“ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እስኪኖረዉ እሠራለሁ”

0
299

የባህል ሕክምና በአፋዊና አንዳንዴ በጽሑፍ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ባህላዊና መንፈሳዊ ይዘት ያለው ክዋኔ ነው:: እንደ ዘመናዊ ሕክምና ማንኛውም ሰው በመማርና በማጥናት ሕክምናውን መስጠት የሚያስችልበት መንገድ አልተመቻቸም:: ለበሽታው የሚዘጋጁ ቅመማዎች ምስጢራዊና ዕውቀቱም ለተመረጡ ሰዎች ብቻ የሚተላለፍ ነው::

በዚህ እና መሰል ምክንያቶች የተነሳ እስከአሁን ተገቢው ትኩረት ስላልተሰጠውና ጥናት ስላልተደረገበት የሚጠበቅበትን ያህል ማደግ አልቻለም:: “ይህንን ቅጠል ከዚህ ነገር ጋር ቀምመህ ለዚህ በሽታ ተጠቀም” የሚሉ አንዳንድ መጻህፍቶች ቢኖሩም:: ይህንን በደንብ ጥናት አድርገንበት መድኃኒቶችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በፋብሪካ ደረጃ ማምረት የሚቻልበት አቅም መፈጠር ግን እስካሁን አልተቻለም ይላሉ የደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ የባህል ህክምናውን በተመለከተ ያለንበት ሁኔታ የት ነው በሚል በ2009 ዓ.ም በተደረገ ውይይት ለሪፖርተር ጋዜጣ አስተያየት የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥንታውያት መዛግብት ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር መርሻ አለኸኝ::

ዶ/ር መርሻ በሀገሪቱ ዘመናዊ ሕክምና ከተጀመረ 100 ዓመት እንኳን እንዳልሞላው ገልፀው፤ ከዛ በፊት ግን ሰዎች ሲታመሙ የሚታከሙት በባህላዊ ሕክምና እንደነበር ነው ያስታወቁት:: የባሕል ህክምናን የሚያሳድጉ በርካታ መጻሕፍት በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር ተሰርቀው መውጣታቸውንና በሌላ ሀገሮች ምርምር እየተደረገባቸው እንደሚገኝም በቁጭት ይናገራሉ::

የዓለም ጤና ድርጅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች  ለባህላዊ ሕክምናዎች ዓይነቶች   ዕውቅና ከሰጠ ሰነባብቷል:: በባህላዊ ሕክምና ቀዳሚ የሆነችው ቻይና እ.ኤ.አ. በ2012 በባህላዊ ሕክምና ብቻ 83 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማግኘት ችላለች:: ቻይና በአንድ ዓመት ብቻ ይህንን ያህል ከፍተኛ ገቢ ያገኘችበትን ይህንኑ የባሕል ህክምና ጥበብ ትኩረት ሰጥቶ እና አዘምኖ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ደጋፊ እንዲሆን የማድረጉ ተግባር ገና ያልተሰራበት ቢሆንም በግለሰቦች ደረጃ ግን ጥረት የሚያደርጉ በርካታ የባሕል ሀኪሞች አሉ:: ሀኪም ሙሉ አልማው ደግሞ ከነዚህ አንዷ ነች::

በሀገራችን የነበረውን እና ያለውንም ጥበብ  በዘመናዊ መንገድ አሳድገን ከተጠቀምን ትልቅ እውቀት እና ትርፍ ያመጣል ብላ እንደምታምን የገለፀችልን ሀኪም ሙሉ አልማው “ሙሉ ሄሞሮይድ” በሚል የንግድ ስም ትታወቃለች:: ላለፉት አራት ዓመታት ከዛ በፊት ደግሞ በፍኖተ ሰላም ከተማ ለአንድ ዓመት በዚሁ ሕክምና ዘርፍ እውቅና እና ፍቃድ አግኝታ ስትሰራ ቆይታለች::

ከሌሎች የባህል ሀኪሞች የምትለየው በአንድ ዘርፍ ወይም በኪንታሮች ሕክምና  ብቻ መድኃኒትን በመሰማራቷ ነው::

የባህል ህክምና በብዛት ከቤተሰብ የሚወረስ ልምድ ቢሆንም የሙሉ ወደ ዘርፉ የመግባት አጋጣሚ ግን ከቤተሰብ ያልተወረሰ እውቀት እንደሆነ ታነሳለች::

ተወልዳ ባደገችበት ምዕራብ ጎጃም  ጅጋ አካባቢ በልጅነቷ እጇ ላይ የሚወጣ ኪንታሮት በጣም ያስቸግራት እንደነበር አንስታ ብዙ ጊዜ ብትታከምም ሙሉ ለሙሉ ኪንታሮቱ ሊጠፋ እንዳልቻለ ታስታውሳለች::

የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ግን አንድ ቀን በጨዋታ ላይ እያለች ስትወድቅ ኪንታሮቷ ያለበት እጇ በመመታቱ የፈሠሠውን ደም ለማስቆም ከአካባቢው  ያገኘችውን  አንድ ዕፅ ቅጠል          ቆርጣ በሚደማው እጇ አካባቢ ያዘችበት:: “ደሙ መፍሰስ ሲያቆም ወደ ጨዋታዬ ተመለስኩ” የምትለው ሙሉ ይህ በሆነ በሦስተኛው ቀን እጇን ስትታጠብ የኪንታሮቱ ግማሽ ክፍል መነሳቱን አስተዋለች:: ያኔ እናቷ  የተጠቀመችውን ቅጠል እንድታሳያቸው አድርገው በቀረው የኪንታሮቱ ክፍል ቅጠሉን ቀጥቅጠው አሰሩበት::ውለው ሲያድሩም የዕፅ በእርግጥም የኪንታሮት ማጥፊያ መድኃኒት መሆኑን አረጋገጡ::

ኪንታሮት ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ እሷና ቤተሰቧ መደሰታቸውን ካስተዋሉ ማህበርተኞቻቸው መካከልም የአንዳቸው ልጅ  ዓይን ላይ ኪንታሮት ወጥቶ ያስቸግራት ነበር እና እንድትረዳቸው ሙሉ እና እናቷ ተጠየቁ፤ ያኔ ሙሉ ቅጠሉን በመቁረጥ እናቷ ደግሞ  ቅጠሉን ቀጥቅጠው በሚቀባ መልክ በማዘጋጀት እንደሰጧት እና የልጅቱ ኪንታሮት ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ የቅጠሉን ውጤታማነት መተማመን እንደቻሉ ትገልፃለች::

መድኃኒቱ ከቆዳ ኪንታሮት በተጨማሪ በፊንጢጣ አካባቢ ላለው ሄሞሮይድም ቢደረግ መድህን እንደሆነ የተገነዘበችው ግን የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነበር፤ ሀኪም ሙሉ አንደምትገልፀው አንድ በሹፍርና ሥራ የተሰማራ ዘመዳቸው በበሽታው በጣም እየተሰቃየ መሆኑን ሲሰሙ ቅጠሉን አድርቃ በማዘጋጀት በጥብጦ በሽታው ባለበት አካባቢ ለ13 ቀናት እንዲቀባው አደረገች::

የመድኃኒቱን ውጤታማነት ያረጋገጠችው ሀኪም ሙሉ ትኩረቷን ትምህርት ላይ በማድረግ 10 ኛ ክፍል ስታጠናቅቅ ወደ ኮሌጅ በመግባት ባዮሎጂ አጠናች::

የባዮሎጂ ትምህርት የላብራቶር (የተግባር ልምምድ) ጊዜ ደግሞ በአካባቢ ያለን ሀብት እንዴት በአግባቡ መገንዘብ እና መጠቀም እንደሚገባ ብዙ እድል ስለሚፈጥር በባህል መድኃኒት ህክምና እንድትሰማራ ገፋፍቷታል::

ከዚሁ ገፊ ምክንያት በተጨማሪ የትዳር አጋሯም የምትወደውን የኪንታሮት ህክምና ወደ ስራ ቀይራ እንዲተዳደሩበት እና ለህክምና ፈውስ እንድታገኝ ስለገፋፋት ከጤና ቢሮ ፍቃድ በማውጣት በፍኖተሰላም ከተማ የባህላዊ ህክምና ሥራዋን ጀመረች::

የመድኃኒቱን ፍትሃዊነት ደግሞ ከተጠቃሚዎች በሚገኝ ግብረመልስ በመታገዝ እየሰጠች ተጠቃሚውም ውጤታማነቱን ሲመሰክርላት ሰፊ ተጠቃሚ ወዳለበት  ባሕር ዳር ከተማ በመምጣት ሽንብጥ ቀበሌ አካባቢ መሥራት ቀጠለች::

“የመድኃኒቱን ውጤታማነት መጀመሪያ የሞከርኩት በራሴ ስለነበር ለሌላው ስሰጥ አልተሳቀቅኩም::” የምትለው ሀኪም ሙሉ የሄሞሮይድ በሽታ ያለውን ደረጃ፣ ህመሙን፣ ጉዳቱን የተደረጉ ጥናቶችን በመመልከት፣ የተጠቃሚን ግብረ መልስ በጽሁፍ በማስፈር እና ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ባገኘችው ድጋፍ በሙሉ ልብ ወደ ሥራው እንደገባች ትናገራለች::

የአምሮአዊ ንብረት ማረጋገጫ ሲሰጣት ጎንደር ዩንቨርሲቲ ደግሞ ሞዴል ፋርማሲ ለመገንባት የንግድ ምልክት መሥራትን እንዳሰለጠናት እና ስልጠናውም ውጤታማ እንደነበር ትገልፃለች::

የባህል ሐኪሞች ማህበር አባል የሆነችው ሁኪም ሙሉ በማህበሩ ከሌሎች ተሞክሮ በመቅሰም በኩል ከደቡብ አፍሪካ ከመጡ የባህል ሀኪሞች ጋር ተሞክሮ በመውሰድ ምርምር እያደረገች መድኃኒቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየሰራች እንደሆነም ነው የገለፀችው::

“የሄሞሮይድ በሽታ የውስጥ እና የውጭ ተብሎ በሁለት ይከፈላል” የምትለው ሙሉ የውስጥ ከሆነ መድኃኒቱን ከ15 እስከ 20 ቀን እየታጠቡ ማታ የሚቀቡት ነወ::

የውጭ ከሆነ ደግሞ አንድ ወር ድረስ በመቀባት እንደሚጠፋ ትገልፃለች::

የኪንታሮት በሽታ በተለያዩ የአካል ክፍሎች ላይ ሊከሰት የሚችል ቢሆንም በተለይ በፊንጢጣ ላይ የሚከሰተው ኪንታሮት ግን አራት ደረጃዎች አሉት ትላለች ሀኪም ሙሉ፤ የመጀመሪያው ደረጃ መድማት ፣ሁለተኛው ሽንትቤት ሲቀመጡ ከውስጥ ወደ ውጭ መውጣት እና ተመልሶ መግባት ፣ሦስተኛ ደረጃ እብጠቱ ይወጣ እና መጠኑም ይጨምራል፣ አራተኛው ደረጃ ላይ እብጠቱ ወደ ውጭ ይወጣና በህክምና እስካልተፈወሰ የማይመለስ እንደሆነ ትገልፃለች::

አቶ ሃብቴ ድረስ በሆሞሮይድ (ኪንታሮት) በሽታ ለ10 ዓመት እንደተሰቃዩ ይናጋራሉ:: “በሽታው በባህሪው የመጠዝጠዝ እና የማበጥ ስሜቱ እረፍት ስለሚነሳ ብዙ ያስቸግራል::” በማለት በታመሙ ጊዜ ተቸግረው እንደነበር ያስታውሳሉ:: ከስድስት ወር በፊት ግን ለኪንታሮት (ሄሞሮይድ)  የባሕል ህክምና የምትሰጥ አንዲት ሴት አለች  መባሉን ሰምተው ወደ ህክምና መስጫዋ ሲሄዱ ያገኙት መድሃኒት ዛሬ ላይ በጤንነት ህይወታቸውን እንዲመሩ ማስቻሉን ነው የነገሩን::

መድኃኒቱን ወደፊት በዘመናዊ መንገድ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እስኪኖረው ድረስ እስደምትሰራ የምትገልፀው ሀኪም ሙሉ  ጎንደር ዩንቨርሲቲ ስትሰለጥን አጭር ቪድዮ በመሥራት እና ዌብሳይት ላይ በመልቀቅ እንዳስተዋወቀው እና ያንን እያዩ የሚመጡ ሰዎች ቁጥርም እንደጨመረ ትናገራለች::

ወልዳ በተኛችበት አጋጣሚም ቢሆን መድኃኒት ፈላጊ ሰዎች ብዙ ስለነበሩ አራስነቷን ሳትጨርስ ወደ ሥራ እንደገባች የምትገልጸው ሙሉ ከ60 ዓመት በላይ ላሉ እና መንቀሳቀስ ለማይችሉ ደግሞ በቤት ለቤት ህክምና ፈውስ እንዲያገኙ ስታደርግ ትልቅ እርካታ እንደምታገኝ ገልፃልናለች::

ብዙ ሴቶች ያላቸውን እውቀት ወደ ሃብት መቀየር ስለማያስቡ እንጂ ብዙ እውቀት ውስጣቸው አለ የምትለው ሀኪም ሙሉ እሷም በራሷ ትንሽ አጋጣሚ ያገኘችው እውቀት ህይወቷን መምራት የሚያስችል ሥራን ስለፈጠረ እና ለሰዎችም የመዳን ምክንያት ስለሆነች ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here