እውነት ነው፤ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዳለው ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ድቅድቅ ጨለማ ያልፍና ብርሃን ይፈነጥቃል፤ ክረምት በበጋ ይተካል፤ ማግኘት ማጣትን ያስረሳል፤ “የጎመን ምንቸት ውጣ፣ የገንፎ ምንቸት ግባ!’’ እንዲል ወቅት ይፈራረቃል፤ ጊዜም ይለወጣል፡፡
ሌላው ቀርቶ የነገ ትንሳኤያችንን እያሰብን ዛሬ ላይ ተስፋ የጣልንበትና ተስፋችን እውን እንዲሆን እየተረባረብንበት የሚገኘው ዓባይ እንኳ ትናንት ሌላ ነበር፡፡
የትናንቱ ዓባይ ለሀገሩ ስጋትና ውጋት፣ ለጐረቤት ህይወትና መብራት ነበር፡፡ ከራሱ ምንጭ እና ከገባሮቹ ከሚያገኘው ውኃ ላይ የክረምት ዝናብ በተጨመረበት ቁጥር ደግሞ የሀገሩን ለም አፈር እያሟጠጠ ለጐረቤት የሚቸር፣ ወገኑን አስርቦና አራቆቱ ባዕዳኑን የሚያሳድግ ፍርደ ገምድል ሀብት ነበር፡፡
ለ’ኛ የችጋር መንስኤ፣ ለሌላው የብልፅግና ምንጭ በሆነበት በዚህ ግብሩ ምክንያትም፡-
“የዓባይ ውኃ ሞልቶ እስከዳር ደረሰ፣
እርባና ቢስ ሆነ ለኛም አልደረሰ፡፡
ትንሹን ትልቁን ሁሉንም ሰብስቦ፣
ሄደ ገሠገሠ ሀገሩን አስርቦ፡፡
ዓባይ ከመፍለቂያው ሠከላ ብሄድ፣
ብዙ ሰው አገኘሁ በራብ ሲታጨድ፡፡
ዓባይን መከረው ጣና ንኳ አፍ አውጥቶ
ሲጋልብ ስላየው ጓዳውን አራቁቶ፡፡
ዓባይ ለወገኑ እንዴት ይጨክናል?
የራሱን ፊት ነስቶ ለሌላው ያበላል!
ሲባልበት ኖሯል፡፡ በዚህ ዘመናትን ባስቆጠረ ተመሳሳይ ግብሩ ሲያራቁት የኖረው የኢትዮጵያን አፈር ብቻ ሳይሆን ሰዉን፣ እንስሳቱን፣ ግንዱን ሳር ቅጠሉን፣ ማእድኑም ሳይቀር ነበርና፡-
አመለኛው ዓባይ መጣበት ዘንድሮ
አብስዬ እንዳልበላ ግንዱን አንከባሎ፣
ቅጠሉም አልቀረ አጋዘው ጠራርጐ፣
በክረምት መሬት የተስፋ ዓይኔን መርጐ፡፡
ከዓባይ ምንጭ ነበር ስንዴ ሚታፈሰው፣
ግና ሳይሆን ቀርቶ
ዓባይም ተሰግቶ
የክረምቱን ረሀብ በካናዳ ስንዴ በችጋር አለፍነው፡፡
አንተ የማትረባ የባዕድ እንቧይ
ማረሻ በሬየን መውሰድህ ነውይ?
እየተባለ ሲወቀስ ኖሯል፡፡ በዓባይ ምክንያት ለም አፈሩን እያጣ ለረሀብ ሲዳረግ የኖረ ህዝብ ዓባይን በሰነ ቃሉ ከመውቀስ አልፎም፡- መንግሥት በመንበሩ አድፍጦ ዝም አለ፣
ማን ይነካኝ ብሎ ዓባይም ሸለለ፡፡
በማለት ገዥዎቹን እስከ መሸንቆጥ ደርሷል፡፡
ዓባይን በመግራት በኩል የመንግሥት ዝምታ ተስፋ ባስቆረጠው ጊዜ ደግሞ፡-
ዓባይ ወዲያ ማዶ ያለኸው እረኛ፣
ዝም አትበል ክሰሰው ለሰማዩ ዳኛ፡፡
ዓባይ ኮበለለ ተስፋችንን ይዞ፣
ኧረ እስከ መቼ ነው ሁልጊዜ ተክዞ
እያለ ለቁጭቱ ስንኝ ሲቋጥር ኖሯል፡፡
የትናንቱ ዓባይ በሀገሬው ላይ ሲያሳድር የኖረው ጫና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊም ነው፡፡ ዓባይ ማበርከት የነበረበትን ባለማበርከቱ የተቆጩ ወገኖች፡-
መብራት እንኳ የለኝ ሁሌ በጨለማ
ከጉያየ እያሉ ዓባይና ጣና
ይኸው ለዘመናት ኩራዝ እያበራሁ
ዓይኔ ተበደለ
ጉዳቴን እያየ ዓባይም ዝም አለ
እያሉ ሲያንጐራጉሩ ኖረዋል፡፡
በግንቦት ወንዝ ተሻግሮ የዘራውን ማሳ ከክረምት በኋላ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይሰበስብ የዓባይ ውኃ ሙላት እንቅፋት የሆነበት አርሶ አደር፡-
ዓባይ ወዲያ ማዶ ማሽላ ዘርቼ፣
ወፉ በላው አሉ መሻገሪያ አጥቼ
ሲል ይኽው ውኃ ሙላት ከዘመድ አዝማድ ጋር አላገናኘው ያለው ደግሞ፡-
ዓባይ ወዲያ ማዶ ዘመድ አለኝ ማለት፣
ዋ ብሎ መቅረት ነው ውኃው የሞላለት
እያለ የዓባይን ደንቃራነት ይናገራል፡፡ የዓባይ ውኃ ሙላት ከሚወዳት ጉብል ጋር አለያይቶት እንዳይቀር የሰጋ ኮቦሌ፡-
የማዶዋን ፍቅሬን ሳላያት ስባትት፣
ምን ይውጠኝ ይሆን ዓባይ የሞላለት፣
አንቺ የማዶዋ የልቤ ሰቀቀን
ዓባይ ሊሞላ ነው ሳንገናኝ ልንቀር
ሲል ጉብል በበኩሏ፡-
ባያሌው እንዴት ነህ አንተ ልጅ የኔው፣
የዓባይ ወንዝ ሳይሞላ ልምጣ ወደ አንተው
በበጋው መጥቼ አይንህን ልየው፣
ክረምት ከገባማ ዓባይ ሌባ ነው፡፡
ትለዋለች፡፡
በክረምት የሞላው ዓባይ ወንዝ ቶሎ አልጐድል ብሎ የወዳጇ መምጫ ጊዜ የራቀባት አፍቃሪ
ዓባይ ጉደል ጉደል ቀጭን መንገድ አውጣ
የናፈቀ ወዳጅ ተሻግሮ እንዲመጣ፡፡
እያለች ስትማፀን ወንዱ በበኩሉ
ዓባይ ጉደል ብለው አለኝ በታህሣስ፣
የማን ሆድ ይችላል እስከዛው ድረስ
በማለት ብሶቱን ይተነፍሳል፡፡
የትናንቱ ዓባይ በእነዚህና መሠል ህፀፆቹ ሳቢያ በሊቃውንቱ ቅኔ፣ በደራስያን ብዕር፣ በአዝማሪዎች ዜማ፣ በሰዓሊው ብሩሽ፣ በእረኛው ቀረርቶ፣ ፉጨት እና ዋሽንት በጥበብ ሲወቀስ፣ በጥበብ ሲከሰስ፣ ሲነቀፍ ሲገሰስ እዚህ ዘመን ደርሷል፡፡
ዛሬስ? ዛሬማ ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከአፍሪካ በቀዳሚነት የተቀመጠ ግድብ በማስገኘት ሊክሰን ተዘጋጅቷል፡፡
እነሆ ዘንድሮ ለምረቃ ሲበቃም የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ይሆናል፡፡ እናም የዛሬው ዓባይ የድህነታችን መንስኤ መሆኑ ቀርቶ የብልፅግናችን ምንጭ ሊሆን ጫፍ ላይ በመድረሱ የኢትዮጵያዊያኑ ቅኔዎች እና ስነ ቃሎችም ቅኝታቸው ተቀይሯል፡፡ ለዚህ አብነት ከጌትነት እንዬው “ዓባይ ሐረግ ሆነ” የጥበብ ሥራ ውስጥ ጥቂቱን እነሆ፡-
ሀገርን እንደ ልጓም በአንድ ልብ ያሰረ፣
ከእውነት የነጠረ ከእውቀት የጠጠረ፣
ዓባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ፡፡
እናም አደራህን ከእንግዲህ ሀገሬ፣
አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ ጉራጌ፣ አፋር ሆንክ ትግሬ፣
ወላይታ፣ ከፋ፣ ቤንሻንጉል፣ ኮንሶ፣ ጋምቤላ ሐረሬ፣
አንተ የአንድ ወንዝ ልጅ ሁን፤
ይሄን የዓባይ ሐረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ፣
ከጋራ አንገት መድፋት ከጋራ መሳቀቅ ከጋራ ሀፍረት ወጥተህ፣
ከየዓለማቱ ጥግ በያለህበቱ በአንተነትህ ኮርተህ፣
በሙሉ የራስ እምነት አንገትህን አቅንተህ፣
ድምፅህን ከፍ አርገህ ደረትህን ነፍተህ፣
‘የዓባይ ልጅነኝ እኔ ጦቢያ ናት ሀገሬ!’ በል አፍህን ሞልተህ፡፡
ይሄው ነው ከእንግዲህ፣ የሠውነት ሞገስ ፀጋ በረከትህ፣
የትውሉድ ኒሻን የእድሜ ሽልማትህ!
(ጌታቸው ፈንቴ)
በኲር የጳጉሜን 3 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም