ከሰሞኑ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “ፈረንሳይ እና አጋሮቿ የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ ማስቆም ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፍላጎት አልነበራቸውም” ማለታቸው ዓለምን ያነጋገረ አጀንዳ ሆኗል:: ማክሮን ፈረንሳይ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋትን ለማስቆም ባለመቻሏ ይቅርታ ጠይቀዋል::
የሩዋንዳውን የዘር ጭፍጨፋ 30ኛ ዓመት ለማክበር በተዘጋጀው የቪዲዮ መልዕክት ማክሮን “በቱትሲዎች ላይ ሙሉ በሙሉ የማጥፋት ሂደት ሲጀመር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማወቅ እና እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዘዴ ነበረው” ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም ሀገራቸው “ከምዕራባውያን እና ከአፍሪካ አጋሮቿ ጋር የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያስቆም የሚችል ፍላጎት አልነበራትም” ማለታቸውን አናዶሉ ዘግቧል::
እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት በመቶ ቀናት ዉስጥ ከ800 ሺህ በላይ አንዳንዶች አንደሚሉት ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሩዋንዳዊያን እንደ ቅጠል ረግፈዋል። በዚህ ጭፍጨፋ ሕፃናት ያለ አሳዳጊ፣ አዛውንቶች ያለ ጧሪ፣ ሕሙማን ያለ አሳካሚ ቀርተዋል። ሚሊዮኖች ደግሞ እግራቸዉ እንደመራቸዉ ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
ታዲያ ዓለም ለዘር ጭፍጨፋው ትኩረት የሰጠው ወደ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ገደማ ካለቀ በኋላ ነበር” ሲል ዶቸቨሌ ዘግቧል::
እ.አ.አ. በ1994 በሩዋንዳ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መላው ዓለም በዘግናኝነቱ ሲያስታውሰው ይኖራል::
ሂስትሪ ድረገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው በሁቱ ብሔርተኞች በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ የጀመረው የዘር ማጥፋት ወንጀል በመላው ሀገሪቱ በአስደንጋጭ ፍጥነት እና ጭካኔ ተስፋፋ። በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በቱትሲ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር በወታደራዊ ጥቃት ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ወቅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያን ሲሞቱ ሁለት ሚሊዮን ስደተኞች (በተለይ የሁቱ ብሔር ተወላጆች) ከሩዋንዳ ተሰደዋል።
እ.አ.አ. በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ትንሿ ሩዋንዳ የተትረፈረፈ የግብርና ምጣኔ ሀብት ያላት እና በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች። ከሕዝቧ 85 በመቶ ያህሉ ከሁቱ ብሔር የተገኙ ነበሩ። የተቀሩት ቱትሲዎች ሲሆኑ የሩዋንዳ የመጀመሪያ ነዋሪዎች ከሆኑት ከጥቂት የቲዋ ጎሳ አባላት ጋር በአንድነት ይኖሩ ነበር።
እ.አ.አ ከ1897 እስከ 1918 ጀርመን በቀኝ ግዛት ከተቆጣጠረችው የምሥራቅ አፍሪካ ክፍል መካከል ሩዋንዳ ከጎረቤት ብሩንዲ ጋር በሊግ ኦፍ ኔሽን /የዓለም ሀገራት ሕብረት/ ትዕዛዝ የቤልጂየም ባለአደራ ሀገር ሆነች። በወቅቱ ገዥዎቹ ቤልጂማዊያን ከሁቱ ይልቅ አናሳ የሆኑትን ቱትሲዎች ያግዙ ነበር፤ ጥቂቶች ብዙዎችን የመጨቆን ዝንባሌ እንዲኖራቸው ያባብሱ ነበር:: ይህም ሩዋንዳ ነፃነቷን ከማግኘቷ በፊትም ወደ ብጥብጥ እንድታመራ አድርጓታል::
እ.አ.አ. በ1959 የሁቱ አብዮት ወደ 330 ሺህ የሚደርሱ ቱትሲዎችን ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ አስገድዶ ነበር:: ይህ ደግሞ በቁጥር አናሳ አድርጓቸዋል።
እ.አ.አ. በ1961 መጀመሪያ ላይ አሸናፊው ሁቱ የሩዋንዳውን ቱትሲ ንጉሥ በግዞት አስገድዶ የሀገሪቱን ሪፐብሊክነት አወጀ። በዚያው ዓመት ከተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ሕዝበ ውሳኔ በኋላ ቤልጂየም እ.አ.አ. በሐምሌ ወር 1962 ለሩዋንዳ በይፋ ነፃነቷን ሰጠች።
ምንም እንኳን ሩዋንዳዊያን ነጻነታቸውን ቢያገኙም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ከነጻነት በኋላ በነበሩት ዓመታት ቀጥለዋል። እ.አ.አ. በ1973 አንድ የወታደራዊ ቡድን ሜጀር ጄኔራል ጁቨናል ሀቢያሪማናን ለዘብተኛ ሁቱ አድርጎ ሾመ። ለሚቀጥሉት ሁለት ዐሥርት ዓመታትም የሩዋንዳ መንግሥት ብቸኛ መሪ ሆኑ::
በመቀጠልም ሀቢያሪማና ብሔራዊ አብዮታዊ የልማት ንቅናቄ (ኤን አር ኤም ዲ) የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መሠረቱ። እ.አ.አ. በ1978 በፀደቀው አዲስ ሕገ መንግሥትም ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል:: እንዲሁም በድጋሚ በ1983 እና በ1988 ብቸኛ ዕጩ ሆነው በመቅረብ የፕሬዝዳንትነቱን በትረ ሥልጣን ተቆጣጥረዋል።
እ.አ.አ. በ1990 የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) በዋናነት የቱትሲ ስደተኞችን ያቀፈው ከኡጋንዳ በመምጣት ሩዋንዳን ወረረ። ሀቢያሪማናም የቱትሲ ብሔር ተወላጆችን “የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) ተባባሪዎች ናቸው” በማለት በመቶዎች የሚቆጠሩትን ወሕኒ አወረዷቸው።
እ.አ.አ. ከ1990 እስከ 1993 ባለው ጊዜ ውስጥም የመንግሥት ባለስልጣናት በቱትሲዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ በመምራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገደሉ። በኋላም እ.አ.አ. በ1992 የተኩስ ማቆም ስምምነት በማድረግ በመንግሥት እና በሩዋንዳ አርበኞች ግንባር መካከል ድርድር ተካሂዷል::
በመቀጠልም እ.አ.አ. በነሐሴ ወር 1993 ሀቢያሪማና የሩዋንዳ አርበኞች ግንባርን የሚያካትት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም የሚጠይቅ ስምምነት በአሩሻ ታንዛኒያ ተፈራረመ። ይህም የአሩሻ የሰላም ስምምነት በመባል ይጠራል::
ይሁንና ይህ የስልጣን ክፍፍል ስምምነት የሁቱ ጽንፈኞችን አስቆጥቷል፤ ይህንን ቁጣቸውን ለማክሸፍም በሁቱዎች ላይ ቱትሲዎች ፈጣን እና ዘግናኝ እርምጃ ወስደዋል።
እ.አ.አ. ሚያዚያ 6 ቀን 1994 ሀቢያሪማናን እና የቡሩንዲውን ፕሬዝዳንት ሳይፕሪያን ንታያሚራን የጫነ አውሮፕላን በዋና ከተማዋ ኪጋሊ ላይ በሚሳኤል ተመታ፤ አውሮፕላኗም ጋየች:: ዘጠኝ መንገደኞችና ሦስት የአውሮፕላኑ ሠራተኞችም አብረው ነደዱ።
በወቅቱ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት ወንጀለኞች እነማን እንደሆኑ በእርግጠኝነት አልታወቀም። ይሁንና አንዳንዶቹ የሁቱ አክራሪዎችን ሲወቅሱ ሌሎች ደግሞ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር መሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ከአውሮፕላኑ አደጋ በኋላ በአንድ ሰዓት ውስጥ የፕሬዚዳንት ሀቢያሪማና ጥበቃ ሠራዊት አባላት ከሩዋንዳ የጦር ኃይሎች (FAR) እና የሁቱ ሚሊሻ ቡድኖች እንዲሁም ተመሳሳይ ግብ ካላቸው ጋር በመሆን “ኢንተርሃምዌይ” (የጅምላ ጭፍጨፋ) በማወጅ መንገድ በመዝጋትና በማገድ ቱትሲዎችንና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ያለ ምንም ምክንያት ማረድ ጀመሩ።
የዘር ጭፍጨፋው የመጀመሪያ ሰለባ ከሆኑት መካከል ለዘብተኛዉ የሁቱዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አጋቴ ኡዊሊንግዪማና እና ዐሥር የቤልጂየም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ይገኙበታል። ይህ ሁከት የፖለቲካ ክፍተት ፈጠረ፤ የቤልጂየም ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መገደላቸው ቀሪዎቹን የቤልጂየም ወታደሮች ሩዋንዳን ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።
በኪጋሊ የተጀመረው የጅምላ ግድያ በፍጥነት በመላው ሩዋንዳ ተዛመተ። በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ አብዛኞቹ ቱትሲዎች በሚኖሩበት በማዕከላዊ እና በደቡብ ሩዋንዳ የሚገኙ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ተቃውመዋል። እ.አ.አ. ከሚያዚያ 18 ቀን 1994 በኋላ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተቃዋሚዎቹን አስወግደው ብዙዎቹን ገደሏቸው። ከዚያ በኋላ ግን ሌሎች ተቃዋሚዎች ዝም አሉ ወይም ግድያውን በንቃት መርተዋል። ባለሥልጣናቱ ለገዳዮች ምግብ፣ መጠጥ፣ መድኃኒት እና ገንዘብ ሸልመዋል። በመንግሥት የሚደገፉ የራድዮ ጣቢያዎች ሁቱዎች ጎረቤቶቻቸው የሆኑ ቱሲዎችን እንዲገድሉ ጥሪ ማድረግ ጀመሩ። የሁቱ ሚዲያዎች ቀደም ሲል ቱትሲዎች ሀገሪቱ ውስጥ ስልጣን በነበራቸው ጊዜ በሁቱ ብሔር ላይ በደል ፈጽመዋል በማለት ቅስቀሳ አድርገዋል:: በሦስት ወር ውስጥም 800 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ተጨፈጨፉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ጦርነቱን ቀጠለ፣ ዘር ማጥፋትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ። እ.አ.አ. በሐምሌ ወር መጀመሪያ 1994 ላይ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ኃይሎች ኪጋሊን ጨምሮ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል መቆጣጠር ችለዋል።
በምላሹም ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሁሉም ሁቱዎች ከሩዋንዳ ሸሽተው በኮንጎ (በወቅቱ አጠራር ዛየር) እና በሌሎች አጎራባች ሀገሮች ወደሚገኙ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተሰደዋል።
ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል በኋላ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ብዙ ታዋቂ ሰዎች የውጭው ዓለም አጠቃላይ ሁኔታውን ስለዘነጋው እና ጭካኔው እንዳይከሰት ለማድረግ እርምጃ ባለመውሰዱ ቅሬታቸውን በምሬት ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞ ዋና ጸሐፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ለፒቢኤስ የዜና ፕሮግራም ፍሮንትላይን እንደተናገሩት የሩዋንዳ ውድቀት ከዩጎዝላቪያ ውድቀት በዐሥር እጥፍ ይበልጣል።
ከዘር ማጥፋት ዘመቻ በኋላ ሩዋንዳ ለዓመታት እርቅ ስታካሂድና ከሕመሟ ለማገገም ስትሞክር ቆይታለች:: አሁን ላይ “ውሾን ያነሳ ውሾ ነው” እንዲሉ ስለብሔር እና ስለ አለፈው የዘር ጭፍጨፋ የሚያነሳ የለም። ካነሳም ዘብጥያ ይወርዳል፤ ሀገሪቱ ስለ ብሔርኝነት ማውራትን በሕግ ከልክላለች:: ሀገሪቱ ትኩረት ያደረገችው ሀገራዊ አንድነትን በማስፈንና የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብትን በመገንባት ላይ ነው። በሕይወት የተረፉት ሰዎች በሩዋንዳ ዕድገት ከፍተኛ ጥንካሬ በማሳየትና ሕይወታቸውን በማደስ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በተጨማሪም በሕይወት የተረፉትን የሚደግፉ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች የተቋቋሙ ከመሆኑም በላይ በመላ ሀገሪቱ የመታሰቢያ ቦታዎችን በማዘጋጅት የተሰውቱን በየዓመቱ ይዘክራሉ::
ይህ በእንዲህ እያለ አሁንም በመላው ዓለም የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ምልክቶች እየተካሄዱ ይገኛል:: ድርጊቱን ለማስቆም ግን ዓለም አሁንም ዝምታን እንደመረጠ ነው:: በሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎች በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተካሄዱ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት ያሳያል፤ ሆኖም በአጥፊዎች ላይ እርምጃ ሲወሰድ አይሰተዋልም:: ነገሩ “በእንቁላሉ በቀጣሽኝ” እንዳይሆን ካሁኑ እርምጃ መውስዱ ተገቢ ነው::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም