ዓለምን ያስጨነቀዉ የእስራኤል – ሃማስ ጦርነት

0
78

ዲፕሎማቶች ለእስራኤል እና ፍልስጤም የሁለት-ግዛት መፍትሄ ማምጣት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ (ጉባኤ) ለማድረግ መዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡ በመጪው ሰኔ ወር ለሚካሄደው ወሳኝ  ኮንፈረንስ መሰረት ለመጣልም በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ዋና መሥሪያ ቤት ከሰሞኑ ተሰብስበው ነበር።

የጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንት (ጉባኤውን በበላይነት የሚመሩት) ፊሊሞን ያንግ “ከዐሥራ ዘጠኝ ወራት በላይ በጋዛ ውስጥ የተመለከትናቸው አሰቃቂ ድርጊቶች የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነትን ለማስቆም አስቸኳይ እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል፡፡ ሞት፣ ውድመት እና መፈናቀልን የመሰሉ አስከፊ ዑደቶች እንዲቀጥሉ መፍቀድ የለብንም” ብለዋል፡፡

 

“ይህ ግጭት በዘላቂ ጦርነት ወይም ማለቂያ በሌለው ወረራ መፈታት አይችልም። የሚያበቃው እስራኤላዊያን እና ፍልስጤማዊያን በራሳቸው ሉዓላዊ፣ ገለልተኛ ግዛቶች፣ በሰላም፣ በደኅንነት እና በክብር አብረው መኖር ሲችሉ ብቻ ነው” ሲሉም አክለዋል።

ፈረንሳይን እና ሳዑዲ አረቢያን በመወከል ጉባኤው ላይ የሚገኙት ዲፕሎማቶች በሰኔ ወር የሚካሄደው ኮንፈረንስ መርሆችን ከማረጋገጥ ባለፈ ተጨባጭ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ያለውን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አማካሪ የሆኑት አኔ-ክሌር ሌጀንደር ከቃላት ወደ ተግባር በአስቸኳይ መንቀሳቀስ እንደሚገባ እና በጋዛ ያለውን ጦርነት ከማቆም ወደ ግጭቱ ራስ (መንስኤ) መሸጋገር እንደሚበጅ ነው የገለጹት፡፡ “በመሬት ላይ ካሉ እውነታዎች አንጻር የፍልስጤም የግዛት ተስፋዎች ሊጠበቁ ይገባልም ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም፣ የሰብአዊ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲገባ እና ታጋቾች እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የሳዑዲ አረቢያ ተደራዳሪ ቡድን መሪ ማናል ቢንት ሀሰን ሬድዋን ንጹሃን  ወዲያውኑ ማብቃት በነበረበት ጦርነት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ” ነው ያሉት፡፡ ጦርነቱን ለማቆም ብቻ ሳይሆን ለስምንት ዐሥርት ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማስቆም መነጋገር እንደሚገባ ነው  የጠቆሙት፡፡

በጠቅላላ ጉባኤው “የፍልስጤም ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና የሁለት-ግዛት መፍትሔ ትግበራ” በሚል ርዕስ የተግባር ተኮር የውጤት ሰነድ ይቀርባል። ዓላማው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎች መሰረት ወደ አጠቃላይ፣ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ግልጽ እና የማይቀለበስ መንገድን መቀየስ ነው።

 

የጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ እና ተባባሪ ሊቀ መንበሮች መግለጫዎች ያሉት የምልአተ ጉባኤ  ሲሆን አባል ሀገራት እና ታዛቢዎችም ይሳተፉበታል፡፡ ጉባኤው ስምንት መሪ ሃሳቦችን ያካተተ ሲሆን እያንዳንዳቸው በሁለት-ግዛት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

እስራኤል እ.አ.አ ከመጋቢት 02 ቀን 2025 ጀምሮ የጋዛ መሸጋገሪያዎችን በመዝጋቷ  ምግብ፣ ሕክምና እና ሰብአዊ እርዳታዎች ተቋርጠው ቆይተዋል፡፡ ከ11 ሳምንታት በኋላ እገዳውን ያነሳች ቢሆንም አሁንም ለተጎጂዎቹ እርዳታው በአግባቡ እየደረሰ እንዳልሆነ ነው እየተነገረ የሚገኘው፡፡ ይህም በግዛቱ ውስጥ ቀድሞውንም የነበረውን የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ እያባባሰ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡ በዚህ ድርጊቷም ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ እና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ወቀሳ እየቀረበባት ነው፡፡

 

ከሰሞኑም የጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ የእስራኤል ሚኒስትሮች ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ ለማስወጣት ያቀረቡትን ሃሳብ ተቃውመዋል፡፡ “ይህ ፈጽሞ ተቀባይነት ያለው አማራጭ አይደለም። ፈጽሞ ሊሆንም አይችልም” ነው ያሉት። ለጣሊያን ፓርላማ ንግግር ያደረጉት አንቶኒዮ ታጃኒ እ.አ.አ በጥቅምት 07 ቀን 2023 እስራኤል ለሃማስ ጥቃት የሰጠችው ምላሽ “ፍፁም አሳዛኝ እና ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ነው በአፅንዖት የተናገሩት።

የቦምብ ጥቃቱ ቆሞ ሰብዓዊ ዕርዳታ ወዲያውኑ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው የግብፅን የጋዛን መልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ዕቅድም እንደሚደግፉ ነው የገለጹት፡፡ ታጃኒ “ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ ማስወጣት  ተቀባይነት ያለው አማራጭ አይደለምና በጭራሽ አይሆንም” ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል፡፡

በተያያዘም “እስራኤል ጋዛ ላይ የምታደርገው ጥቃት ሃማስን ለመውጋት ከሚያስፈልገው በላይ ነው” ሲሉ አንድ  የአውሮፓ ሕብረት ከፍተኛ ዲፕሎማት መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ካጃ ካላስ  የሚባሉ ከፍተኛ የአውሮፓ ሕብረት ዲፕሎማት እንዳሉት  የአውሮፓ ሕብረት በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈውን አዲሱን የእርዳታ ማከፋፈያ ሞዴልን እንደማይደግፍ ተናግረዋል። “የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭትን ወደ ግል ማዞርን አንደግፍም። ሰብዓዊ እርዳታን እንደ መሳሪያ መጠቀም አይቻልም” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

 

የአውሮፓ ሕብረት ለጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ከሚያደርጉት ትልልቅ ለጋሾች መካከል አንዱ ነው፡፡ “ለጋዛ አብዛኛው እርዳታ የሚሰጠው በአውሮፓ ሕብረት ቢሆንም በእስራኤል ስለታገደ ለሕዝቡ እየደረሰ አይደለም” ብለዋል ካላስ። እስራኤል መጋቢት ላይ ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ መከልከሏ ይታወቃል፡፡ ታዲያ እገዳ ከጣለች ከ11 ሳምንታት በኋላ  እገዳውን አንስታለች፡፡ ሆኖም የአውሮፓ ሕብረት ከእስራኤል ጋር ያለውን የንግድ ስምምነት በተመለከተ መደበኛ ግምገማ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ካላስ በመጪው ወር (እ.አ.አ ሰኔ 23 ቀን 2025) በብራሰልስ በሚካሄደው የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ አማራጮችን እንደሚያቀርቡ ነው የተናገሩት።

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን በበኩላቸው በቅርቡ እስራኤል በጋዛ ሲቪል መሰረተ ልማት ላይ ያደረሰቻቸውን ጥቃቶች “ያልተመጣጠነ” ሲሉ ገልጸውታል። እንዲሁም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወታደራዊ ጥቃት እንድታቆም ጠይቀዋል፡፡ በተለይ እንግሊዝ ከእስራኤል ጋር የነበራትን የንግድ ስምምነቶችን እያቋረጠች እንደሆነም ተናግራለች።

 

በተያያዘም በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕግ ባለሙያዎች እንግሊዝ ከእስራኤል ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነቷን እንድትገመግም ጠይቀዋል፡፡ እንዲሁም  በእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ እና የጉዞ እገዳ መጣልን ጨምሮ የእንግሊዝ መንግሥት በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያለውን መንገድ ሁሉ እንዲጠቀም አሳስበዋል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው መቀመጫቸውን በእንግሊዝ  ያደረጉ 828 የሕግ ባለሙያዎች እና የቀድሞ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ናቸው ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ደብዳቤ ፈርመው ያስገቡት፡፡

 

ይህ በእንዲህ እያለ ከሰሞኑ  በጋዛ የሚገኙ የእስራኤል ታጋች ቤተሰቦች ሁሉም ታጋቾች እንዲመለሱ ለመጠየቅ በቴል አቪቭ የሚገኘውን አውራ ጎዳና ዘግተው ውለዋል። ሁሉም ታጋቾች እንዲፈቱ ዋስትና የሚሰጥ እና በጋዛ ያለውን ጦርነቱን የሚያስቆም  አጠቃላይ ስምምነት እንዲደረግ መጠየቃቸውን አናዶሉ ዘግቧል፡፡

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እስካሁን 58 ታጋቾች እንደሚገኙ ትገምታለች፤ 20ዎቹ በሕይወት ይኖራሉ ተብሎ ይታመናል። በተመሳሳይ ከ10 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ደግሞ በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ የፍልስጤም መንግሥት ተናግሯል፡፡

በሌላ በኩል የየመን ታጣቂ ቡድን ሃውቲ ተደጋጋሚ የሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል ላይ ካደረሰ በኋላ እስራኤል በሃውቲ ቁጥጥር ስር የሚገኘውን የሳናአ አየር ማረፊያን ደብድባለች። በዚህም የሃውቲ  የመጨረሻ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ወድሟል፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ኢራን ከየመን ለሚሰነዘረው ጥቃት ተጠያቂ ናት” ማለታቸውን  አናዶሉ ዘግቧል፡፡

 

በዌስት ባንክ የእስራኤል ሰፋሪዎች   ፍልስጤማዊያን ላይ ጥቃት መፈጸማቸው የተዘገበውም ከሰሞኑ ነው፡፡ በደቡባዊ ናቡስ ውስጥ በአል-ሉባን አል ሻርቂያ ከመንደሩ አጠገብ ያለውን ዋና መንገድ ዘግተው የፍልስጤም መኪናዎችን በድንጋይ መደብደባቸውን እማኞች ለአናዶሉ ተናግረዋል።

የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ በእስራኤል ወታደራዊ ጥበቃ ስር ያሉ በርካታ የእስራኤል ሰፋሪዎች የመንደሩን ዳርቻ በመውረር ዋናውን የራማላ-ናብሉስ መንገድ መዝጋታቸውን ዘግቧል፡፡ በከራማላ ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ቢርዚት ደግሞ በፍልስጤማዊያን እና በእስራኤል ወታደሮች መካከል ግጭት ተቀስቅሷል፡፡ ይሁንና ምንም አይነት ጉዳት እና እስራት እንዳልተፈፀመ ነው የገለጸው።

 

እ.አ.አ በጥቅምት ወር 2023 ሃማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ በሚወስደው የመልሶ ጥቃት ከ54 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን  ተገድለዋል። አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውን በሃማስ የሚመራው የፍልስጤም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

 

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here