በዚህ ሀገርኛ ግጥም ውስጥ ያለው የጉደል ልመና እና እስከዚያው አልችልም ሃሳብ ዝም ብሎ ቤት የመምታት ዝም ብሎ ግጥም የመግጠም ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ በአንዱ የውሃ ሙላት ወቅት ሰኔ ወይም ሐምሌ አሊያም ነሀሴ የአባይ ሞልቶ አላሻግር ባለ የሆነ አንድ ውሽንንፍራም ቀን የተጻፈ ናፍቆት ያናወዘው ናፋቂ ወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ የጻፈው ግጥም ብቻም አይደል፡፡ ይህ ግጥም እንዳሰበው ካሰበው ለመድረስ ያልቻለ ናፋቂ ወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ መች ትጎድላለህ ብሎ ደጅ የሚጠና ትግስት አልባ ናፋቂ የጻፈውም አይደለም፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ አንድ ሰው አይደለም የመሸበት አንድ ሰው አይደለም የናፈቀ፤ አንድሰው ብቻ አይደለም እስኪጎድል የሚጠብቅ፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ ትውልድ ነው የጠበቀው፡፡ ይህ ጥያቄ የአንድ ሰው ሳይሆን የትውልድ ጥያቄ ነው፡፡ ዓባይን እንደ አንድ ሰው የጠየቀው አንድ ሰው ሳይሆን ትውልድ ነው፡፡
በዓባይ ውሃ ሙላት የተመሰለ ለዘመናት የተጠራቀመ ችግርና መከራ ነው፡፡ እስኪጎድል እንደሚያስጨንቅ ውሃ ሙላት ችግርም እስኪያልፍ እንደዚያው ነው፡፡ የማያልፍ የሚመስል ቀን ያልፋል፤ ውሃ ሙላቱም ይጎድላል-ሰውም ወደናፈቀው ይሻገራል፡፡ ከዘመድም ጋር ይገናኛል፤ ደስም ይለዋል፡፡
ይህንን የትውልድ እንጉርጉሮ መሻገር በናፈቀው መንገደኛ አሳቦ ትውልድ ሲያንጎራጉረው ዘመናትን ያስቆጠርንበት የአባይ እንቅፋትነት በትውልድ ቅብብሎሽና በትውልድ ትብብር ዛሬ ሁሉንም ሊክስ ወደእንጀራነት ተቀይሯል፡፡ አሁን “ዓባይ እንደሁሌው ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል ” የሚለው አሽሙርን ዛሬ አባይ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ በተንጣለለው የሀገሩ አድባር መክተሙን እያዬ አይደግመውም፡፡
በሕይወትም እንዲሁ ነው፤ አንዳንድ ከባድ ቀን ማቅ ለብሶ በማልቀስና ቁጭ ብሎ በመጠበቅ አያልፍም፡፡ አንዳንዳን ችግር በመሸሽና በሌሎች በማሳበብ፣ አንዳንዱን ራስን በመውቀስ፣ አንዳንዱን ደግሞ እንደማያልፍ ራስን በማስነፍ ካሉበት ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡
በወቅት መፈራረቅ ተፈጥሮ እንደሚቀየረው ሁሉ ተፈጥሮ ደስታና ሀዘንን የምንሸከምበት ትክሻና የምንወጣበትን ዘዴም አብራ ለግሳናለች፡፡ እንደወቅት መፈራረቅ ደስታና ሀዘንም ይፈራረቃል፤ ደስታው ዘላለማዊ አይደለም- ሀዘንም እንዲሁ፡፡
ስለዓባይ የነበረን ቁዘማና ተስፋ መቁረጥ በትውልድ ብርቱ ልፋትና ትብብር ተቀይሯል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዜጎች ተባብሮ መስራትና ታሪክ የመቀየር ፍላጎት በተግባር የታየበት ነው፡፡ እንደህዝብ በአንድ መቆምና መተባበር፤ አይቻልም የሚልን የሰነፍ ሃሳብ ሰርቶ መቀየር በሚችል ብርቱ ክንድ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አስረኛ የሆነውን ታላቅ ግድብ ገንብቶ የኢትዮጵያውያንን ታላቅነት ዳግም የመለሰ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ይህን መከወን መቻል ዝም ብሎ ግድብ ከመገንባትና ከማጠናቀቅ ሃይልም ከማመንጨት በላይ ነው፡፡ የዚህ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ ከዚህም በላይ የመስራትና የመጨረስ አቅም እንደለን ማሳያ ነው፡፡
የዓባይን ወንዝ ጥቅም ላይ መዋል ያየ ትውልድ ላለፈው ሳይሆን ለመጪውም በአንድነትና በጋራ እንዲሁም በስራና ተስፋ ባለመቁረጥ ያሰበውን ያሳካ ዘንድ የሕዳሴው ግድብ ተገንብቶ መጠናቀቅ ለትውልድ እንደ አብነት ነው፡፡
በኲር የመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም