“ዓለማችን ደስታን እና ሀዘንን ስታስተናግድ ሁለቱም ነገሮች መገለጫቸው ኪነ ጥበብ ነው”

0
209

በክፍል አንድ የእንግዳ አምድ እትማችን ከከያኒ በምናቡ ከበደ ጋር ቆይታ አድርገናል:: በቆይታችንም ከያኒ በምናቡ የት ተወልዶ እንዳደገ፣ የትምህርት እና የሥራ ሁኔታውን፣ የኪነ ጥበቡን ዓለም እንዴት እንደተቀላቀለ፣ ምን ያህል ድራማዎችን እና ፊልሞችን ለአድማጭ ተመልካቾች እንዳበረከተ፣ በገጠር ተውኔቶች ላይ ለማተኮሩ ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ የጐጆ መውጫ ድራማ መነሻ ሃሳብ እና አሠራሩ እንዴት እንደሆነ እና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስተንለት ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎችን ሰጥቶናል::

ከያኒ በምናቡ ከበደ ጋር በክፍል ሁለት ቆይታችንም የተለያዩ ጥያቄዎችን እያነሳን ቆይታ አድርገናል፤

መልካም ንባብ!

 

የውጭ ፊልሞች እና ድራማዎች በሀገራችን ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ ምን ተፅዕኖ አሳድረዋል?

በእኔ ሃሳብ እንደ ቃና ያሉ ተከታታይ የትርጉም ድራማዎች ወደ ሀገራችን ሲገቡ  በነበሩት ቲያትሮች፣ ድራማዎች እና ፊልሞች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ የሚል ሥጋት ነበረኝ፤ እነዚህ ፊልሞች እና ድራማዎች የቀረፃ ጥራታቸው በጣም የሚያምር እና ለእኛም ሀገር  የኪነ ጥበብ ሥራዎች አርዓያ መሆን የሚችሉ ናቸው:: እውነታው ግን በነዚህ ፊልሞች አማካይነት የሚተላለፉት መልዕክቶች ፊልሞቹን የሠሩትን ሀገራት ባህል እና ትውፊቶችን የሚያንፀባርቁ የውጭ ፊልሞች እና ድራማዎች በሀገራችን ውስጥ በስፋት መታየት ሲጀምሩ የኛን ሀገር የጥበበ ሥራዎች ከገበያ ያስወጧቸዋል የሚል ሥጋት ከነበራቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ፤ በሂደት የታየው ውጤት ግን እሱ አይደለም::

ሰዎች ፊልሞችን ወይም ድራማዎችን የሚያዩት ለስሜታቸው የሚቀርበውን በመምረጥ ነው፤ ቃና እንደተጀመረ አካባቢ ብዙ የቤተሰብ አባላት ብዙ ተከታታይ ድራማዎችን ይከታተሉ ነበር፤ እናቶች እና የቤት ሠራተኞች ምግብ ማብሰያ ጊዜ እስኪያጡ ድረስ ለቃና ድራማዎች ጊዜያቸውን ሰጥተውም ነበር:: አሁንስ? ብለህ ብትጠይቀኝ ግን ቃናን የሚመለከተው ሰው እንደበፊቱ ቁጥሩ የበዛ አይደለም:: ይህ የሆነው ደግሞ ቃናን ማየትም ሆነ ማሳየት በሕግ ታግዶ ሳይሆን በቃና ውስጥ የሚተላለፉት መልዕክቶችም ሆኑ የሚታዩት ተግባራት ለኢትዮጵያዊ ሕይወት የቀረቡ ባለመሆናቸው ነው:: በዚያ ላይ በቃና የሚተላለፉት ተከታታይ ድራማዎች የአብዛኛዎቹ ጭብጦች ተቀራራቢነት ያላቸው በመሆኑ በሂደት ተመልካቾችን ከማዝናናት ይልቅ ወደ ማሰልቸት ሄደዋል የሚል የራሴ ግምገማ አለኝ::

እንደ ቃና ካሉ ተከታትይ ድራማዎች እኛ የሙያው ሰዎች ብዙ ነገሮችን ልንማርባቸው እንችላለን:: ተከታታይ ድራማዎች በንግግር ሳይሆን በድርጊት ሲታጀቡ ምን ያህል የሰዎችን ትኩረት እንደሚስቡ ዐይተንባቸዋል:: የድራማ እና የፊልም ጥራት ተመልካችን ምን ያህል እንደሚስቡም ከተከታታይ ሥራዎቹ መረዳት ይቻላል:: በአጠቃላይ ግን የውጭ ፊልሞች እና ድራማዎች በሀገራችን ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ሳይሆን አስተማሪ የሆኑ ነገሮችን ይዘው እንደመጡ አምናለሁ:: ለድራማዎቹ በሚሰጠው የበዛ ጊዜ ምክንያት በቤተሰብ ውስጥ ይፈጠር የነበረውን አለመግባባት ደግሞ በመጥፎ ጐኑ ማየት ይቻላል::

 

ለሙያህ አርዓያ ያደረካቸው ሰዎች እነማን ይሆኑ?

በወሎ ኪነ ጥበብ ውስጥ አስተዋፅኦ ከነበራቸው የያኔዎቹ ከያኒያን ውስጥ እኔ ፍስሐ በላይን አርዓያዬ አድርጌዋለሁ:: ፍስሐ በላይ “አልቃሽ እና ዘፋኝ” የሚል ቲያትር ነበረው፤ እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ቲያትርም ይሄው አልቃሽ እና ዘፋኝ የተባለውን የፍስሐ በላይን ሥራ ነው:: አልቃሽ እና ዘፋኝ ቲያትር የሚገርም ፍልስፍና ያለበት ቲያትር ነው:: በዚህ ቲያትር ውስጥ በአንድ ቤት ውስጥ አስለቃሽ እና ዘፋኝ ወይም ሕይወት እና ሞት የሚታይበት በመሆኑ ከተዝናኖት ባለፈ በቲያትሩ ውስጥ ብዙ ፍልስፍናዎችን አይቼበታለሁ::

በቲያትሩ ዘርፍ ውድነህ ክፍሌን አለማድነቅ አይቻልም፤ ውድነህ ክፍሌ ማለት ለኔ የቲያትሮች መሀንዲስ ማለት ነው:: እሱ የሠራቸው እነ ባቢሎን በሳሎን፣ የቼዝ ዓለም፣ ቤርሙዳ እና ሌሎችም የውድነህ ክፍሌ ሥራዎች ብዙ ነገር የምታውቅባቸው ብቻ ሳይሆኑ የምትማርባቸውም ጭምር ናቸው:: ከተዋናይ ደግሞ እነ ሽመልስ አበራ እና አልዓዛር ሳሙኤልን የመሳሰሉ ተዋናዮች ፈጥነው ወደ ውስጤ ገብተዋል::

በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ውስጥም እንደ ስለሺ አምባው ያሉ ደራሲዎች፣ ግዮን ዓለምሰገድ፣ መላኩ ታደሰ፣ ደሳለኝ ድረስ እና ሌሎችም ተዋናዮች ችሎታቸው ላቅ ያለ መሆኑን በቅርባቸው ሆኜ አይቻለሁ:: አብረውኝ ከሠሩት ውስጥ ደግሞ ተስፋ ብርሃን በግጥም ሥራዎቹ በጣም የማደንቀው ነኝ:: “ጭስ አልባው ነዳጅ “(ስለ ህዳሴው ግድብ)  የሙዚቃ ግጥም የሠራውም ተስፋ ብርሃን ነው::

 

በሀገራችን ውስጥ ኪነ ጥበብ እያደገ ነው ወይስ አይደለም? ካላደገ ምክንያቱ ምን ይሆን?

የሀገራችንን ኪነ ጥበብ እያደገ ነው ወይም አይደለም ብሎ ለመፈረጅ ጥናቶች ያስፈልጋሉ፤ ጥናቶች ሳይኖሩ እና መለኪያ መስፈርቶች ሳይዘጋጁ ኪነ ጥበባችንን አድጓል ወይም አላደገም ማለት አይቻልም:: የሀገሪቱን የኪነ ጥበብ ሁኔታ ወደ ራሴ አቅርቤ ሳየው ግን ምቹ ሁኔታዎች እንዳልተፈጠሩ መግለፅ እችላለሁ:: ለአብነት እኔ በእጄ  ላይ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የድራማ ጽሑፎች (ስክሪኘቶች) ይገኛሉ፤ እነዚህን ጽሑፎች ለተመልካች ማድረስ አለመቻሌ ለኪነ ጥበቡ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎች እንደሌሉ ማሳያ አድርጌ እወስደዋለሁ::

በአንድ ወቅት በጥሩ ሥራዎቻቸው ቀና ብለው ያየናቸው ከያኒዎችም አሁን ላይ አጐንብሰዋል፤ የኪነ ጥበቡ ዓለም ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ ዘርፍ ነው:: በኢትዮጵያ አውድ እንየው ካልን ግን ኪነ ጥበቡን የሚደግፉ ባለ ሀብቶች የሉም፤ የኪነ ጥበብ ሙያተኞች መልካም ሃሳብ እንጂ ገንዘብ የላቸውም፤ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ዘርፉን አይደግፉትም::

የሀገራችንን ኪነ ጥበብ እስከወዲያኛው ጨለማ አድርጌ ማሰብም አልፈልግም፤ ምክንያቱም እንደ ዲ ኤስ ቲቪ ያሉ የመገናኛ አውታሮች ለኪነ ጥበቡ እና ለሙያተኞቹ ጥሩ ክፍያ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ:: እነዚህ ማሰራጫ ጣቢያዎች (ቻናሎች) በገበያው ላይ መታየትን ለማትረፍ ሲሉ በርከት ያሉ ኪናዊ ሥራዎችን እየገዙ እና እያስተላለፉ ይገኛሉ፤ እንደዚህ ዓይነት ተስፋዎችን ሳይ የሀገራችን ኪነ ጥበብ ሊያድግ ይችላል፣ ሙያውም ብዙ ተከታዮችን ያፈራል ስል ተስፋ አደርጋሁ:: እስከዚያው ግን የሀገራችንን ኪነ ጥበብ አድጓል ወይም አላደገም ለማለት ድፍረቱ የለኝም::

 

ኪነ ጥበብን ለማሳደግ ከማን ምን ይጠበቃል?

ኪነ ጥበብን ለማሳደግ የብዙ አካላት ተሳትፎ ያስፈልጋል፤ ያም ቢሆን ግን የላቀውን ድርሻ መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው:: ሱዳንን እንደ አብነት ባነሳ እነ ሰኢድ ከሊፋ እና መሀመድ ወርዲ የተባሉት አቀንቃኞች በነበሩበት ወቅት በብዙ ዓለም የምትታወቀው ሱዳን እና የአሁኗ ሱዳን ተመሳሳይ አይደሉም::

እዚህ ላይ የምንገነዘበው ኪነ ጥበብ ለመልካም ገፅታ ግንባታ ያላትን ጉልህ አስተዋፅኦ ነው:: በእኛም ሀገር የአብዮት ወይም የለውጥ ወቅት ላይ ብዙ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ያቆጠቁጣሉ፤ አብዮቱ ወይም ለውጡ መረጋጋት ሲጀምር ደግሞ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ድራሻቸው ይጠፋል:: ኪነ ጥበብን በግለሰቦች ጥረት ወይም በውድድር ብቻ ማሳደግ ይቻላል የሚል እምነቱ የለኝም:: የሀገራችን የተለያዩ መንግሥታት ኪነ ጥበብን ለኘሮፓጋንዳ በመጠቀም ያኙትን ጥቅም እያሰሉ፣ ኪነ ጥበብን ለሀገር እድገትም እንደ መሣሪያ መጠቀም እንደሚቻል መገንዘብ ይኖርባቸዋል:: የኪነ ጥበብ ሙያ ብዙ ወጪን የሚፈልግ በመሆኑም የመንግሥትን የበጀት ድጋፍ የግድ ይሻል::

የኪነ ጥበብ መድረኮች በሚዘጋጁባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የሚታደሙትን ሰዎች ብዛት እያየን ነው፤ ይሄንን ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች ማሻገር ቢቻል ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆነው ሁሉም ማህበረሰብ እና መንግሥት ጭምር ነው:: ዓለማችን ደስታን እና ሀዘንን ስታስተናግድ ሁለቱም ነገሮች መገለጫቸው ኪነ ጥበብ ነው::

ለኪነ ጥበብ ሥራ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ካሜራዎች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች እና ሌሎችም ከውጭ ሀገር የሚገቡት በውድ ዋጋ ነው:: እነዚህን መሣሪያዎች ከውጭ አስገብቶ ሥራ ላይ ለማዋል ደግሞ ሙያተኛው የገንዘብ አቅም የለውም፤ ስለዚህ ባለሀብቶች እና መንግሥት ዘርፉን የግድ ማገዝ አለባቸው::

 

የማልረሳው የምትለው ገጠመኝ ይኖርሀል?

“ዋሸራ” የተባለ ሥራን ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ስሠራ የአብነት ተማሪዎች በሚገቡባቸው ትናንሽ ጐጆዎች ውስጥ ለመግባት ሞክሬ ያልተሳካልኝን፣ ቁራሽ ልለምን ስዞር በውሻዎች የተባረርኩትን እና መሰል የሥራ ገጠመኞቼን አልረሳቸውም:: ከውትድርናው ዓለም ወጥቼ በግል የፒያኖ ተጫዋች ሆኜ ስሠራ አሠሪው ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ የጋበዘኝ ራት በጣም ውድ የሆነውን ነበር፤ በሁለኛው ቀን ደግሞ በዋጋው ከመጀመሪያው ቀን ቀነስ የሚል ራት ተጋብዣለሁ፤ በሦስተኛው ቀን ደግሞ ከሁለቱ ቀናት በዋጋ ቀነስ የሚል እና ርካሽ ምግብ መጋበዜን አስታውሳለሁ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ የክበቡ አባል ስለሆንኩኝ ራት የሚቀርብልኝ እንደማንኛውም ሠራተኛ መሆኑ ተነግሮኛል:: በእኛ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረግልህን አቀባበል በሌላ ጊዜም አገኛለሁ ብለህ ማሰብ እንደሌለብህ ያስተማረኝን አጋጣሚ ከዚህ ሁኔታዬ አይቻለሁ::

 

ኪነ ጥበብ ለሀገር ሰላም መሆን ምን ማበርከት ይኖርባታል?

ኪነ ጥበብ የሀገር ሰላም ከሌለ መኖር የማትችል እና ህልውናዋ የሚያከትም ናት:: ይሄንን በተጨባጭ ለማረጋገጥ ደግሞ ከኛ ሀገር የተሻለ ምሳሌ አናገኝም:: ሀገራችን ሰላም በምትሆንበት ወቅት የኪነ ጥበብ ሥራዎች በብዛት ለሕዝብ ይደርሳሉ፤ ሀገር ሰላም ስታጣ ደግሞ ኪነ ጥበብም ቦታዋን ታጣለች:: ሰላም በሌለበት ሀገር ውስጥ ተንቀሳቅሶ መሥራት አስቸጋሪ ነው:: የሚስቁ ጥርሶችን ማየት ይቸግራል:: ሰላም ለኪነ ጥበቡ ብቻ ሳይሆን ለሁሉ ነገር መሰረታችን ስለሆነች አጥብቀን ልንፈልጋት ይገባል:: መንግሥትም ሆነ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ሰላም መሆን የድርሻውን መወጣት ይኖርባቸዋል:: በኪነ ጥበብ ሥራዎች ስለ ሰላም መስበክም የሙያተኞች ግዴታ መሆን ይኖርበታል::

 

ከጋዜጣችን ጋር ለነበረህ ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን!

እኔም ስለተሰጠኝ እድል በኲር ጋዜጣን እና አንተን አመሰግናችኋለሁ!

 

 (እሱባለው ይርጋ)

በኲር ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here