ዐይኖች ሁሉ ድጋሚ ወደ ቶኪዮ…

0
12

ከሠላሳ አራት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አትሌቲክስ  ሻምፒዮና ወደ ቶኪዮ ተመልሷል። ውድድሩም “ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና  ቶኪዮ  25”  በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በዚህ ታላቅ የአትሌቲክስ  መድረክ ከ200 ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች በ25 የውድድር ዓይነቶች እየተፎካከሩ ይገኛሉ፡፡  በውድድሩ ስድስት የስደተኞች ቡድንም እየተሳተፉ መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ አመልክቷል፡፡ 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና “እያንዳንዱ ሰከንድ አስደናቂ!” (“Every second, SUGOI”) በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ በዝግ ስታዲየም ከተካሄደ በኋላ የጃፓን ብሔራዊ ስታዲየም በአራቱም የዓለም ማዕዘን በመጡ ደጋፊዎች መሞላቱ ድግሱን አድምቆታል። ይህ ግዙፍ የአትሌቲክስ መድረክ 20ኛውን ምዕራፍ እያከበረም ይገኛል፡፡ ሻምፒዮናው የጃፓንን ጥንታዊ ባህል እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለዓለም እያሳየ ነው፡፡ የቶኪዮ 2025 የአትሌቲክስ  ሻምፒዮና ካስተዋወቃቸው አዳዲስ ነገሮች ውስጥ  የውድድር መርሀግብር ላይ የተደረገው ሥር ነቀል ማሻሻያ ነው። ይህ ማሻሻያ እያንዳንዱን የፍጻሜ ውድድር ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ የተመልካቾችን ስሜት ከፍ ዝቅ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ከዚህ ቀደም የመድረኩ ታላላቅ ፉክክሮች በመጨረሻዎቹ ቀናት ላይ ነበር የሚደረጉት። አዲሱ መረሀ ግብር ግን ቅዳሜ እና እሁድ (Super Weekend) በርካታ የፍጻሜ ውድድሮች እንዲከናወን በማድረግ መድረኩን አድምቆታል።

በሻምፒዮናው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንዶች እና የሴቶች የመቶ ሜትር የፍጻሜ ውድድሮች በአንድ ምሽት ማለትም በውድድሩ ሁለተኛ ቀን በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ተካሂዷል። ይህም የዓለም ፈጣን ወንድ እና ሴት አትሌቶች በአንድ መድረክ ላይ የሚታዩበትን ድራማዊ ምሽት ፈጥሯል። ለብዙ ዓመታት ውድድሩ በወንዶች 4×400 ሜትር የዱላ ቅብብል ፉክክር ነበር የሚጠናቀቀው ። በቶኪዮ ግን በከፍተኛ ፍጥነት እና ድራማ በሚታወቀው በወንዶች 4×100 ሜትር የዱላ ቅብብል ፍጻሜ ይዘጋል። ይህም መድረኩን ፈጣን እና አስደሳች መደምደሚያ ይሰጠዋል ተብሎ ይታመናል።

ሁሉም የጎዳና ላይ ውድድሮች (ማራቶን እና እርምጃ) ጠዋት ላይ  ብቻ ተካሂደዋል። ይህም  አትሌቶችን ከቀኑ ሙቀት ይጠብቃል፡፡ በተጨማሪም  በማታው መርሀግብር  በሚደረጉ የመም  እና የሜዳ  ተግባራት ውድድሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያስችላል። አዲሱ የውድድር መርሀግብር  እንደ ጦር ውርወራ፣ የምርኩዝ ዝላይ እና  ስሉ  ዝላይ  ያሉ  የሜዳ  ላይ  ተግባራት ከመም ውድድሮች  ጋር ሳይጋጩ  የራሳቸውን  የትኩረት  እንዲያገኙ በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቷል።  ሻምፒዮናው የተከፈተው በ4×400 ሜትር የድብልቅ የዱላ  ውድድር ሲሆን ወንድ እና ሴት አትሌቶች በጋራ የሚሳተፉበት በመሆኑ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ከውድድሩ መጀመሪያ ጀምሮ ያሳያል።

ቶኪዮ በቴክኖሎጂ ያላትን ዝና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን አስተዋውቃለች። የዓለም አትሌቲክስ ከሶኒ ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ለተመልካቾችም ሆነ ለዳኞች አዲስ ልምድ ለማቅረብ ሰፊ ሥራዎችን ሠርቷል። ሶኒ ለሻምፒዮናው አጋር በመሆን  የስርጭት ጥራትን እና የዳኝነት ሥራን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዘመናዊ መሣሪያዎችን አቅርቧል።

በውድድሩ ወቅት የሶኒ “አልፋ” (Alpha™) መስታወት አልባ ካሜራዎች እና “ጂ ማስተር” (G Master™) ሌንሶች ጥቅም ላይ አውሏል። እነዚህ መሣሪያዎች እጅግ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምስሎች እና ፈጣን ያልሆኑ እንቅስቃሴ (slow-motion) ቪዲዮዎችን ለመቅረጽ በማስቻል ተመልካቾች በቤታቸው ሆነው የእያንዳንዱን የአትሌት እንቅስቃሴ እና ስሜት በቅርበት እንዲመለከቱ ያስችላቸዋል።

የቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በታሪክ መዝገብ ላይ በውጤት ብቻ ሳይሆን ባስተዋወቃቸው መሠረታዊ ለውጦች የሚታወስ ይሆናል። ከአስደናቂ የመረሀ ግብር ማሻሻያ አንስቶ እስከ የላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድረስ፣ ይህ ሻምፒዮና የአትሌቲክስ ስፖርት ወደፊት ምን መምሰል እንዳለበት አመላክተዋል። ለአትሌቶች የተሻለ መድረክ ለተመልካቾች ደግሞ የማይረሳ ልምድ በመፍጠር የአትሌቲክስን አዲስ ዘመን አብስራለች።

የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የቀረበው የ”ኮዶ” ባህላዊ ከበሮ ትርኢት የዚህ ማሳያ ነው። “እያንዳንዱ ሰከንድ አስደናቂ!” (“Every second, SUGOI!”) የሚለው መሪ ቃልም የጃፓንን ባህላዊ መስተንግዶ እና ለአትሌቲክሱ ያላቸውን ጥልቅ ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው ተብሏል።

የዓለም አትሌቲክስ የማጣሪያ መስፈርቶችን ከወትሮው በተለየ ሕጉን ማሻሻሉ አይዘነጋም፡፡ ሃምሳ በመቶ የሚሆኑት አትሌቶች በቀጥታ የማጣሪያውን ሰዓት በማለፍ ነው ወደ ቶኪዮ ያቀኑት፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በዓለም ባላቸው ፈጣን ሰዓት እንዲያልፉ መደረጉ የውድድሩን ጥራት ከፍ አድርጎታል።

የአትሌቲክስ ስፖርት አፍቃሪዎችን ቀልብ ይስባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ውድድች መካከል  የአጭር ርቀት እና የረጅም ርቀት ፉክክሮች  ይገኙበታል፡፡  በሴቶች አጭር ርቀት የጃማይካ አትሌቶች የበላይነት ቢጠበቅም የአሜሪካ እና የአውሮፓ አትሌቶችም ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይገመታል። በረጅም ርቀት የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ትንቅንቅ የሻምፒዮናው ጌጥ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በወንዶች ምርኩዝ ዝላይ ስዊድናዊው ሞንዶ ዱፕላንቲስ የራሱን የዓለም ክብረ ወሰን ያሻሽላል የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡ _በጦር ውርወራ እና በስሉዝ ዝላይ የሚደረጉ ፉክክሮችም ትኩረት እንደሚስቡ መረጃዎች አመልክተዋል። በማራቶን ውድድር የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች የበላይነታቸውን ለማስቀጠል ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ።

የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በተለያዩ ዘመናት ገድላቸው እንደ አፈ ታሪክ የሚነገር  አስደናቂ አትሌቶችን እና መድረኩን የተቆጣጠሩ በርካታ ሀገራትን አሳይቶናል። አሜሪካዊቷ አሊሰን ፊሊክስ በሻምፒዮናው ታሪክ እጅግ  ስኬታማዋ አትሌት ስትሆን በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 11ዱ የወርቅ ሜዳሊያዎች መሆናቸውን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ድረገጽ ያስነብባል፡፡

የምንግዜም ምርጡ የአጭር ርቀት ሯጩ ዩሴን ቦልት 11 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከወንድ አትሌቶች በቀዳሚነት ተቀምጧል።  ሼሊ አን ፍሬዘር ፕራይስ  በመቶ ሜትር ርቀት አምስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ በመድረኩ ልዩ ታሪክ ያላት አትሌት ናት።  ፖርቹጋላዊው ጆአዎ ቪዬራ  በእርምጃ ውድድር   በ14 የዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ በመሳተፍ አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል። በስሉዝ ውርወራ የምትታወቀው ፈረንሳያዊት ሜሊና ሮበርትሚሾን በቶኪዮ ለ11ኛ ጊዜ በመሳተፍ የሴት አትሌቶችን ክብረወሰን ሰብራለች።

ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በሻምፒዮናው ታሪክ ፍጹም የበላይነት ያላት ሀገር ናት፡፡ እስከ 2023ቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ድረስ 183 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨምሮ በድምሩ 414 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ጎረቤታችን ኬኒያ 62 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ሩሲያ 41 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመያዝ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ኢትዮጵያ 36 ወርቅ በአጠቃላይ 104 ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ከዓለም ስድስተኛ እና ከአፍሪካ ከኬንያ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ውድድሩ ለቶኪዮ ከተማ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ይፈጥራል። ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ቱሪስቶች፣ ጋዜጠኞች እና ደጋፊዎች የቱሪዝም ዘርፉን ያነቃቃል። በተጨማሪም  ሻምፒዮናው በጃፓን ያሉ ወጣት አትሌቶችን በማነሳሳት ለአትሌቲክስ ስፖርት ያላቸውን ፍላጎት ያሳድጋል። “የጀርባ መድረክ መሪዎች!” (“Backstage Navigators!”) በሚል መረሀ ግብር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከዓለም ምርጥ አትሌቶች ጋር እንዲገናኙ እና ልምድ እንዲቀስሙ ዕድል ማግኘታቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

የቶኪዮ 2025 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የስፖርት ውድድር ብቻ አይደለም። ይልቁንም የዓለም ህዝብ በስፖርት አማካኝነት በፍቅር የሚሰባሰብበት፣ ባህሉን የሚለዋወጡበት እና ለቀጣዩ ትውልድ ተስፋን የሚሰጥበት ታላቅ ድግስ ነው።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here