ውይይት እና ድርድር፡- አትራፊዉ መንገድ

0
132

በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አንድ ዓመትን ተሻግሯል፤ ይህም ክልሉን ለከፋ ጉዳት ዳርጎታል:: ለአብነትም ሚሊዮኖችን ከትምህርት ገበታ አስቀርቷል፤ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን አውኳል፤ ከምንም በላይ ደግሞ ምትክ የለሹን የበርካቶችን ሕይወት ነጥቋል::

እንቅስቃሴ በመገደቡም የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ አድርጓል፤ ይህ ደግሞ ክልሉን ለምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ዳርጎታል:: በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ውድመት ሳያገግም ለአሁናዊ ግጭቱ በመዳረጉም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል::

ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ በብዙው ተነግሯል፤ ለአብነትም የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት “ግጭቱ በዓመቱ ለማከናወን ያቀድኩትን እንዳልፈጽም አድርጎኛል” በማለት በሪፖርቱ አመላክቷል::

በተመሳሳይ የታቀደውን ግብር መሰብሰብ አለመቻሉን ከክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፤ በበጀት ዓመቱ ከ71 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱ ይታወሳል:: ይሁን እንጂ መሰብሰብ የተቻለው ከ42 ቢሊዮን ብር በታች ነው::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ክልሉ ከገባበት ችግር እንዲወጣ ውይይት እና ድርድር የተሻለው የመፍትሔ መንገድ መሆኑን በተደጋጋሚ ተነግሯል፤ የክልሉ መንግሥትም በውይይት እና ድርድር ችግሩን ለመፍታት ፍላጎቱን አስታውቋል፤ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከሰሞኑ እንዳሉት በጦርነት፣ በጦር መሣሪያ የሚፈታ ችግር የለም:: በመሆኑም ክልሉን ከገባበት ችግር ለማውጣት አማራጩ ውይይት እና ድርድር መሆኑን ጠቁመዋል፤ የክልሉ መንግሥትም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን አክለዋል::

ከሰሞኑ በተካሄደው መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ የክልሉን ሰላም በተመለከተ የምክር ቤት አባላት ሐሳብ አንስተዋል፤ የታሰቡ የልማት ሥራዎችን ለማሳካትም ሰላምን ማሳፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆን እንደሚገባ ጠይቀዋል፤ ለዚህም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የሰላም ሂደቶች ዳር እንዲደርሱ ሁሉም ኃይሎች መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል:: “የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ማጽናት የሞት ሽረት ጉዳይ ነው” ሲሉም ነው የምክር ቤት አባላቱ ያሳሰቡት::

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋዬ “በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ድርድር ምርጫ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው” ብለዋል። አፈ ጉባዔዋ አክለው እንዳሉት የሰላም እጦቱ በየቤታችን ከፍተኛ ችግር እያደረሰ ነው። በመሆኑም ሰላም እንዲመጣ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።

በመደበኛ ጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አፈ ጉባዔዋ ክልሉ ያለፈበትን ነባራዊ ሁኔታ አብራርተዋል።

ለአንድ ዓመት የዘለቀው ግጭት የክልሉን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጎድቶታል ያሉት አፈ ጉባኤዋ የሰላም ችግር የመጨረሻ መፍትሔው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ መቋጨት እንደሆነ አመላክተዋል::

እንደ ወ/ሮ ፋንቱ ማብራሪያ ጦርነት እና ግጭት መቋጫው ሰላማዊ ውይይት ነው። በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ውይይት እና ድርድር ምርጫ ሳይሆን ብቸኛ አማራጭ ነው:: የሰላም አማራጭን ባዘገየን ቁጥር የሚፈጠረው ተጨማሪ ቀውስ እና ጉዳት እንደሆነ መገንዘብ ይገባል። በመሆኑም ለሰላም ቀን ከሌሊት መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::

በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት በቅርቡ የሰላም ምክር ቤት (ካውንስል) መቋቋሙ ይታወሳል፤ የሰላም ምክር ቤቱም ሁሉም ኃይሎች ለድርድር ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል::

(ጌትሽ ኃይሌ)

በኲር ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here