ዓለም በ2017 ዓ.ም

0
57

በ2017 ዓ.ም ዓለማችን የተለያዩ ክስተቶችን አስተናግዳበታለች:: ከጦርነት እና የአየር ንብረት መዛባት ጋር የተያያዙ አያሌ ችግሮች እና አደጋዎች ተመዝግበዋል:: ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶችም ደርሰዋል::

ከዓመት ዓመት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየጨመሩባት የምትገኘው ኘላኔታችን ባለፈው ዓመትም በአሳሳቢ ሁኔታዎች ውስጥ ለማለፍ ተገድዳለች:: በ2017 ዓ.ም በርካታ የዓለማችን ሀገራት ከእርስ በርስ እስከ ዓለማቀፋዊ ይዘት ባላቸው ግጭቶች ውስጥ ነበሩ፣ አሁንም በዚሁ የግጭት አዙሪት ውስጥ ናቸው::

እነዚህ ጦርነቶችም ወደ ከፍተኛ ውድመት እና ሰብዓዊ ቀውሶች ያመሩ መሆናቸውን አርምድ ኮንፍሊክት ሎኬሽን ኤንድ ኢቨንት ዳታ ኘሮጀክት የተባለ ተቋም ይፋ ያደረገው የጥናት መረጃ ያሳያል::

መረጃው እንደጠቆመው ግማሹ የዓለማችን ክፍል በግጭቶች ውስጥ ነበር:: በዋናነት ደግሞ ዩክሬን፣ ፍልስጤም፣ ማይናማር፣ ሱዳን፣ ኢራን እና እስራኤል ከጦርነት ጋር የተያያዙ ከፍተኛ የሞት ቁጥር ተመዝግቦባቸዋል:: በተጨማሪም ዲሞክራቲክ ሪፐበሊክ ኮንጎ፣ ሶማሊያ፣ ናይጄሪያ፣ የመን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሕንድ እና ፓኪስታን የችግሩ ሰለባዎች ነበሩ ሲል መረጃው አክሏል::

በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ባለፉት ዓመታት የተጀመሩ ግጭቶች ተጠናክረው የቀጠሉበት እና የሠላም ተስፋው የቅዥት ያህል የተቆጠረበት ነበር::

ምንም እንኳ ዓመቱ የአሜሪካው አዲሱ ኘሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዓለም ሠላም እየሰበኩ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት (ዋይት ሀውስ) የገቡበት እና ለሚሊየኖች ሞት፣ መቁሰልና መፈናቀል ምክንያት የሆነው የሶሪያ ግጭት በአል አሳድ መወገድ የሠላም ተስፋ የተሰነቀበት ቢሆንም ሌሎቹ ጦርነቶች ግን የተባባሱበት ዓመት ነበር::

በዓለማችን ከስድስት ሰዎች አንዱ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ለትጥቅ ግጭት ተጋላጭ ስለመሆኑ የመረጃ ምንጩ ጠቁሟል፤ ይህም አስደንጋጭ ክስተት ዓለም ማብቂያ በሌላቸው ጦርነቶች ውስጥ መሆኗን ነው ያመላከተው::

እንደ መረጃው ከሆነ ከ50 በላይ የዓለማችን ሀገራት በተለያዩ አይነት ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ ናቸው፤ ከዚህ ውስጥ 22ቱ በአፍሪካ መሆናቸውን  መረጃው ይጠቁማል:: መረጃው አክሎም ከእነዚህ 50 የግጭት ቀጣናዎች 10ሩ እጅግ የከፋ እና ወደ ሌሎች ሀገራት የመስፋፋት አዝማሚያ ነበራቸው ሲል ያትታል::

እንደ ማይናማር እና ሱዳን ያሉ ሀገራት የውስጣዊ መከፋፋል እና የስልጣን ትግል መልክ ያላቸው የእርስ በእርስ ጦርነቶች ውስጥ ይገኛሉ:: የእርስ በርስ ግጭት ካለባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያም ተጠቅሳለች::

እንደ ናይጄሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ያሉ ሀገራት ደግሞ መንግሥታት እና ማሕበረሰቦች እንዳይረጋጉ የማድረግ ዓለማ ካላቸው አሸባሪ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋርጦባቸው ታይተዋል::

በተመሳሳይ የሩሲያ – ዩክሬን እና የእስራኤል ፍለሰጥኤም ጦርነት ድንበር ዘለል ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሲሆን ዳፋው ለሌሎች ሀገራት ተርፎ የታየበት ዓመት ነበር::

ሌላው በተጠናቀቀው 2017 ዓመት ከተስተናገዱ ዓበይት ክስተቶች መካከል የአደንዛዢ እፅ ጦርነት ይጠቀሳል፤ ለዚህ ደግሞ ሚክሲኮ በአብነት ተጠቃሽ ናት፤ ከእፅ አዘዋዋሪ ቡኖች ጋር በተደረገ ጦርነት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠር ሕይወት እንደሚቀጠፍም ተመላክቷል::

በአጠቃላይ በ2017 ዓ.ም በተካሄዱት ጦርነቶች  እጅግ ብዙ ሰዎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ ሚሊዮኖችን በሀገር ውስጥ እና ወደ ውጭ ሀገራት በመሰደድ በመጠለያ እንዲቆዩ የተገደዱበት እንደነበር ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል፤ የአያሌ ሰዎች ሕይወትም ተቀጥፏል ብሏል:: ለዚህ በማሳያነት የተነሳው ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ ቀይ ባሕርን ለማቋረጥ በሚደረግ ሙከራ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞችን ነው የጠቀሰው፤ የድርጅቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም ድረስ በመላው ዓለም 11 ሚሊዮን ሰዎች ተሰደዋል:: በግጭቶቹ መራዘም የተነሳም የመሠረተ ልማት ተቋማት እንደወደሙ በማንሳት ይህም ለመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት እንቅፋት ሆኗል ሲል ነው የገለጸው::

በ2017 ዓ.ም ለዓለማችን ሌላው ስጋት የነበረው የዓለም አየር ንብረት መዛባት መሆኑ በብዙ መልኩ ተስተውሏል:: የአየር ንብረት ለውጥ በመላው ዓለም ላሉ ሕዝቦች የዕለት ተዕለት ስጋት መሆኑ ታይቷል:: ለአብነትም በዚሁ በተጠናቀቀው ዓመት የዓለም ሙቀት በአንድ ነጥብ 75 ዲግሪ ሴልሺየስ (1.750c) ጭማሪ ማሳየቱን ዎርልድ ክላይሜት ቼንጅ የተሰኘው የመረጃ ምንጭ አመላክቷል:: ይህም የአየር ንብረት መዛባትን ለመቆጣጠር በፖሊሲ ስምምነቱ ላይ ከአንድ ነጥብ አምስት ሴልሺየስ (1.50c) እንዳይበልጥ የተባለውን ያለፈ ሆኖ ተመዝግቧል::

የአር ንብረት ለውጥ እየተባባሰ በመሄዱ በአውዳሚ የሰደድ እሳት፣ የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት እና የበረዶ መቅለጥ አደጋዎች በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት አድርሰዋል:: በዓመቱ አጋማሽ ላይ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ ከተማ ላይ የደረሰው እጅግ ከባድ ሰደድ እሳትም ከተማዋን ለታላቅ ውድመት ዳርጓል:: ከ180 ሺህ በላይ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ያደረገ እና ለ10 ሰዎች ሞትም ምክንያት ሆኗል:: በተጨማሪም ካናዳ እና አውሮፓም ለአደገኛ ሰደድ እሳት አደጋዎች የተጋለጡበት እና ሚሊየኖች የተፈናቀሉበት ክስተት ተመዝግቧል::

በዓለም ሙቀት መጨመር የተነሳ የውኃ መጠን መጨመር እና የመሬት መዋጥ ጥምር ፈተናዎች በባሕር ዳርቻ ያሉ አካባቢዎችን ለጥቃት ዳርጓል፤ የናሳ የ2017 ዓ.ም ጥናት እንደሚያሳየው እንደ ሳንፍራንሲስኮ እና ሎስ አንጀለስ ያሉ ከተሞች በመስጠም ላይ ናቸው:: ይህም በተጠናቀቀው 2017 ዓ.ም አንዱ ክስተት ነበር::

በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከ707 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከቀየው መፈናቀሉን መረጃዎች ያሳያሉ፤ ለእነዚህ ችግሮች ዋና ገፊ ምክንያቶች እስካሁን ለውጥ ያላሳየው የተፈጥሮ ነዳጅ ጥቅም ላይ መሆን፤ የደኖች መመንጠር፣ የኢንዱስትሪዎች የጭስ ልቀት መጠን መጨመር ተጠቃሽ ናቸው::

የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመፍታት በዓመቱ በተናጠል ከሠሩ አርአያ ሀገራት መካከል ዴንማርክ፣ ኢስቶኒያ እና ኖርዌይ የዓመቱ ግንባር ቀደም ተብለዋል:: ዴንማርክ በተለዋጭ ኃይል ሽግግር፣ በጠንካራ የአየር ንብረት ፖሊሲ እና በንፋስ ቴክኖሎጂ አመራር ተወድሳለች:: ኢስቶኒያ በኃይል አጠቃቀም እና በጋዝ ልቀት ቅነሳ ፖሊሲዋ የተነሳ የንጋቷ ኮከብ ተብላለች:: ኖርዌይ በኤሌክትሪክ ኃይል ተሽከርካሪ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ መስፈርትን በማሟላት አርዓያ መባሏን የ2017 ዓ.ም የክላይሜት ቼንጅ ፐርፎርማንስ ኢንዴክስ መረጃ ያስረዳል::

ኢትዮጵያ ደግሞ እጅግ የተጠናከረ የአረንጓዴ ልማት ተግባር ውስጥ መሆኗ ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል የበኩሏን በመወጣት ላይ ናት:: በዚህም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከማግኘት ባለፈ ሙገሳም ተችሯታል፤ በተመሳሳይ ሰሞኑን የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ለአካባቢ ስነ ምሕዳር ያለው ሚና ትልቅ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል::

 

(መሰረት ቸኮል )

በኲር የመስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here