ውዱ የገበያ ጐዳና

0
111

በጣሊያን ሚላን ውስጥ የሚገኘው ሞንቴናፓሊዮን የተሰኘው የገበያ ጐዳና ላለፉት በርካታ ዓመታት ከ138 ውድ የችርቻሮ መዳረሻዎች ቁንጮ ላይ ከነበረው የላውዮርኩ አምስተኛው ጐዳና መሪነቱን መረከቡን ኦዲት ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

በአሜሪካ የሚገኘው ኩሽማን እና ዊክፊልድ የተሰኘው ኩባንያ መረጃ በመሰብሰብ በየዓመቱ ውድ የገበያ ጐዳናዎችን ከሚይዙት የቦታ ኪራይ ዋጋ አንፃር ደረጃ በመስጠት ለህትመት ያበቃል፡፡ ኩባንያው ለንባብ ባበቃው ህትመት ባለፉት በርካታ ዓመታት የመሪነት መንበሩን ይዞ ከቆየው የኒውዮርኩ አምስተኛው ጐዳና በጣሊያን ሚላን የሚገኘው ሞንቴናፓሊዮን ውድ የገበያ መዳረሻ ጐዳናን በአንደኛነት መቆጣጠሩን ይፋ አድርጓል፡፡

የሚላኑ ውድ የገበያ ጐዳና ርዝመቱ ከ400 ሜትር አይበልጥም፡፡ ይህም በራሱ ለገበያ ቦታው  ውድነት ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ በጐዳናው ላይ ያሉት የንግድ ድርጅቶች ልዩ፣ በስም የታወቁ፣ ዝናን ያተረፉ ምርቶችን ነው የሚቸበችቡት፡፡ ወደ ጐዳናው ለሸመታ የሚያመሩት ታዋቂ፣ ዝነኛ የኪነጥበብ ሰዎች፣ የእግር ኳስ ፈርጦች፣ ባለሀብቶች የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በሞንቴናፖሊዮን ጐዳና ተገኝተው የሚሸምቱ ዝነኞች ወይም ታዋቂ ግለሰቦች በአንድ ግዢ በአማካይ እስከ 330 ሺህ ብር እንደሚያወጡም ነው የተገለፀው፡፡

በሚላን የሚገኘው ውዱ የገበያ ጐዳና ካለፈው 2024 እ.አ.አ ወዲህ የቅንጦት ውድ የገበያ ጐዳና ብቻ ሳይሆን የጐብኝዎች መዳረሻም ሆኗል፡፡ ለዚህም ሁለት የፋሽን እና የንድፍ ስራዎች ትርኢት ማቅረቢያ ሣምንታት መዘጋጀታቸው እና በቀጣናው መስተናገዱ በምንክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

በሞንቴናፓሊዮን የገበያ ጐዳና ለንግድ ቦታ ኪራይ በአማካይ 20 ሺ ዩሮ ለአንድ ካሬ ሜትር ወይም ሁለት ሺህ ዶላር ለአንድ ካሬ ጫማ መክፈልን ግድ ይላል፡፡ ይህ በመሆኑም በገበያ ጐዳናው የሚገኝ የመሸጫ ቦታን የያዙት ስመጥር፣ ታዋቂ ምርቶች ለአብነት እንደ ናይክ፣ አዲዳስ… የመሳሰሉት መሆናቸው ነው የተጠቆመው፡፡ በውዱ የገበያ ጐዳና የመሸጫ ቦታን የያዙ አብዛኞዎቹ ድርጅቶች ከ50 እስከ 100 ሚሊዬን ዩሮ ለቦታ ኪራይ እንደሚያወጡ ነው በድረ ገጹ በማደማደሚያነት ለንባብ የበቃው፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here