1822 ዓ.ም በሳንታ ማርታ፣ ኮሎምቢያ ያረፈው የሲሞን ቦሊቫር አስከሬን ከ47 ዓመታት በኋላ አሁን በካራካስ በሚገኘው ብሔራዊ ፓንቴዮን ውስጥ ተቀብሮ ይገኛል።
ይህ የተቀደሰ መቃብር ውብ የጣሪያ ሥዕሎችን እና የቬንዙዌላን ታሪክ የቀረጹ ፕሬዚዳንቶች፣ ፖለቲከኞች እና አርቲስቶችን ጨምሮ የቦሊቫርን ክብር የሚያጎሉ በርካታ ሐውልቶችን ያሳያል።
ከቦሊቫር አደባባይ በስተምስራቅ የካራካስ ካቴድራል ይገኛል። ይህ በቅኝ ግዛት ዘመን የአሰራር ዘይቤ የተሰራ ቤተክርስቲያን ነጭ ግድግዳዎች ድንቅ ሕንፃ ነው። በመሬት መንቀጥቀጥ ከወደመ በኋላ እንደገና ተገንብቶ አሁን ያለውን ውብ ገጽታ ለማሳካት በርካታ እድሳት ተደርጎለታል። የሲሞን ቦሊቫር ወላጆች እና ባለቤቱ እዚህ ተቀብረዋል። ብቻ በካራካስ የሲሞን ቦሊቫር መታሰቢያ የሆኑ በርካታ ታሪካዊ መስህቦች ውስጥ እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።
ተፈጥሯዊ ውበቷ ደግሞ የካራካስ ሌላ ዋና መለያዋ ነው። አቪላ ተራራ (ዋራይራ ሬፓኖ ብሔራዊ ፓርክ) ከተማዋን እንደ አረንጓዴ ግድግዳ ከሰሜን በኩል ይከብባታል። ነዋሪዎችና ጎብኚዎች በኬብል መኪና ወይም በእግር መንገድ ወደ ተራራው ሲወጡ የከተማዋንና የካሪቢያን ባሕርን አስደናቂ እይታ ያገኛሉ። በከተማዋ ውስጥ እንደ “ፓርኬ ዴል እስቴ” ያሉ ፓርኮች ለነዋሪዎች የእረፍትና የተፈጥሮ መዝናኛ እድል ይፈጥራሉ።
የሎስ ሮክስ ደሴቶች ስብስብ የካራካስ ሌላው የተፈጥሮ ውበቷ ነው። የሎስ ሮክስ የደሴቶች ስብስብ ከካራካስ በስተሰሜን በካሪቢያን ባህር ውስጥ ከ350 በላይ አስደናቂ ደሴቶችን ያቀፈ ነው። ንፁህ ነጭ የባህር ዳርቻዎች እና አስደናቂ ሐይቆች ስላሉት፣ የተለያዩ አዝናኝ ተግባራትን በመከወን ሀሴትን ያላብሳሉ። አካባቢው ለአሳ ማጥመድም ተወዳጅ ነው፤ እንደ ባራኩዳ ያሉ ትላልቅ ዓሦችን ለመያዝ እድሎች ይሰጣል።
ካራካስ ዘመናዊ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ከታሪካዊ ህንፃዎች ጋር ተቀላቅለው የሚፈጥሩት ውህድ ውበት ያፈካት ልዩ ከተማ ናት፤ ይህም ከተማዋን ልዩ እና አነጋጋሪ መልክ ይሰጣታል። በአንድ በኩል ዘመናዊ የንግድ ማዕከሎችና የመኖሪያ ሕንፃዎች፣ በሌላ በኩል በተራሮች ላይ የተዘረጉ የህዝብ መኖሪያ አካባቢዎች ይገኛሉ።
በአረንጓዴ ውበት ካራካስን ያደመቁ ፓርኮች እና የአትክልት ስፍራዎች ብዙ ናቸው። የፓርኬ ዴል ኤስቴ፣ የቦታኒካል ጋርደን እና ፓርኬ ሎስ ካኦቦስ ለከተማዋ አረንጓዴ ውበት ይሰጣሉ። ከአስገራሚ ፓርኮቿ መካከል ጥቂቶችን እያነሳሳን ሽርሽራችንን እንቀጥል።
ፓርኬ ሎስ ካኦቦስ
ፓርኬ ሎስ ካኦቦስ፣ ካራካስ ውስጥ የሚገኝ፣ በአረንጓዴ ዛፎች፣ በሚያማምሩ አበቦች እና ማራኪ የስነጥበብ ስራዎች የተሞላ ታሪካዊ የከተማ ፓርክ ነው። ይህ 21.8 ሄክታር አረንጓዴ ቦታ የተመሰረተው በ1932 ሲሆን ስሙም በቬንዙዌላ ተወላጅ ማሆጋኒ ዛፍ ስም ነው። ፓርኩ ለመዝናኛ የእግር ጉዞ እና ለቤተሰብ ጉዞዎች ፍጹም ቦታን ይሰጣል። ለልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ስለ አካባቢው ታሪክ እና ስነጥበብ ለመማር እድል የሚሰጡ የተለያዩ ቅርጻ ቅርጾችን እና ሀውልቶችን ያሳያል።
አቪላ ብሔራዊ ፓርክ
በቬንዙዌላ የሚገኘው አቪላ ብሔራዊ ፓርክ አስደናቂ የፓኖራሚክ እይታዎችን፣ እንደ የእግር ጉዞ እና የወፍ በረር እይታ (በርጽስ አይ ቢው)ያሉ የውጪ እንቅስቃሴዎችን እና ጸጥ ያለ የተፈጥሮ አቀማመጥን የሚያቀርብ ተራራማ ገነት ነው። የፓርኩ ታዋቂው የአቪላ ተራራ በሰሜን በኩል ካራካስን በማለፍ ለከተማዋ ቀዝቃዛ አየር ተስማሚ ሙቀትን ይሰጣል።
በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዚየም በከተማዋ ይገኛል። ጎብኚዎች ስለ እንስሳት፣ ስለ ጂኦሎጂ እና ስለ አርኪኦሎጂ መማር የሚችሉበት ተቋም ነው። ሙዚየሙ ከ200,000 በላይ ናሙናዎችን ይይዛል። ከእነዚህም ውስጥ የእንስሳትና የነፍሳት ማሳያዎች፣ የተቆፈሩ ቅሪተ አካላት፣ የሸክላ ዕቃዎች እና የጥንት የጦር መሳሪያዎች ይገኙበታል።
በባህል ዘርፍ ካራካስ እጅግ የበለፀገች ናት። ሳልሳ፣ አፍሮ-ቬንዙዌላዊ ሙዚቃና የባህላዊ ዜማዎች በከተማዋ ዕለታዊ ሕይወት ውስጥ ተቀላቅለው ይሰማሉ። ታዋቂው ቴሬሳ ካረኞ ቲያትር ከተማዋን የሙዚቃና የሥነ-ጥበብ ማዕከል አድርጓታል። ብዙ ሙዚየሞች፣ ጋለሪዎችና የባህል ተቋማት የካራካስን ፈጠራዊ ኃይል ያሳያሉ።
ካራካስ “የሙዚቃ የፈጠራ ከተማ” በመባል የምትታወቅ ሲሆን፣ ከ61 በላይ የባህል ስፍራዎች ለሙዚቃ የተመደቡባት መዲና ናት። ከሳልሳ እስከ አፍሮ-ቬንዙዌላ የሙዚቃ ስልቶች ድረስ በየጎዳናው ይደመጣሉ። በተለይም ወጣቶችን በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለማሳተፍ የሚሰራው “ኤል ሲስቴማ” (National System of Youth and Children’s Orchestras) የተሰኘው ፕሮግራም ከተማዋ ለሙዚቃ ዘርፍ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ።
ምንም እንኳን ከተማዋ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ልዩነት፣ የአካባቢ ብክለት እና የከተማ መስፋፋት ያሉ ተግዳሮቶች ቢገጥሟትም፣ ነዋሪዎቿ (ካራኬኞስ) በጽናታቸው፣ በደግነታቸው እና ለከተማቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ይታወቃሉ። ዛሬ ካራካስ በቱሪዝም፣ በፈጠራ ስራዎች እና በባህላዊ ልውውጦች አማካኝነት የተሻለ መጻኢ እድልን ለመፍጠር እየተጋች ትገኛለች። እኛም አበቃን።
አጫር እዉነታ
ስለ ቬንዙዌላ አጫጭር እውነታዎች
- ቬንዙዌላ በ ደቡብ አሜሪካ ሰሜን ይገኛል።
- ዋና ከተማዋ ካራካስ ናት።
- በዓለም ላይ የተረጋገጠ ከፍተኛ የነዳጅ ክምችት አላት።
- የዓለም ከፍተኛው ፏፏቴ አንጀል ፏፏቴ በቬንዙዌላ ይገኛል።
- ከ ካሪቢያን ባሕር ጋር ዳርቻ አላት።
- ዋና ቋንቋዋ ስፓኒሽ ነው።
- የሀገሪቱ ገንዘብ ቦሊቫር ነው።
- ቬንዙዌላ በጣም ባለብዙ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ናት።
- “ቬንዙዌላ” ማለት «ትንሽ ቬኒስ» ማለት ነው።
- የሀገሪቱ የብሔራዊ ወፍ ቱርፒያል ነው።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


