ዓድዋ በውጪዉ ዓለም ዕይታ

0
119

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በተጋድሏቸው ያገኙት ሲሆን ድልነቱ ግን የዓለም እና የዓለምን ታሪክም የቀየረ ነው፤ በቅኝ ገዢዎች ላይ የሚደርሰውን ጭካኔ የተሞላበት ጭቆና ሲዋጉ ለነበሩ ሕዝቦች ሁሉ ኩራታቸው፣ አርማቸው እና የነጻነት ተምሳሌታቸው አድርገው ይቆጥሩታል። ከዓድዋ ድል በፊት አንድም ሌላ የአፍሪካ ሀገር የአውሮፓ ጦርን አሸንፎ አያውቅም። ኢትዮጵያዊያን ግን አደረጉት፤ በወቅቱ በወራሪ አውሮፓዊያን ላይ የተቃውሞ ውጊያዎች ቢደረጉም  ውጤት አላስገኙም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የዓድዋ ጦርነትን ድል ስትቀዳጅ ዜናው በመላው ዓለም ተሰማ።  ድሉ ትልቅ ታሪክ የተሠራበት፣ የዓለምን የተዛባ ዕይታ የቀየረ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አግኝቷል። ዜናውም መላውን አውሮፓ ያስደነገጠና ያስገረመ ነበር።

የአፍሪካ ተዋጊዎች የቱንም ያህል ድፍረትና ወኔ ቢያሳዩም በደንብ የሰለጠኑት፣ በሚገባ የተደራጁትና በሚገባ የታጠቁት የአውሮፓ ኃይሎች ከአቅማቸው በላይ ነበሩ። የሥልጣኑ ሚዛን ምንጊዜም ለአውሮፓ ሠራዊት የሚያጋድል ነበር። ዓድዋ ግን ይህንን የቀየረ ነበር፡፡

በርካታ በዓለም ላይ የሚገኙ የታሪክ ምሁራን፣ መፅሔቶችና ጋዜጦች ስለ ዓድዋ ብዙ ነገር ብለዋል፡፡ ለአብነትም ዘ ዋሺንግተን ኢንፎርመር (The Washington Informer)   የኢትዮጵያ ድል  በንጉሥ ምኒልክ እና በባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ መሪነት  በዓለም ዙሪያ ፍርሃትን መፍጠሩን አትቷል።  እንደ ማርከስ ጋርቬይ እና ኔልሰን ማንዴላ ያሉ የነጻነት ታጋዮችንም ትግላቸውን ማበረታታቱን ይጠቁማል።

ዋሺንግተን ፖስት በበኩሉ ከላይቤሪያ በስተቀር የአፍሪካ ሀገሮች በአውሮፓዊያን ቅኝ ግዛት ሥር ሲገቡ፣ ኢትዮጵያ ግን የጣሊያንን ጦር አሸንፋ ብቸኛ ነፃ የአፍሪካ ሀገር ሆና መቆየቷን ይገልጻል፡፡  የኢትዮጵያ ስኬት የተገኘው በኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው አንድነት፣ አስተዋይ አመራር፣ አስፈሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የሀገሪቱ ረጅምና ዘላቂ ታሪክ ያላት እና የሕዝቡ የጦርኛነት መንፈስ መሆኑንም ያብራራል፡፡

ከድሉ በኋላ የመላው ዓለም ጥቁር ሀገሮችና ሕዝቦች ኢትዮጵያን የነጻነትና የክብር አርማ አድርገው ማየት ጀመሩ። የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ጽንሰትና ጅማሮም ‘ሀ’ የተባለው  በዚህ ጊዜ ነበር። ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓይነት ግፍና ጭቆና የመቃወም ምልክት ተደርጋ ትቆጠር የጀመረችው ከዓድዋ በኋላ ነበር።

ኦሪጂንስ (origins.osu.edu) ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚለው የዓድዋ ድል ቀደም ሲል ነጮች ብቻ ያሸንፉ የነበረውን ሁኔታ ጥቁሮች ማድረግ እንደሚችሉ ያሳዬ ነው፡፡

በዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሬይመንድ ጆናስ እንደጻፉት የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ አስደናቂ ድል፣ ለጣሊያን ደግሞ ውድመት እና ውድቀት ነበር። ዓድዋ አፍሪካዊያን የራሳቸውን ነፃነት የሚያዩበት ታሪክ ሆኗል፡፡

እ.አ.አ በ1896 (1888 ዓ.ም) የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት የጣሊያን መንግሥት ለውጥ እና የአውሮፓዊያን የአፍሪካ አመለካከት ለውጥን ጨምሮ ብዙ ውጤቶችን አስከትሏል፡፡ በዋነኛነት ኢትዮጵያ አውሮፓን በጦርነት ድል ያደረገች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር አድርጓታል። አውሮፓዊያን በአፍሪካ ላይ ያላቸው አመለካከትም ተቀይሯል፡፡ አውሮፓዊያን አፍሪካዊያንን በቁም ነገር መመልከት የጀመሩት ከዓድዋ ድል በኋላ ነበር ሲሉ ነው ዕውቁ የታሪክ ምሁር የጻፉት፡፡

ሬይሞንድ እንደጻፈው ምንም እንኳን የዘረኝነት አመለካከቶች ባይወገዱም  ድሉ የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ሥርዓት ፈታኝነትን  ቀንሷል። ጦርነቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁር ሕዝቦችን አስከብሯል። በፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሀሳብ ላይ አውንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል፡፡ እንዲሁም የአፍሪካዊያንን የነጻነት እንቅስቃሴዎችን አነሳስቷል። ጣሊያንን ጨምሮ ዋና ዋና ቅኝ ገዢዎች ለኢትዮጵያ ነፃነት ዕውቅና ሰጥተዋል። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ የአውሮፓ ሀገራት ቆንስላዎች  ተከፍተዋል። የባለቤታቸውን የእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጠንካራ ድጋፍ ወደ ተግባር ማምጣቱ ለውጤታማነት እንዳበቃቸው ያነሳው ሬይሞንድ ጆናስ ይህም የአጼ ምኒልክን ብልህነት እንደሚያሳይ መስክሯል።

አፍሪካማጋዚን(www.afrikamagazine.com)ከተሰኘው ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ እንደሚያትተው በቅኝ ግዛት ሥር የሚገኙ የዓለማችን ጥቁር ሕዝቦች መነሳሳት የጀመሩት በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። “ኢትዮጵያዊያን ይህን ማድረግ ከቻሉ እኛ ለምን ማድረግ አልቻልንም?” የሚል ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት   ከድሉ በኋላ ነበር፡፡

በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በመሰል ምክንያት የሚሰቃዩ ሰዎች ጨቋኝ መሪዎቻቸው ላይ ለማመፅ ማሰብ እንዲጀምሩ እንደ ዓድዋ ድል ያለ መነሳሳት ያስፈልጋቸው ነበር። ለዚህም ነው ዓድዋ በጭቁን ሕዝብ ዘንድ አዲስ ተስፋና ብርሃን  ተደርጎ የሚቆጠረው። በአሜሪካ እና በካሪቢያን ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች  የዓድዋን ድል ስንቅ በማድረግ የፍትሕ መጓደልን በመቃወም ለነጻነታቸው ተጋድሎ አድርገዋል።

ከዓድዋ ድል በኋላ በቅኝ ግዛት ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት በብሔርተኛ አስተሳሰብና ፖለቲካ ውስጥ ያለው ሚና ታላቅ እና አበረታች እንደነበር ይገለጻል፡፡

ሳሂስትሪ ድረ ገጽ (www.sahistory.org) ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያትተው ደግሞ የጣሊያኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ክሪስፒ ከሥልጣን ያስለቀቀው የዓድዋ ድል ወራሪዎችን ሲያሳፍር የአፍሪካዊያን የኩራት ምንጭ ሆኖ የነጻነት ትግሎችን ማቀጣጠል ችሏል። አፍሪካዊያን ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ከጀመሩ በኋላ በአንድነት መቆም እንደሚገባቸው አምነው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እ.አ.አ በ1963 ሲያቋቋሙ የዓድዋ ድል መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል።

ከድረ ገጹ የተጻፈው መጣጥፍ እንደሚያትተው  የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ የበላይነት የተቀዳጀችበት ወሳኝ ድል ነው። ይህ ታላቅ ድል በመላው አፍሪካና ዓለም በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ ሁሉ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ መነሳሳትን ፈጥሯል። ዓድዋ ለአፍሪካዊያን አዳዲስ ጭቆናዎችን በመቃወም ረገድ ጠቃሚ ትምህርትም አለው።

“ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጀግንነት እና የነጻነት አርማ ሆናለች፣ የክብርና የተስፋ መሠረት ሆና በአውሮፓዊያን ወረራ ሙሉ ድንጋጤ ውስጥ ለነበሩት አፍሪካዊያን ሁሉ መጽናኛ ነበረች” ይላል ጽሑፉ፡፡

ድረ ገጹ እንዳስነበበው  የዓድዋ ድል ታሪካዊም ተምሳሌታዊም ነው።  እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና የአንድነት ኃይል የታየበትም ነበር።

የዓድዋ ድል በምዕራባውያኑ አስተሳሰብ ለተጨቆኑ ሁሉ የነፃነት ድል ማበርከቱንም ያትታል። ዓድዋ የጣሊያን ቅኝ ገዢዎችን ድል በማድረግና የነጮችን የበላይነት አፈ ታሪክ በማስወገድ የታሪክን አካሄድ ቀይሯል። የነጭ የበላይነት ጽንሰ ሐሳብ አፈ ትውፊታዊ ሆኖ መቅረቱን የሚያሳይ ነበርም ይላል።

እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት ደግሞ የአድዋ ድል ከትግል ባሻገር በደቡብ አፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚል የሃይማኖት አስተምሮ እንቅስቃሴን ያስጀመረ ታሪካዊ ከስተት ነው።

የዓድዋ ድል የጣሊያን  መንግሥት እንዲቀየር ምክንያት ሆኗል።  ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ተገደዋል።

በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የቺካጎ ፐሬስ አምድኛ እና የሶሾሎጂ መምህር የነበሩት ዶናልድ ኤን ሌቪን እንደጻፉት “ዓድዋ ያቀዳጀው አስደናቂ ድል  አውሮፓውያን ኢትዮጵያንና አፍሪካን ይበልጥ በቁም ነገር  እንዲይዟቸው ማድረጉ ነው፡፡

ጃማይካዊው ፖለቲከኛ ማርከስ ጋርቬይ፣ አሜሪካዊው የጥቁር ሕዝቦች ተቃውሞ መሪ የነበሩት ዊሊያም ድ ቦይስ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ እንዲሁም የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ጆርጅ ፓድሞር እና ለሌሎችም የዓድዋ ድል ለትግላቸው መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ማርከስ ጋርቬይ እንደጻፈው ዓድዋ ጥቁሮችን ከአፍሪካ ጥንታዊ ክብር እና የወደፊት ተስፋ ጋር አገናኝቷል፡፡

ብራዚል ውስጥ የሚታተመው እና “ኦ ምኒልክ” የተሰኘው ጋዜጣ እ.አ.አ ከ1915 ጀምሮ በጥቁር ማንነት እና መሰል ታሪኮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎችን ያሳትም ነበር።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አሜሪካውያን የየካቲት ወርን የጥቁር ሕዝብ የታሪክ ወር በሚል ሰይመው መዘከር ከጀመሩ 50 ዓመት በላይ እንደሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

በተመሳሳይ እ.አ.አ በነሐሴ ወርቨ 1896 ዕትም ፔቲ ጆርናል የዓድዋን ድል በተመለከተ ተከታታይ ጽሑፎችን አውጥቷል፡፡

ኒው ዮርክ ታይምስ በዘጋባው አቢሲኒያውያን(ኢትዮጵያዊያን)ጣሊያናዊያንን ድል አደረጉ፤ ሁለቱም የባራቶሪ ሠራዊት ክንፎች በኃይል ጥቃት ተሸንፍው ነበር” በማለት አስነብቧል፡፡

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here