ዓለማችን ረሃብ ተጋርጦባታል

0
178

በየቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዐሥር ሰዎች አንድ ሰው እንደራበው ወደ መኝታው ያመራል፣ በአፍሪካ ደግሞ ከአምስት አፍሪካውያን አንዱ የከፋ ረሀብ ተጋርጦበት መገኘቱ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) እንዳስታወቀው።

ድርጅቱ ያወጣው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት እንደሚያሳየው በዓለማችን እስከ 783 ሚሊዬን ሕዝብ የከፋ ረሀብ ተጋርጦበታል። ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዐሥር ሰዎች መካከል አንድ ሰው ረሀብን ይጋፈጣል ማለት ነው።

በከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ ያሉ ልዩ ትኩረት የሚሹ ዐሥራ ስምንት አሳሳቢ ቦታዎች ያሉ ሲሆን ይህም 17 ሀገራትን ወይም ግዛቶችን እና አራት ሀገራትን የያዘ አንድ ቀጣናዊ ክላስተርን ያካተተ ነው። በማሊ፣ ፍልስጥኤም፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ያለው የስጋት ደረጃ ከፍተኛ በሚባል የተፈረጀ ሲሆን እንዲሁም ሀይቲ እየተባባሰ ከቀጠለው ብጥብጥ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የስጋት ደረጃ ምድቡን ተቀላቅላለች። እነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ ውድመት እና ጥፋት የሚፈፀምባቸው ሲሆኑ እጅግ አስቸኳይ ትኩረት የሚሻ ሕይወትን አደጋ ውስጥ በሚጥል የከፋ ረሀብ ውስጥ መሆናቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል።

ከወታደራዊ ግጭቶች እና ከመጠን ያለፈ የአየር ንብረት መዛባት ክስተቶች እስከ የኮቪድ ወረርሽኝ በዘላቂነት ባሳደራቸው ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ተፅዕኖዎች የዓለም አቀፋዊ የረሀብ መጠኑን ወደ አሳሳቢ ደረጃ የወሰዱት ምክንያቶች እንደሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። በተለይ በጦር መሳሪያ የታገዘ ብጥብጥ እና ግጭቶች ዋነኛ የችግሩ ምክንያቶች ናቸው። በእነዚህ አሳሳቢ ሁኔታዎች እየተስፋፋ ያለ መፈናቀል፣ የምግብ ሥርዓቶች መውደም እና የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት መቀነስ የከፋ የምግብ አቅርቦት እንዳይኖር በማድረግ ችግሩን እያወሳሰበው እንደመጣ ተገልፅጿል።

“አሳሳቢ የምግብ ዋስትና ችግር ስንል፣ ቤተሰብን እና ሕይወትን በአፋጣኝ አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችለው አስከፊ ረሀብ ማለታችን ነው። ይህ ረሀብ ወደ ጠኔ ደረጃ እከፋ በመሄድ አያሌ ሞት የማስከተል አቅም ያለው ቀውስ ነው” በማለት የዓለም ምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ዶሚኒክ በርገን የችግሩን አሳሳቢነት ገልፀውታል።

በተቀናጀ ግጭት እና አለመረጋጋት የከፋ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ቡርኪናፋሶ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ሀይቲ፣  ማሊ፣ ሚያንማር፣ ኒጀር፣ ፍልስጥኤም፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ የመን እና ሱዳን ይጠቀሳሉ።

ተቀማጭነቱ በጄኔቫ የሆነው የዓለም ምግብ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ጊያን ካርሎ ሲሪ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ሰዎች በግልፅ በረሀብ እየሞቱባቸው ባሉት ጋዛ እና ሱዳን ትኩረት ይሻሉ። እስራኤል ድብደባ ማድረግ ከጀመረች ከሰባት ወር በኋላ “የጋዛ ሕዝብ መሰረታዊ የምግብ ፍላጎቶችን ማሟላት እንኳ አልቻሉም። ችግሩን መቋቋም የሚያስችሏቸውን ሁሉንም መንገዶች ሞክረዋል፣ ለአብነት የእንስሳትን ቆዳ እስከ መብላት፣ ልመና፣ ያላቸውን ሁሉ ንብረት ለምግብ መግዢያ ሸጠው ባዶ እስከ መቅረት ደርሰዋል። የተወሰኑት በረሀብ እየሞቱ ይገኛሉ” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ዳይሬክተሩ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የጠና አደጋውን ለማስቆም ብቸኛው መንገድ በጣም አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ  በየቀኑ የምግብ አቅርቦት የሚኖርበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ነው። በጋዛ የተሰማው አዲሱ ማስጠንቀቂያ የከፋ የሚባለው ረሀብ በማንኛውም ጊዜ ሊከሰት እንደሚችል ነው። ለዚህም ምልክቶች እየታዩ መሆኑ እየተገለፀ ሲሆን አፋጣኝ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

በከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት እስካሁን እየታመሰች ያለችው ሱዳን ለከፋ የረሀብ አደጋ ተጋልጣ እንደምትገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዓለም እስካሁን አይታው የማታውቅ አይነት ሚሊዮኖችን ለእልቂት የሚዳርግ ከባድ የረሀብ አደጋ እያንዣበበ መሆኑን አሜሪካ በቅርቡ ለተመድ ጉባኤተኞች ስጋቷን ማሰማቷ ይታወሳል። ባለፈው ዓመት የ20 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሱዳናውያን፣ ወይም 42 በመቶው የሀገሪቱ ሕዝብ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከባድ ትግል ውስጥ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ያረጋግጣል። ይህ ቁጥር በዓለም አስቸኳይ ድጋፍ ከሚያስፈልገው የምግብ ዋስትና ችግር ላይ ካለው የዓለም ሕዝብ መሀል ከፍተኛው ቁጥር ነው።

በወታደራዊ አንጃዎቹ መካከል ውጥረቱ እየተባባሰ ባለበት ሀገሪቱ አይታው የማታውቀው የከፋ የምግብ እጦት አደጋ እንደተጋረጠባት ግሎባል ሀንገር ሞኒተር ገልጿል። አልጀዚራ እንደዘገበው ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ ካስቆጠረው ጦርነት በኋላ ከ755 ሺህ በላይ ሱዳናውያን እጅግ አስከፊ የሚባል  የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ለጎን 8 ነጥብ አምስት ሚሊዬን የሚሆነው ሕዝብ ለከባድ የሥርዓተ ምግብ መቃወስ እና ለሞት ሊያበቃ ከሚችል የምግብ እጥረት አደጋ ጋር እየተጋፈጠ ይገኛል።

በዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ መሠረት በሱዳን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሱዳን ውስጥ ተፈናቅሎ ይገኛል። ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዬን ሕዝብ ደግሞ ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዋል። በአሁኑ ወቅት ሱዳን ካላት 48 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ሩብ ያህሉ ቀየውን ለመልቀቅ ተገድዷል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን አቋርጠው ከሀገር መውጣታቸው ተጠቁሟል።

የዓለም ምግብ ፕሮጀክት ሪፖርት እንዳሳሰበው በሱዳን ተጨማሪ የተባባሰ ሁኔታ እንዳይከሰት በመላው ሱዳን የሰብዓዊ እርዳታ በአፋጣኝ እንዲደርስ መደረግ አለበት። ሪፖርቱ አክሎም በደቡብ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ሶማሊያ እና ማሊ የሚገኙ ሕዝቦች ከፍተኛ የምግብ እጥረት አደጋ ውስጥ መሆናቸውን በመጠቆም የችግሩን አሳሳቢነት አስጠንቅቋል።

በሌላ በኩል በዓለም የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የረሀብ መጠኑን እንዲያሻቅብ እያደረጉት ነው። የተፈጥሮ አደጋዎቹ የዓለምን የአየር ንብረት ሁኔታ በማዛባት ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ተያያዥ የረሀብ አደጋ የተጋረጠባቸው አካባቢዎች መበራከታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት ያሳያል። ከመጠን ያለፈ ዝናብ በጣለባቸው አካባቢዎች የተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች በርካቶችን በማፈናቀል እና የሕይወት አደጋ በማድረስ ሕዝቡን ለከፋ የረሀብ ችግር እንደዳረጉት በሚገልፀው በዚሁ ሪፖርት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሀይቲ፣ ሳህል፣ ቻድ፣ ማሊ፣ ናይጀሪያ እንዲሁም ሱዳን ተጋላጭ መሆናቸው ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ምክንያቶች የተነሳ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በዓለማችን በከፍተኛ የረሀብ አደጋ ውስጥ ይገኛል። ችግሩ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደበት እየተወሳሰበ እንደሚቀጥልና የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ተመድ እያሳሰበ ይገኛል። ከዓለም የምግብ እጥረት ሰለባዎች ውስጥ አፍሪካ 20 በመቶውን ትሸፍናለች፣ እስያ ስምንት ነጥብ አንድ በመቶ፣ ላቲን ስደስት ነጥብ ሁለት በመቶውን እንደሚሸፍኑ ጥናቶች አሳይተዋል። “የረሀብ ቀውሱ ከፍተኛ በሆነበት፣ በርግጥም ረሀብን እና ከሥርዓተ ምግብ ጋር ተያያዥ ቀውሶችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ የማድረግ ዕድሉ በእጃችን ነው” በማለት የዓለም አቀፉ ሃንገር ሪስፖንስ ፎር ወርልድ ቪዥን ዳይሬክተር ሜሪ ንጀሪ በተናገሩት ቃላት ትንታኔያችንን አበቃን።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ጥቅምት 18  ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here