በየዕለቱ ምሽት ላይ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴን መሥራት ከመጠን ያለፈ ውፍረት ላላቸው ሰዎች የሚያስገኘው የጤና ጠቀሜታ የላቀ መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡
በአውስትራሊያ የሲዲኒ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ሰላሳ ሺህ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎችን ለስምንት ዓመታት ተከታትለዋቸዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ በየቀኑ በተለያዩ ሰዓታት ደረጃ መውጣት፣ የእግር ጉዞ እና የጉልበት ሥራ የመሳሰሉትን እንዲሠሩ አድርገዋል፤ ከመጠን ያለፈ የወፈሩ ተሣታፊዎችን፡፡
ለበርካታ ዓመታት በምርምሩ ተሳታፊ ከሚሆኑ ሰዎች በምርመራ ተዛማጅ ችግር ወይም የጤና እክል ያለባቸውን ለይተዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡ በተዛማጅ ሌሎች የተወሳሰቡ የጤና እክል ያለባቸውንም ለይተው ከተሳታፊነት አውጥተዋቸዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የተለዩት 29 ሺህ 836 ጐልማሶች በወገባቸው ላይ በታሰረ ተለባሽ መለያ ለምን ያህል ደቂቃ የአካል ብቃት እንደሠሩ፣ እንዲሁም በቀን ስንት ሰዓት እንዳከናወኑ ጭምር መመዝገብ ችለዋል፡፡
የጥናትና ምርምር ቡድኑ በስኮትላንድ በተመሣሣይ መልኩ የተደረገ የናሙና ተሣታፊዎችን ውጤት አቀናጅቶ የማየት ተግባርንም ከውኗል፡፡
የምርምሩን ውጤት የበለጠ ታአማኒ እና ከግምታዊ አካሄድ የፀዳ ለማድረግ የሲጋራ እና የአልኮል ሱስ ተጠቂዎችን እንዲሁም የተለዩ ሱስ አስያዥ እና አደገኛ እጽ ተጠቃሚዎችን ለይተው ከናሙና ተሳታፊነት አውጥተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ረቀቅ ባለ ዘመናዊ ተለባሽ መሣሪያ ክትትል እና መረጃ ማሳባሰብ ችለዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡ በተሰበሰበው የመረጃ ትንተናየመረጃ መሰረት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በ24 ሰዓት ውስጥ የሚሰራበት ሰዓት በውጤቱ ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ነው የደረሱበት፡፡
በመሆኑም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያለባቸው ሰዎች ጠዋት እና ቀን ከሚሠሩት የአካል እንቅስቃሴ ይልቅ በምሽት መሥራት ለጤና ችግራቸው ፈውስ ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም