ዐይናማዉ “ዐይነስውር”

0
12

የ70 ዓመቱ ጣሊያናዊ ላለፉት 53 ዓመታት ዓይነስውር መስለው አንድ ነጥብ 16 ሚሊዬን ዶላር ለአካል ጉዳተኛ የሚሰጥ ድጐማን በማጭበርበር አግኝተዋል በሚል መከሰሳቸውን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት አስነብቧል፡፡

በጣሊያን የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች እንደዘገቡት በቪሴንዛ ከተማ ኗሪው የ70 ዓመት አዛውንት ከ1972 እ.አ.አ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር እንደሆኑ በማስመሰል ከአንድ ሚሊዮን ዩሮ በላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጥ ድጐማን ሲሰበስቡ ቆይተዋል፡፡

ግለሰቡ ላለፉት 53 ዓመታት ዓይነስውራን የሚይዙትን መለያ ቀጭን ብረት ይዘው ሲሻቸው  በውሻ  እየታገዙ ሲጓጓዙም ቆይተዋል፡፡

በዚሁ ሁኔታ ላይ ሳሉ የመኖሪያ ከተማቸው የቪሴንዛ ፓሊስ የግለሰቡ ሁኔታ አጠራጥሯቸው፣ መከታተል እና በምስል መቀረጫ “ካሜራ” እንቅስቃሴያቸውን ሰንዷል፡፡

የከተማዋ የፓሊስ መኮንኖች ግለሰቡ ቀደም ብለው ይሰሩበት ከነበረው ”አርዚናኖ” ከተሰኘ ኩባንያ ባልደረቦች ጋር ከሁለት ወራት በላይ ክትትል እና መረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባርንም ከውነዋል፡፡

መርማሪ ወይም ተከታታይ ፓሊሶቹ ቀደም ብሎ ግለሰቡ በመኖሪያ ጊቢያቸው ሆነ በገበያ ስፍራዎች አይተው ሲመርጡ፣ ገንዘብ ቆጥረው ሲከፍሉ በካሜራ ከቀረጹት ጋር አባሪ አድርጐ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቧል፡፡ ያለ አግባብ የሚሰበሰቡት ለጉዳተኞት የሚሰጥ ጥቅማ ጥቅም መታገዱንም አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም ተከሳሹ ከሰበሰቡት ህገወጥ ገቢ ለመንግሥት መክፍል የነበረባቸው  የቪሴንዛ አቃቢ ህግ ቢሮም “ዓይነሰውር ነኝ” በሚል መንግሥትን ባጭበረበሩት የ70 ዓመት አዛውንት ላይ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ መተላለፉ ነው በማጠቃለያነት ለንባብ የበቃው::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here