ዓይነስውርነት-  ሊረታ ነው

0
8

በእድሜ መግፋት ለዓይነስውርነት ለተዳረጉ ሰዎች በዓይን ብሌን ወይም “ሪቲና” ስር ከፀጉር የሚቀጥን ምስል መለያ “ማይክሮቺፕ” በቀዶ ህክምና በማስገባት እና አጉልቶ በሚያሳይ መነፀር በመታገዝ  ዳግም እንዲያዩ ማድረግ መቻሉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

በእንግሊዝ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንባብ እንዳበቃው በእድሜ መግፋት ለዓይነስውርነት ከተዳረጉ 32 የናሙና ታካሚዎች 26 ተከላው ከተሰራላቸው ከ12 ወራት በኋላ የማየት  ዓቅማቸው ተመልሶ የየዕለት ህይወታቸውን መምራት ችለዋል፡፡

ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና ከሙርፊልድ ሆስፒታል የተውጣጡ ተመራማሪዎች በጋራ በሰሩት ምርምር እና የናሙና ሙከራ በ “ሪቲና” ስር በገባው ሁለት ሚሊ ሜትር በሁለት ሚሊሜትር የተለካ ምስል መለያ፣ የተቀረፀውን   ምስል ታካሚው ወገብ ላይ በታሰረ ወይም በኪስ በሚያዝ  ማጉያ ቪዲዮ ካሜራ በማስተላለፍ ምልክት እና ፊዳላትን መለየት አስችሏቸዋል፡፡

ቀዶ ህክምና ከተሰራ ከወራት በኋላ ታካሚዎች የማየት፣ የማንበብ ዓቅማቸው መመለሱን አረጋግጠዋል፡፡ በናሙና ሙከራው ለመሣተፍ መመረጣቸውም ትልቅ ዕድል መሆኑን ነው የመሰከሩት፡፡ በቀጣይ ምርምሩ አድጐ እና ተስፋፍቶ ለብዙዎች ብርሃን እንዲፈነጥቅ መመኘታቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

በዓለማችን በአጠቃላይ አምስት ሚሊዬን የሚጠጉ አረጋውያን ዓይነስውር መሆናቸውን እና እስከ አሁን የጤናእክሉን ለማከም እና ሁነቱን ለማሻሻል ሳይቻል መቆየቱን በጀርመን የቦን ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ዶ/ር ፍራንክ ሆልዝ ጠቁመዋል፡፡ አሁን ላይ በምርምር የተገኘው ለውጥ  ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው  በማጠቃለያነት ያሰመሩበት፡፡

በታካሚው የሚያዘው የቪዶዮ ካሜራ በዓይን ውስጥ ከተተከለው “ቺፕ” ምስል መለያ ጋር በመናበብ እንደብርሃን መሰብሰቢያ እንቅብ ወይም “ፓኔል” እንደሚያገለግል አስረድተዋል- የተመራማዎቹ መሪ ዶ/ር ፍራንክ ሆልዝ፡፡

በመጨረሻም በእንግሊዝ የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪው ማሂ ሙኪት በመስኩ ቀደም ብሎ ያልነበረ አዲስ ምእራፍ መከፈቱን እና የተገኘውን ውጤት በማወደስ ማደማደማቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here