የ36 ዓመቱ ቻይናዊ በመረጠው ታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማር የሚያስችለውን ውጤት ለማስመዝገብ ላለፉት አስራ ስድስት ዓመታት በተከታታይ ፈተና መውሰዱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አብቅቶታል::
ታንግ ሻንግጁን ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያበቃውን ፈተና የወሰደው በ2009 እ.አ.አ ነበር:: ያስመዘገበው ውጤትም ከ750ው 372 ነጥብ ነበር:: ውጤቱ ታንግ ላለመው ሲንግዋ ዩኒቨርሲቲ መግባት አያስችለውም ነበርና በቀጣዩ ዓመት ለመፈተን ወሰነ:: በቃ በተከታታይ ዓመታትም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የሚያስችለውን ነጥብ ለማምጣት መፈተኑን ቀጠለ::
በ2016 እ.አ.አ የተሻለ ነጥብ ማለትም 625 አስመዘገበ:: ይህ ነጥብ ታንግ ሻንግጁን በሚኖርበት ጓንታይ ክፍለ ሀገር በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ያስገባው ነበር፤ ሲንግዋ ዩኒቭርሲቲ ገብቶ ያለመውን በፊዚክስ እና ኬሚስትሪ እውቀት ለመካን ግን በቂ አልነበረም::
ታንግ ሻንግጁን ተስፋ ባለመቁረጥ በ2019 እ.አ.አ ከ750ው 649 ነጥብ አገኘ:: ነጥቡ በቻይና የተመረጡ በተባሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስገባው ነበር – ከሲንግዋ ዩኒቨርሲቲ በቀር::
በቀጣዩቹ ዓመታት በወሰዳቸው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ያገኘው ውጤት የተሻለ ነጥብ ካመጣበት 2016 እ.አ.አ ያነሰ ሆኖል:: ለዚህ ደግሞ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች ታንግ እድሜው እየጨመረ መሄዱን በምክንያትነት መጥቀሳቸውን ድረ ገጹ አስፍሯል::
ባለፈው የአውሮፖውያኑ ዓመት በማእከላዊ ቻይና በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ገብቶ ለመማር የመግቢያ ፈተና ተፈትኖ ነበር:: በጉንታይ ራስ ገዝ አስተዳደር ፈተናውን ከወሰዱ 460,000 ተፈታኞች ያገኘው ነጥብ ስድስት ሺኛ ደረጃ ነበር ያሰጠው:: ያ ነጥብም ለጓንታይ ሀገር ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባው አልሆነም፤ ታንግ ሻንግጁን ለቻይና ዴይሊ ለተሰኘው መገናኛ ባደረገው ቃለ ምልልስ ባለፈው ዓመት ለመጨረሻ ለ16ኛ ጊዜ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና እንደሚወስድ ተናግሮ ነበር:: ያመጣው ነጥብ ግን 600 ሆኗል፤ በቃ እድሜው 36 ደርሷል- ያለመውንም አላገኘም::
ታንግ ሻንግጁን እድሜው 36 በመድረሱ ህልሙ ተሳክቶ ነጥብ አምጥቶ ባሻው ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ቢመረቅም እድሜያቸው በ20ዎቹ ከሆኑ ምሩቃን ጋር ተወዳድሮ ስራ የማግኘት እድሉ ዝቅተኛ መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል::
በመጨረሻም በቻይና የ21ኛው ክፈለ ዘመን የትምህርት ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ስለታንግ ሻንግጁን “ጥሩ ህይወት ለመኖር ከተመረጠ ዩኒቨርሲቲ መግባት ስኬት ነው አዎ ጥሩ ህይወት ለመምራት ይረዳል፤ ነገር ግን ህይወት ስኬታማ ለመሆን ብዙ መንገዶች አሏት” ሲሉ ነው ያደማደሙት::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም