በካምቦዲያ በተካሄደ የወንዶች ቁንጅና ወይም የውበት ውድድር ለመጨረሻ ማጣሪያ ደርሰው አስተያየት እንዲሰጥባቸው በማሕበራዊ ሚዲያ ፎቶግራፋቸው በተለቀቀ ዕጩዎች ላይ ትችት እና ቅሬታ መነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
የውድድሩ አሸናፊ በ2025 ካምቦዲያን ወክሎ በዓለም የቁንጅና ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ያስነበበው ድረ ገጹ ሀገራዊ ውድድሩ የብዙዎች መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ትችት እና ነቀፌታ ማስከተሉን ነው ያሰፈረው፡፡
አወዳዳሪዎቹ ለፍጻሜ የደረሱ ዕጩዎችን ፎቶግራፍ ለብዙሃን በማህበራዊ ድረገፆች ለእይታ እንዳበቁ የተሰጧቸው አስተያየቶች ሲጨመቁ – ለማጣሪያ ያለፉት ወይም የደረሱት “ተራ ይመስላሉ፣ከደረጃ በታች ናቸው፣ ከፊሎቹ በአካላቸው ላይ ወርቅ መሰል ጌጥ እና ዘይት በመቀባታቸው በማንጸባረቅ እውነታውን ለመሸፈን የታቀደ ነው” የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ከተመልካች የሰላ ትችት ከተሠጠው ለአሸናፊነት ከተቃረቡት መካከል “ቢስትራስመስ ” የተሠኘው የዓይን ዕክል ያለበት መሆኑን ተመልካቾች በግልጽ አመላክተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪ ተመልካቾች ለማጣሪያ ከደረሱት ዕጩዎች መካከል ለአሸናፊነት የሚበቃው ሀገሪቱን ማለትም ካምቦዲያን ወክሎ ለዓለም አቀፍ መድረክ መቅረቡ የሚያስተች እንዳይሆን ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡
አወዳዳሪዎቹ በበኩላቸው ከተመልካች የተሰጡትን አስተያየቶች ግራ ቀኙን ፈትሸዋል- መርምረዋል፤ የወንዶች የውበት ውድድሩ ውጫዊ የአካል ውበትን ብቻ መሠረት የሚያደርግ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከአካል እና ቁመና ውበት ባሻገርም የግል ተሰጥኦ እና በራስ መተማመን በመስፈርትነት መካተቱንም ነው ምላሽ አድርገው ያሰመሩበት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም