ዓለማችንን እየናጣት የሚገኘው ርዕደ መሬት

0
131
A Wednesday, Jan. 13, 2010 aerial photo provided by The American Red Cross shows collapsed buildings following Tuesday's earthquake, in Haiti?s capital Port-au-Prince during a joint Red Cross Red Crescent/ECHO (European Community Humanitarian Organization) aerial assessment mission. (AP Photo/American Red Cross) MANDATORY CREDIT

የመሬት መንቀጥቀጥ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት የሚችል የተፈጥሮ አደጋ ነው። በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።

የመሬት መንቀጥቀጥ ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ከመሬት በታች ያለ ቋጥኝ በድንገት ሲሰበር እና በስህተት ፈጣን እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነው። ይህ ድንገተኛ የኃይል መለቀቅ መሬትን ያናውጣል። የመሬት መንቀጥቀጡ መጠን የሚለካው በሬክተር ስኬል ነው። ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል እስከ ሁለት የሚሆን ከሆነ እምብዛም አይሰማም:: ነገር ግን  መጠኑ ሰባት ከደረሰ በሰፊ ቦታ ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡

ከሰሞኑም በጃፓን ማዕከላዊ ኢሺካዋ ግዛት ከ45ሺህ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠባቸው ተገጧል፡፡

በሬክተር መለኪያ ሰባት ነጥብ አምስት የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስተናገደችው የጃፓን ማዕከላዊ ኢሺካዋ ግዛት 45ሺህ 700 የሚሆኑ ኗሪዎቿ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በኋላ በተነሳ እሳትም ከ100 በላይ ቤቶችና ሱቆች ተቃጥለዋል፡፡ እንዲሁም ከርዕደ መሬቱ በኋላ እስከ አራት ሜትር የሚደርስ የሱናሚ ማዕበል በሀገሪቱ ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ በርካታ አካባቢዎችን መትቷል።

የአውሮፓዊያኑ አዲስ ዓመት(2025) ከባተ በኋላ በቻይና የተከሰተው ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥም በምዕራብ ቻይናና በኔፓል አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን አውድሟል፡፡ እንዲሁም   በቲቤት ጎዳናዎች ደግሞ ፍርስራሾች ተበታትነው ቢያንስ 126 ሰዎችን ገድለዋል።

በቻይና እና በቲቤት ድንበር በኩል  ቢያንስ 188 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሺንሁዋ የዜና ወኪል ገልጿል። ይህ ዘገባ እከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በቻይና የመሬት መንቀጥቀጦች እየተከሰቱ ነበር፡፡

የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተ በኋላ በነበሩት ዘጠኝ ሰዓታት ውስጥ 150 ገደማ የሚሆኑ የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው እ.አ.አ. ከ1998 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት በተከሰቱ ርዕደ መሬቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ 750 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ሕይዎታቸው አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ125 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመሬት መንቀጥቀጥ ተጎድተዋል፡፡ ይህም ማለት በአደጋው ድንገተኛ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ቤት አልባ ሆነዋል ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ከምድር የሚመነጨው የንዝረት እና የመንቀጥቀጥ ኃይል  ውጤት የሆነው የርዕደ መሬት መንቀጥቀጥ  የመሬት መንሸራተት፣ ሱናሚን ፣ የሕንፃዎች ጉዳት እና በውኃ መጥለቅለቅን እንዲሁም ነደድ እሳትን ያስከትላል፡፡

ከውቅያኖስ ወለል በታች የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ሱናሚን ሲያስከትሉ እነዚህ ሞገዶች በባሕር ዳርቻዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ። አንዳንድ ጊዜ በሱናሚ ምክንያት የደረሰው ጉዳት የመሬት መንቀጥቀጡ ካስስከተለው ጉዳት የከፋ ሊሆን ይችላል።

የመሬት   መንቀጥቀጥ የመሬት መንሸራተትን ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በተጎዳው አካባቢ በሚገኙ ሕንፃዎችና ሌሎች መዋቅሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም መንገዶችን ሊዘጋና በመጓጓዣና በመገናኛ መስመሮች ላይ ሌሎች መስተጓጎልን ይፈጥራል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የጋዝ መስመሮችን እና የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ላይ ጉዳት በማድረስ   እሳት እንዲፈጠር ሊያደርግም ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እሳቱ ከመሬት መንቀጥቀጡ የበለጠ ጉዳት ሲያስከትል ይስተዋላል፡፡

ከመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ ደካማ የንጽህና አጠባበቅ ሁኔታ ስለሚኖር የበሽታ መስፋፋት ይኖራል፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ የውኃ መስመሮችን ሊጎዳ እና የአየር  ብክለትን ያመጣል። ግድቦችን  በማፍረስ ጎርፍ ያስከትላል፡፡ እንዲሁም ወሳኝ የሃይድሮፓወር መሠረተ ልማትን ሊያወድም ይችላል፡፡

የመሬት መንቀጥቀጥ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ከምክንያቶቹ መካከልም የመሬት መንቀጥቀጡ ጥንካሬ እና የቆይታ ጊዜ፣ በተጎዳው አካባቢ ያለው የአፈር እና የድንጋይ አይነት፣ ሕንፃዎች እና ሌሎች ግንባታዎች የተነደፉበት እና የሚገነቡበት መንገድን ጨምሮ ለሚደርሰው ጉዳት የሚሰጠው የአደጋ ጊዜ ምላሽ የጉዳት መጠኑ ከፍተኛ የመሆን ምክንያት ናቸው።

በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት የሚከሰተው መንቀጥቀጥ እጅግ በጣም ኃይለኛ እና ለብዙ ደቂቃዎች ሊቆይ ይችላል። መንቀጥቀጡ ሕንፃዎችን እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲታጠፍ እና እንዲደረመሱ ያደርጋል፡፡ ይህም ከፍተኛ ጉዳት እና የሕይወት መጥፋትን ያስከትላል፡፡

በተጎዳው አካባቢ ያለው የአፈር እና የድንጋይ አይነት የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያደርሰው የጉዳት መጠን ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለስላሳ አፈር እና ድንጋይ መንቀጥቀጥን ሊያሰፋ እና በሕንፃዎች እና ሌሎች መዋቅሮች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መጠንም ይጨምራል፡፡ የተራቆተ እና ለም አፈር ያላቸው ቦታዎች በተለይ ለጎርፍ መጥለቅለቅ የተጋለጡ ናቸው፡፡

ሕንፃዎችና ሌሎች ግንባታዎች የሚቀረጹበትና የሚሠሩበት መንገድ በመሬት መንቀጥቀጥ የሚደርሰውን ጉዳት መጠን ሊወስን ይችላል። የመሬት መንቀጥቀጥ ኃይሎችን ለመቋቋም ያልተነደፉ ሕንፃዎች ሊፈርሱ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ በተጨማሪም የቆዩ (ያረጁ) ሕንፃዎች አሁን ያሉትን የግንባታ ደንቦች ስለማያሟሉ  በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ለጉዳት የተጋለጡ ናቸው።

ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው አካባቢዎች በመሬት መንቀጥቀጥ ለሚደርስ ጉዳት የበለጠ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሕንፃዎች ተጠጋግተው ሊገነቡ እና በውስጣቸው በርካታ ሰዎች ሊኖሩባቸው ስለሚችሉ በሚፈጠረው ርዕደ መሬት በርካታ ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡

በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ለመቀነስ የመሬት መንቀጥቀጡ ኃይሎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሕንፃዎችን እና ሌሎች መዋቅሮችን መንደፍ እና መገንባት እና የአደጋ ጊዜ ምላሽ እቅዶችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡

ጅኦሎጂ ሳይንስ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው አንዳንድ እንስሳት የመሬት መንቀጥቀጥን ለይተው ማወቅ ይችላሉ።  ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊት ውሾች እና ድመቶች ከመጠን በላይ በመጮህ ወይም እረፍት በማጣት   እንግዳ ባህሪ እንዳላቸው የሚያሳዩ ብዙ ሪፖርቶች ቀርበዋል። በአንዳንድ ሁኔታዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ከመከሰቱ በፊት የዱር እንስሳት ከአካባቢው ሲሸሹም ተስተውለዋል፡፡

ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊት ውሾች ያልተለመደ ባህሪ ያሳያሉ፡፡  ከመጠን በላይ ሊጮኹ፣ ሊያለቅሱ ወይም ሊበሳጩ ይችላሉ። አንዳንድ ውሾች ደግሞ ወደ ውጭ ለመውጣት እና የመደበቂያ ቦታ ሲፈልጉ ተስተውሏል፡፡

ድመቶች ልክ እንደ ውሾች  ከመሬት መንቀጥቀጥ በፊት እረፍት ያጣሉ፤ እንዲሁም ይቅበዘበዛሉ።  ከወትሮው በላይም የሰውነታቸው ጸጉር ይቆማል፤ ባልተለመዱ ቦታዎችም ሊደበቁ ይችላሉ። አንዳንድ ወፎች ደግሞ ከመሬት መንቀጥቀጥ በፊት ጫጫታቸውን አቁመው በዝምታ ይዋጣሉ፡፡

በወንዞችና በሐይቆች ውስጥ ያሉ ዓሳዎችም ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊት እንግዳ ባህሪ ሲያሳዩ ተስተውሏል። ከውኃው ውስጥ ዘልለው ሊወጡ ወይም ባልተለመደ መልኩ ሲዋኙ ታይተዋል፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ዝሆኖች የመሬት መንቀጥቀጥ ይሰማቸዋል፡፡ ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊትም እረፍት አልባ ይሆናሉ፤ ወይም ድምጽ ያሰማሉ።

በምድራችን እጅግ ገዳይ የሆኑ የመሬት መንቀጥቀጦች በተለያዩ አህጉራት እና በተለያዩ ዘመናት ተከስተዋል፡፡ እያንዳንዱም በተጎዱ ክልሎች ላይ  ጥፋትን እና ዘላቂ ሀዘንን  አሳርፈው አልፈዋል፡፡

ለአብነትም በአውሮፓዉያን የዘመን ቀመር ጥር 23/1556 ማለዳ ላይ በቻይና ሻንዚ ግዛት   የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል ስምንት ነጥብ ዜሮ የሚገመት ሲሆን የ830ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

ይህ አሰቃቂ የመሬት መንቀጥቀጥ 836 ኪሎ ሜትር  ስፋት ያለው በመሆኑ  የሃዋሲያን፣ ዌይናን እና የሁዋይን አውራጃዎችን ጨምሮ አወድሟል። በበርካታ አውራጃዎች ላይ ቀጥተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ብዙ ሰዎች ይኖሩባቸው የነበሩ በደንብ ላልተገነቡ ሕንፃዎች እና ዋሻዎች መፍረስም ምክንያት ሆኗል።

እ.አ.አ በሐምሌ 28 /1976 በቻይና በታንግሻን ግዛት በሬክተር ስኬል ሰባት ነጥብ አምስት በተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ  ደግሞ ከ242ሺህ   እስከ 655ሺህ ሰዎች ሕይዎታቸው ማለፉ  ይገመታል፡፡ ለሰኮንዶች በቆየው ርዕደ መሬት አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች የነበሯትን የታንግሻን ግዛት እንዳልነበረች አድርጓታል፡፡ በወቅቱ የነበረው የነፍስ ማዳን ሥራው ለሟቾች መበራከት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

እንዲሁም በአውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ጥር 12/2010 በሄይቲ የተከሰተው  የመሬት መንቀጥቀጥ ከ200ሺህ በላይ ሰዎችን ገድሏል፡፡ ዋና ከተማዋን ፖርት-አው-ፕሪንስን አወድሟል፡፡  በመሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎችን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ በዘገባው እንዳመላከተው የመሬት መንቀጥቀጥ አሊያም ከፍተኛ ንዝረት ሲከሰት ቤት ውስጥ ከሆናችሁ በፍጥነት ከለላ መፈለግ እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ በቀላሉ የማይሰበር ጠረጴዛ ካለ መንቀጥቀጡ እስኪያባራ እዚያ ሥር መከለልን ይመከራል። ካልሆነ ደግሞ ጭንቅላትን በክርን  ሸፍኖ ያሉበት ቤት ጥግ ላይ መሸሸግን ይመከራል።

ጋዝ ካለበት፣ ከመስታወት፣ ከበር እና ከግድግዳ ውጭኛው ክፍል በአጠቃላይ ሊወድቁ ከሚችሉ ቁሶች አካባቢ መራቅ ይመረጣል።

አልጋ ላይ ካሉ ደግሞ እዚያው እንዲሆኑ ያስጠነቅቃል። ጭንቅላትን በትራስ መሸፈንንም ይመክራል።

ባለሙያዎቹ በመሬት መንቀጥቀጥ ጊዜ አሳንሰር በፍጹም እንዳይጠቀሙ ይመክራሉ፤ ድንገት አሳንሰር ውስጥ ካሉም በፍጥነት መውጣት ይኖርበዎታል፡፡

ርዕደ መሬት ሲከሰት ከቤት ውጭ ከሆኑ ደግሞ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌክትሪክ፣ ከስልክ ገመዶች እና ከመንገድ መብራቶች መራቅ እንዳለበዎት ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

በመሬት መንቀጥቀጥ ጊዜ ከፍተኛ አደጋ ሊኖር የሚችለው ሕንፃዎች አካባቢ ነው። በተለይ በሕንፃ መውጫና እና መግቢያ አካባቢ መሆን አይመከርም። ምንም ነገር የሌለበት ገላጣ ሥፍራ ላይ ከሆኑ መንቀጥቀጡ እስኪቆም እዚያው ባሉበት መቆየት ይመረጣል።  ተሽከርካሪ ውስጥ ከሆኑ በተቻለ ፍጥነት አቁመው መንቀጥቀጡ እስኪቆም እዚያው ተሽከርካሪ ውስጥ ይቆዩ። ቢቻል ሕንፃዎች አካባቢ፣ ዛፎች  እና የኤሌትሪክና ሌሎች ገመዶች ባለቡት ሥፍራ ማቆም የለብዎትም።

መንቀጥቀጡ ከፍተኛ ከሆነ እና ፍርስራሽ ካለ አፍና አፍንጫን በመሀረብ መሸፈን ይመከራል።

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here