ውጥረት እና ጭንቀት በመሠረታቸውም ሆነ፤ በሚያስከትሉት ጉዳት እና መፍትሄያቸው የተለያዩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ግን ለውጥረት የተጋለጠ አንድ ሰው “ምን ሆነህ ነው?” ተብሎ ቢጠየቅ ምላሹ “ተጨናንቄ” አልያም “ውጥረት ውስጥ ገብቸ” ሊለን ይችላል። ምክንያቱም ሁለቱንም እያቀያየሩ መጠቀም ተለምዷዊ ሆኗል፤ ይሁን እንጂ የተለያዩ ናቸው። እንዴት? ለሚለው ጥያቄ በዚህ ፅሑፍ ምላሽ ይሰጣል። ውጥረት ላይ ትኩት በማድረግም የመከሰቻ ምክንያቱ እና መፍትሄው በስፋት ይዳሰሳል።
ውጥረት /stress/- ጭንቀት /Anxiety/ በሚል የእንግሊዝኛውን ቋንቋ ፍች ይዘዋል። ውጥረት ሰውነታችን ለችግሮች እና ለጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ የሚያዘጋጅ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። በአብዛኛው የአጭር ጊዜ ክስተት ሲሆን ምላሹም ትኩረትን ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ውጥረት ግን የልብ ህመምን እና የበሽታ መከላከል አቅም ማዳከምን ጨምሮ ከባድ የጤና እክሎችን ያስከትላል። የሥራ ቀነ ገደብ፣ የገንዘብ እጦት፣ የትምህርት እና ሌሎች ፈተናዎች ጉዳይ … ጋር ተያይዞም ይከሰታል።
የተጨነቀ ሰው ደግሞ ብዙውን ጊዜ የምግብ መፈጨት ችግር ይገጥመዋል። ጭንቀት በአንጎል ውስጥ ይጀምራል፤ በመቀጠልም አንጀታችንን ጨምሮ ሁሉንም የሰውነታችንን ክፍሎች ይጎዳል። መደበኛ ያልሆነ የአንጀት እንቅስቃሴ፣ የሆድ ድርቀት፣ ተቅማጥ እና ሌሎችንም በርካታ የጤና ጫናዎች ያስከትላል። ከፍ ሲልም ጭንቀቱ የደም ግፊት፣ የልብ ድካም እና ሌሎች ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። ከሰዎች ጋር የሚኖረን ተግባቦትም ይታወካል። ከዋነኞቹ መንስኤዎች መካከልም የቅርብ ሰውን በሞት ማጣት፣ የገንዘብ ችግር፣ የተግባቦት ጉድለቶች … ይጠቀሳሉ። በድብርት መገለፅ የጀመረ ጭንቀት መፍትሄ ካልተዘየደለት ራስን በማጥፋት ሐይወትን እስከማሳጣት ያደርሳል። በእነዚህ መገለጫዎች የሁለቱን ልዩነት ከተገነዘብን ቀጣዩ ትኩረት ውጥረትን በጥልቀት መመልከት ይሆናል።
በውጥረት ዙሪያ ጥናት በማድረግ ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ ሃንስ ሴልዬ ነው። ውጥረትን በዘመናዊ መንገድ በማጥናቱም “የውጥረት አባት” እየተባለ ይጠራል። “The stress of Life” በሚለው መፅሐፉም ጎልቶ ይታወቃል። ሴልዬ “ውጥረት ሰውነት ለማንኛውም ግፊት የሚሰጠው አጠቃላይ ምላሽ ነው” ይላል። ይህም ማለት የሰው ልጅ (አካል እና አእምሮ) ከውጭ ወይም ከውስጥ ለሚመጣ ማንኛውም ግፊት (ውጥረት) ሲጋለጥ፤ ሁልጊዜ ተመሳሳይ ዓይነት የአካል እና አእምሮ ምላሽ ይሰጣል ማለት ነው።
ለውጥረት ከሚዳርጉን ምክንያቶች መካከል አንዱ ዝግጅት ሳያደርጉ የፈተና ወቅት መድረስ ነው። በዚህ ወቅት ውጥረት ይከሰታል። ይህም ፈተናውን በውጤታማነት መሥራት አልችልም የሚል የንቃት መጥፋትን አእምሮአዊ ውጥረት ይፈጥራል። ውጥረቱም ፍርሃት እና እረፍት ማጣትን ያስከትላል።
ከዚህ የውጥረት ችግር መውጫው መንገድ ደግሞ በጥናት መርሃ ግብር ላይ የተመሠረተ የፈተና ዝግጅት ማድረግ ነው። በውጥረት ምክንያት ከመረበሽ ይልቅ ከቅርብ ጓደኛ ጋር ለመፍትሄው መነጋገርም ይመከራል። በቂ እንቅልፍ ማግኘት፣ የአካል ማጎልበቻ እንቅስቃሴ ማድረግ እና ካፊን ነክ አነቃቂዎችን መቀነስም ተገቢ ነው። በነዚህ ዘዴዎች የውጥረቱን ግፊት መቀነስ ይቻላል።
ለውጥረት መከሰት ሌላኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ የሥራ መደራረብ ነው። የሥራ መደራረብ (role overload/work overload) የሚያስከትለው ውጥረት በሥነ ልቦና እና ድርጅታዊ ሥነ ልቦና (organizational psychology) ይገለጻል።
የሥራ መደራረብ ውጥረት ውስጥ ያስገባው ሰው አንድም ከአቅሙ በላይ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፤ አልያም በራሱ ድክመት ሥራ እንዲደራረብ አድርጓል። በዚህ ምክንያት የሥራ ጫና ውጥረት ይደርስበታል። ውጥረቱ አእምሯዊ ትኩረት ማጣትን ይፈጥራል፤ መርሳትን ያስከትላል፤ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አዳጋች ሁኔታን ይፈጥራል። በአካላዊ ውጥረት ደግሞ ድካም እና ራስ ህመምን ያስከትላል። የደም ግፊት መጨመርም ሊከሰት ይችላል። ብስጭት እና እርካታ መቀነስም ስሜታዊ መገለጫዎች ናቸው።
ከሥራ ጋር በተያያዘ ከሚከሰት ውጥረት ለመውጣት ደግሞ ሥራን ቅደም ተከተል ሰጥቶ መፈፀም፣ ሥራን በአቅም ልክ ተከፋፍሎ መፈፀም እና በአንድ ጊዜ አንድን ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው።
ግልፅ የሥራ መግለጫ፣ የጊዜ አጠቃቀም ግንዛቤን ማዳበር እና ለሰራተኞች የዕረፍት ጊዜ መስጠት ደግሞ በአንድ አሰሪ ድርጅት በኩል የሚከናወን፤ ድርጅታዊ ድጋፍ (organizational solutions) ተብለው ይገለጻሉ።
ለእንቅልፍ በቂ ጊዜ መስጠት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እና በቂ የእረፍት ጊዜን መፍጠር የሚሉት ደግሞ በሥራ ምክንያት ውጥረቱ እንዳይከሰት በግል የሚዘየዱ የመፍትሔ እርምጃዎች ተብለው ይገለጻሉ።
አብዛኛዎቹ አዋቂ /በእድሜ ከፍ ያሉ/ ሰዎች ከራስ ህመም እስከ መረበሽ የሚደርስ የውጥረት ምልክት በየጊዜው ያጋጥማቸዋል። ውጥረት የሥነልቦና እና ሥነ አካላዊ መዛባቶችን በማስከተል፣ የአእምሮ እና አካል ጤናን በመጉዳት መልካም ሕይወት መምራት እንዲያቅት ሊያደርግ ይችላል።
ውጥረት ለአጭር ጊዜ እና ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ በሚል በሁለት ተከፍሎ እንደሚታይ ደግሞ ቢቢሲ ዶት ኮም እ.አ.አ ነሐሴ 2025 ባወጣው ዘገባ ላይ አስገንዝቧል። ውጥረት ለአጭር ጊዜ ሲሆን ምላሽን ከፍ በማድረግ ውጤታማነትን ሊያሻሽል ይችላል። ይህም ማለት ለፈተና በቂ ዝግጅት ያላደረገ አንድ ተፈታኝ በአጭር ጊዜ ውጥረት በቂ ዝግጅት አለማድረጉን ይገነዘባል፤ ለመፍትሄውም ፈጥኖ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ያስችለዋል። ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ውጥረት ግን የልብ ህመምን እና የበሽታ መከላከል አቅምን ማዳከም ጨምሮ ከባድ የጤና እክሎችን ያስከትላል። በአግባቡ ከተያዘ አጣዳፊ ውጥረት ዘላቂ ጉዳት አያስከትልም። ግለሰቦች ለፈጣን ተግዳሮቶች ውጤታማ ምላሽ እንዲሰጡ ሊረዳቸው ይችላል። ሥር የሰደደ ውጥረት ግን በሰውነት ላይ ረዘም ያለ ጫና ይፈጥራል።
ውጥረት በሰውነት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ፤ የከካል ብቃት እንቅስቃሴ የጭንቀት ሆርሞንን በመቀነስ ጥሩ ስሜትን ከፍ ያደርጋል። ሜዲቴሽን (አረምሞ/ተመስጦ) ደግሞ አእምሮን ለማረጋጋት ያግዛል። ማኅበራዊ ድጋፍም ስሜታዊ ጥንካሬን በማጎልበት ውጥረትን ይከላከላል።
(ጥላሁን ወንዴ)
በኲር የጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


