የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ጥናት እንደሚያሳዩት በአማራ ክልል በመስኖ የሚለማ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ11 በመቶ በታች ነው፡፡
መረጃው እንዳመላከተዉ ክልሉ ከፍተኛ የከርሰ ምድር እና የገፀ ምድር ውኃ ሀብት እንዳለውና- ዓባይን ጨምሮ እንደ ተከዜ፣ አይማ፣ ሽንፋ፣ አንገረብ፣ ላህ… ያሉ ትላልቅ ወንዞች፣ ጣና ሐይቅ፣ ዘንገና እና ሌሎች ሐይቆችም በክልሉ ይገኛሉ። እነዚህ ሀብቶች ለመስኖ ልማት በእጅጉ የተመቹ ቢሆኑም የክልሉ ተጠቃሚነት ግን ዝቅተኛ መሆኑን ነው መረጃው የጠቆመው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተያዘው የምርት ዘመን በበጋ የመስኖ ልማት ከ342 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ47 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ ለዚህ ደግሞ (የቀጣይ የመኸር እርሻን ጨምሮ) ከ66 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ለማዋል የታቀደ ሲሆን ከ60 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ የሚሆነው መዘጋጀቱን ቢሮው አስታውቋል፡፡
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር ባደረግነው የስልክ የመረጃ ልውውጥ እንደተገነዘብነው አርሶ አደሮች በመደበኛው የግብርና ሥራ (በመኸር) ያለሙትን ሰብል ከመሰብሰብ ጎን ለጎን ለበጋ መስኖ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡
ከዝግጅቶች መካከልም የመሬት ልየታ፣ የማሳ ዝግጅት፣ ደጋግሞ ማረስ፣ የመስኖ ቦይ (ካናል) ጠረጋ፣ የውኃ ጠለፋ፣ የግብዓት እና የዘር ዝግጅት ማድረጋቸውን በስልክ አጋርተውናል።
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ አስኩና ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተፈራ አባየ ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት መስኖ ልማት ላይ በትኩረት በመሥራታቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። ከመስከረም ወር 2017 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የመስኖ እርሻ ሥራቸውን ማከናወን እንደጀመሩና በአሁኑ ወቅትም መሬታቸውን አለስልሰው ስንዴ እና የቢራ ገብስ መዝራታቸዉን ነግረዉናል።
ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን አምርተው ለገበያ እንዳቀረቡ የተናገሩት አርሶ አደሩ በዚህ ዓመትም በዋናነት ሽንኩርት፣ ቀይ ሥር፣ ድንች፣ ካሮት እና ጥቅል ጎመን ለማልማት በቂ ዝግጅት አድርገዋል። ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግል ዘመናዊ የውኃ ቦይ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ማዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል።
አርሶ አደሩ ምርታቸው እንዲጨምር የተፈጥሮ የአፈር ማዳበሪያን (ኮምፖስት) አዘውትረው በመጠቀማቸውም የምርት ጭማሪ አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ ማረስ እና መዝራት ከዚያም መንከባከብ ለፍሬ እንደሚያበቃው እማኝነታቸውን ሰጥተውናል።
አርሶ አደሩ አክለውም እንደ አርሶ አደር የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያከናውኑ በማንሳት የተሻሻለ ምርጥ ዘር እና የግብርና ቴክኖሎጂ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ሐረት ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ይርጋ ወልደሐዋሪያም ቀደም ሲል የተነሳውን ሐሳብ ይጋራሉ፤ እርሳቸው እንዳሉት በሰላም እጦቱ ምክንያት በግብርና ሥራቸው ላይ ከባድ ችግር ገጥሟቸው ነበር፤ ቢሆንም ችግሩን በመቋቋም የግብርና ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ነው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ የተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅትም “የመስኖ ልማት ለማልማት በቅቻለሁ” ብለዋል።
የስንዴ ምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያም በበቂ ሁኔታ ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ በአንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቀይ ሽንኩርት እና ስንዴ ዘርተው እየተንከባከቡ ነው። የውኃ መሳቢያ ሞተር በመጠቀምም የመስኖ ልማትን እያከናወኑ ነው የሚገኙት። አርሶ አደሩ አክለውም በመስኖ ያለሙትን የስንዴ ሰብላቸውን ከአረም እየተከላከሉ፣ ሽንኩርታቸውን ደግሞ እየኮተኮቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ማሳቸውን መንከባከባቸው እና ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማቸው ደግሞ ምርት እንዲጨምር እንዳስቻላቸው አስታውቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከመኸር ሰብል ስብሰባው እና ጥበቃው ጎን ለጎን የበጋ መስኖ ልማትን በትኩረት እየሠራ መሆኑን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ስማቸው ለበኩር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት፤ በምርት ዘመኑ በአዲስ እና በነባር 39 ሺህ 552 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 27 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የሚለማ ነው።
ምክትል ኃላፊው እንዳሉት ለማልማት ከታቀደው ውስጥ ከ28 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል። ከስድስት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ደግሞ በዘር ተሸፍኗል። ለመስኖ ልማቱ የወንዝ ጠለፋ፣ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮችን የመጠገን እና ወደ ሥራ የማስገባት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ዕቅዱን ለማሳካትም የግብዓት እና የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን እየሰበሰበ፣ እያረሰ እና እየዘራ ነዉ ያሉት አቶ አዲሱ ለበጋ መስኖ ልማቱ የሚውል 84 ሺህ 514 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልግ ሲሆን ከአምስት ሺህ በላይ ኩንታል ተሰራጭቷል። 1 ሺህ 250 ኩንታል ምርጥ ዘር ለማቅረብም በዕቅድ ተይዟል። ሦስት መቶ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ማሰራጨት ተችሏል።
ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በምርት ዘመኑ 918 ሺህ ኩንታል ምርት በበጋ መስኖ ስንዴ ይገኛል ተብሎም ይጠበቃል።
በተመሳሳይ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ታደሰ ማሙሻ ለበኩር ጋዜጣ እንደገለፁት ዞኑ 43 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት አቅዶ እየሠራ ነው። አርሶ አደሩ የመኸር ሰብሉን እየሰበሰበ የመስኖ ሥራን እያከናወነም ይገኛል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ከኅዳር ወር ጀምሮ እስከ ታኅሳስ አጋማሽ 2017 ዓ.ም በበጋ መስኖ የሚለማውን መሬት በዘር ለመሸፈን በዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። በልማቱም 22 ሺህ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አርሶ አደሩ ለመስኖ ልማቱ የሚረዱ ግብዓቶችን ማዘጋጀት፣ የቦይ ጠረጋ ሥራን ማከናወን፣ መሬቱን ማለስለስ እና መዝራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የተሻለ ምርት ለማግኘት ጊዜን እና ጉልበትን እንዲሁም ግብዓት እና የግብርና ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት መምሪያ ኃላፊው የመስኖ ልማት ሥራን እስከ ሦሥት ጊዜ ማከናወን ይገባልም ብለዋል።
አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት በመሰብሰብ ለመስኖ ልማት ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የተናገሩት ኃላፊው “ውኃ እና መሬት መገናኘት አለባቸው፤ መሬቱ ፆም አይደር” ብለዋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ (ኅዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም) ለማልማት ከታቀደው 43 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 33 ሺህ ሄክታር መሬት ታርሷል። ሦስት ሺህ ሄክታሩ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።
ለበጋ መስኖ ልማቱ ጥቅም ላይ የሚውል 126 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብም ታቅዷል። ምርጥ ዘር ምርታማነትን ለማሳደግ አይነተኛ ዘዴ ነው ያሉት ኃላፊው በምርጥ ዘር አባዢ ድርጅቶች ምርጥ ዘር መዘጋጀቱን በመግለጽ፣ የምርጥ ዘር ችግር አይኖርም ብለዋል።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በ2017 በጀት ዓመት 342 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በ1ኛ፣ በ2ኛ እና በ3ኛ ዙር በመስኖ በማልማት ከ47 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እንደሚሸፈን ተመላክቷል። ለዚህም በቅድመ ዝግጅት ወቅት በመስኖ የሚለማውን መሬት የመለየት፣ ለተሳታፊ አርሶ አደሮች ግንዛቤ የመፍጠር፣ ግብዓት በወቅቱ የማቅረብ እና ሌሎች ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛል።
የዘንድሮውን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ቢሮው እንዳለው የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር እና የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ የተሻለ የምርት ጭማሪ ለማግኘት ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።
ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግል ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብም ታቅዷል።
በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ሚሊዮን 197 ሺህ 28 አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚጠጉ አርሶ አደሮች መስኖ ማልማት ጀምረዋል። ስድስት ሺህ 237 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመስኖ ቦይ ጠረጋም ተካሂዷል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም