ውይይቶች ምን ጠቆሙ?

0
313

“ስለሰላም በተደጋጋሚ የምናወራው በአገራችን የማያባራ ግጭት በመኖሩ ነው” ይላሉ የሰላምና ደህንነት ምሁሩ ኘሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ ከሕዝብ ጋር ሲመክሩ::

ሰሞኑን በአማራ ክልል በተለያዬ አካባቢ በተካሄዱ የሰላም ኮንፍረንሶች የተሳተፉ የክልሉ ኗሪዎችም በራሳቸው፣ በቤተሰቦቻቸው እና በአጠቃላይ በክልሉ እየደረሰ ያለውን ውድመት እና ሰቆቃ በመጥቀስ ተፋላሚ ኃይሎች ጦርነቱን አቁመው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አሳስበዋል::

የክልሉ መንግሥት በበኩል በዚሁ ጦርነት ምክንያት የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መስተጓጐላቸውን እና ከ15 ቢሊዬን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን ነው ይፋ ያደረገው:: በትምህርት ላይ የደረሰውን ጉዳት ብቻ እንደ አብነት በመውሰድም 298 ትምህርት ቤቶች ወድመው 3725 ያህሉ ደግሞ በመዘጋታቸው ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዬን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ መሆናቸውንም አሰታውቋል::

አሜሪካን እና የአውሮፖ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶችም ጦርነቱ በተለይ በንፁሃን ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ አውግዘው ጉዳዩ እንዳሳሰባቸውም በተደጋጋሚ አስታውቀዋል::

የፌደራሉ መንግስት በጦርነት የሚፈታ ችግር እንደሌለ በመጥቀስ  ችግሩን በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን እየተናገረ ይገኛል:: ተፋላሚው ኃይል የሰጠው ምላሽ ባይታወቅም ጦርነቱ ግን አሁንም ድረስ የንፁሀንን ህይወት ጭምር እየቀጠፈ፣ የሀገርን አንጡራ ሀብት እያወደመ፣ ዜጐችን ለድህነት እየዳረገ ቀጥሏል::

ታዲያ ይኸው አገርንና ሕዝብን እያወደመ ያለው ግጭት እና ጦርነት እንዴት ይፈታ? እንዴትስ ይቁም?

ፖለቲከኞች በተለይ የደቡብ አፍሪካን እና የሩዋንዳን የግጭት አፈታት እንደምሳሌ በማንሳት በኢትዮጵያም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መጀመሪያ ብሔራዊ እርቅ ማድረግና አገራዊ መግባባትን መፍጠር አስፈላጊ ነው ይላሉ::

ይህንኑ የብሔራዊ እርቅ ሀሳብ የሚያቀነቅኑ ምሁራን ባለፉት ዘመናት በአገሪቱ ለተከሰቱ ልዩነቶች እና መቋሰሎች አንድ መፍትሄ እስካልተበጀ ድረስ ስለ አገር ማውራትም ሆነ መወያየት ከችግሩ እንዳንወጣ ያደርገናል ሲሉ የአጀንዳውን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ::

እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት እና የኢትዮጵያን ህልውና ለማስጠበቅ እስካሁን የነበሩ በደሎች፣ ቅሬታዎች እና አለመግባባቶች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ መፍትሄ ማበጀት ያስፈልጋል የሚለውን የብሔራዊ እርቅ ፅንሰ ሀሳብ ያለፈው ገዥ ፖርቲ ኢህአዴግ “ማን ተጣላና” በሚል ገሸሽ አድርጐት ቢቆይም  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግን “ወደፊት በጋራ ለመጓዝ ያለፈውን በመተው በአዲስ አስተሳሰብ እና በፍቅር መሥራት ይገባል” ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል::

ይህንኑ ተከትሎ ይመስላል በተለይ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በምሁራን እና በመንግሥት እቅድ ጭምር በግጭቶች ዙሪያ ሰላማዊ መፍትሔ ለማግኘት ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ::

የአገራችን ሰላም ጉዳይ ያሳስበናል ያሉ ግለሰቦች እና ምሁራን በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ “ዕርቀ ሰላም እና ብሔራዊ መግባባት” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ሙያቸውን እና የህይወት ተሞክሯቸውን ቀምረው የውይይት መነሻ ካቀረቡት መካከል የሰላምና ደህንነት ምሁሩ ኘሮፌሰር ህዝቅያስ አሰፋ  አንዱ ናቸው::

“ስለ ሰላም በተደጋጋሚ የምናወራው በአገራችን የማያባራ ግጭት በመኖሩ ነው” ሲሉ የውይይቱን አስፈላጊነት ያስቀደሙት  ኘሮፌሰሩ “መፍትሔውንም ራሳችን ቁጭ ብለን መፈለግ ያለብን እንጂ ወደ ሦስተኛ ወገን የምንገፋው ሊሆን አይገባም” ነው ያሉት – እንደ ኢትዮጵያን ሪፖርተር ዘገባ::

ከግጭት አፈታት አንፃር የዜጎች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ኘሮፌሰር ህዝቅያስ ከተሳትፎ አኳያ ልዩነት ያሏቸው ስድስት ያህል የግጭት መፍቻ ዘዴዎች መኖራቸውን አሳይተዋል:: እነዚሁ ዘዴዎች ኃይል /force/፣ ፍርድ/Adjudication/፣ ግልግል/Arbitration/፣ ድርድር/Negotiation/፣ ሽምግልና /mediation/ እና ዕርቅ /Reconciliation ናቸው::

ከእነዚሁ ዘዴዎች ውስጥ የጦር መሣሪያን ወይም ሌላ ጉልበትን በመጠቀም ሌላውን ወገን በማስገደድ የሚከናወነው የኃይል የግጭት አፈታት ዘዴ ሰላምን ለማምጣት የብዙዎች የመፍትሔ ሐሳብ የማይደመጥበት፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ያልሆነበት እና አሁን በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው አካሄድ ነው ያሉት ኘሮፌሰር ዘዴውን “ለማንም የማይጠቅም!” ብለውታል::

ችግር ያለባቸው ወገኖች ቁጭ ብለው አብረው በመስራትና በመነጋገር ለችግራቸው መፍትሔ የሚፈልጉበት የድርድር ግጭት መፍቻ ዘዴን ሁለቱንም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለማምጣትና ለውይይት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ እና አስቸጋሪ ቢሆንም ባለድርሻ አካላቱን ማምጣት ከተቻለ ግን ካለው የተሳትፎ መጠን አንፃር ግጭቶችን ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ነው ብለውታል:: ሁሉም የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንደግጭቱ አይነት ችግርን ለመፍታት አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም ዕርቅ /Reconciliation/ የምንለው ዘዴ ግን በግጭት ወቅት የተፈጠረውን ችግር ከመፍታት በዘለለ የተከሰቱ ማህበራዊ ስንጥቆችን እስከወዲያኛው መፍትሔ ማበጀት ላይ የሚያተኩር እና ተመራጭ መሆኑን ይናገራሉ::

“በሽምግልና እና ዕርቅ መሀል ያለው ልዩነት ሽምግልና በሁለቱ ወገኖች የሚነሳውን ችግር አስመልክቶ መፍትሄ መስጠት ላይ ብቻ ሲያተኩር ዕርቅ ግን አድማሱን ከሽምግልና አስፍቶ በግጭቱ ወቅት የተጐዳው፣ የተፈናቀለው እና የተዋረደው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈጠረውን ስብራት እንዴት እንጠግነው የሚለው ላይ ጭምር የሚያተኩር ነው” ነው ያሉት – እንደ ኢትዮ::

ከዚህ አንፃር ምንም እንኳን ግጭቱ አንዴ ቢፈታም የተበጠሰው ዝምድና እንዴት እንደሚጠገን፣ ቂምን፣ ጥላቻን፣ ፍርሃትን፣ ሐዘን እና የመሳሰሉትን የግጭት ጠባሳዎች እንዴት መጠገን እንደሚቻል ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ይኸው የዕርቅ ግጭት መፍቻ ዘዴ ችግሩን ከመፍታት አልፎ የማህበረሰብን ጠባሳ እና ቁስሎች የማከም ከፍተኛ ኃይል ያለው በመሆኑ በቅጡ ተግባር ላይ ከዋለ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው የተባለው::

ኢትዮጵያ እነዚህን ዘመናዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች ጨምሮ የራሷ የሆኑ በርካታ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችም ያሏት ሆኖ  ሳለ የሚከሰቱባትን የማያባሩ ግጭቶች እና ጦርነቶች ለመፍታት ያልተጠቀመችባቸው ስለምን ነው? የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው ኘሮፌሰሩ “የአገራችንን ችግር ለመፍታት የጎደለው የፍላጐት ማጣት ጉዳይ ነው” ካሉ በኋላ ፍላጐት ማምጣት ከተቻለ የኢትዮጵያ ችግር ከሌላው ዓለም አንፃር ከባድ አይደለም” ብለዋል::

ተሳታፊዎቹ ውይይታቸውን ያጠናቀቁት ታዲያ ግጭት ውስጥ ያሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉም የሀገራቸውን እና የሕዝባቸውን ሰላም ለማስፈን ሲሉ እርቅን አማራጭ አድርገው ወደ ጠረጴዛ እንዲቀርቡ ጥሪ በማቅረብ ነው::

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የስነ ፅሁፍና ፎክሎር መምህሩ ዶ/ር ብርሃኑ አሰፋ ደግሞ ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን ተጠቅሞ የክልሉንም ሆነ የሀገራችን የተለያዩ ግጭቶች እና ጦርነቶች በማስቆም ዘላቂ እርቅ እና ሰላምን ማምጣት ይቻላል ይላሉ::

የራያውን ዘወልድ፣ የተሁለደሬውን አበጋር እና የሀብሩውን ሸህለጋን እንደ አብነት በማንሳት እነዚሁ ስርዓቶች በማህበረሰቡ እምነት እና ስነ ልቦና ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ውጤታማነታቸውና የእርቁ ዘላቂነት ተመራጭ ያደርጋቸዋል ብለዋል::

አሁን ያጋጠሙንን ግጭቶች በመፍታት በኩልም የብሔራዊ የምክክር እና የዕርቅ መድረኩ እነዚሁን ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች ሊጠቀምባቸው  ይገባል ነው ያሉት ለአሚኮ በሰጡት ቃለ ምልልስ::

ዶ/ር ብርሃኑ የጠቀሷቸው እነዚሁ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች በማህበረሰቡ እሴት ውስጥ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህዝቡ እንደ በጐ እሴት የሚጠቀምባቸው እና ጎልብተው ለዘመናት የዘለቁ፣ በሀገር ሽማግሌዎች፣ በሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎች እና ህዝብ አምኖ በሚመርጣቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የሚተገበሩ ውጤታማ ስልቶች መሆናቸውን ጠቅሶ ሰላምን ለማስፈን ልንጠቀምባቸው እንደሚገባ የጠቆመው ደግሞ የፌደራል አቃቤ ሕግ ነው – በድረ ገፁ::

ወሎ አካባቢ እንደሚሰራባቸው ከተጠቀሱት ባሕላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶች ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ መንገዶች ያሉ ሲሆን በአማራ እና ትግራይ ሕዝብ የሚታወቀው “የሽምግልና ስርዓት፣ በከረዩዎች የሚታወቀው “አራራ፣ የኦሮሞዎቹ “ጃርሱማ”፣ የሲዳማዎቹ” ኦቱባ”፣ የሶማሌዎቹ “ገራድ” እና የአፋሮቹ “ገረብ” ከሚጠቀሱት ጥቂቱ ናቸው::

እነዚሁን ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች በጥበብ እና በዘዴ ተጠቅሞ ወደ ሰላማዊ የዕርቅ ሥርዓት መግባት እና በአፈፃፀሙም ወቅት በመልካም ተግባቦት፣ በተባባሪነት፣ በአስታራቂ ሀሳብ አቅራቢነት እና ስሜትን ተቆጣጥሮ በመወያየት አሸናፊ ሀሳብን መርጦ የኢትዮጵያንና ሕዝቧን ሰላም ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባር ነው:: የአማራ ክልል የሰላም ኮንፈረንስ ተወያዮች የውይይታቸው መቋጫ እርቅና ሰላምን መሻት ላይ አትኩሮ መገኘቱም ጦርነት ካስከተለበት ዳፋ ይመነጫልና ተፋላሚ ሀይሎች ሁሉ በተለይም ደግሞ የተሻለ አቅምና ሀላፊነት ያለበት መንግሥት  ለሰላም ልባዊ ፈቃዳቸውን ሊያሳዩ ይገባል:: አሊያ ግን ጦርነት ያስመረረው እና መድረሻ ያጣው ሕዝብ በነቂስ ጦር መዝዞ እንደማይወጣ ምንም ማረጋገጫ የለም- እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ::

 

(ጌታቸው ፈንቴ)

በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here