ዕቅዱ እንዲሳካ…

0
35

ወቅቱ፦

“ገበሬው መጣ ሳስሎ ማጭድ!

“ስንዴ እና ጤፉን በወቅቱ ሊያጭድ!” የሚለው የኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች ብሂል በተግባር የሚታይበት ወቅት አሁን ነው። አርሶ አደሩ ማሳውን  አርሶ፣ አለስልሶ፣  ዘርቶ፣ ኮትኩቶ፣ አርሞ፣ ከወፍ እና ከተባይ ጠብቆ… በከፍተኛ ጥረት ለፍሬ ያበቃውን ሰብል መሰብሰብ ጀምሯል። በዚህ ወቅት ታዲያ ጥንቃቄ ካልተደረገ ከፍተኛ የምርት ብክነት በመጠን እና በጥራት ይከሰታል። በመሆኑም በሂደቶቹ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የምርት ብክነትን መቀነስ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በወቅቱ፣ በአግባቡ እና በጥንቃቄ ሰብልን አለመሰብሰብ እና አለመያዝ፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን አለመከተል፣ የሰብሉን ትክክለኛ የመድረቅ ደረጃ አለመለየት፣  ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አለመጠቀም፣ የእህል ማስቀመጫ ጎተራዎችን አለማፅዳት፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ የተባይ ክስተት እና መሰል ችግሮች ለምርት ብክነት እና ለጥራት ጉድለት ምክንያት መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሰብል ስብሰባ ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እየሰበሰቡ መሆኑን ለበኵር በስልክ ሐሳባቸውን ካጋሩን አርሶ አደሮች መካከል  በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢ ጠህናን ወረዳ አርባዕቱ እንስሳ ቀበሌ ነዋሪው አቶ መስፍን ተሰማ አንዱ ናቸው። አርሶ አደሩ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት/በ2017/18 የምርት ዘመን/  የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ይገኛል፡፡ በምርት ዘመኑም  የሚጠብቁትን ያህል ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል።

አርሶ አደሩ በምርት ዘመኑ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ግብዓት አግኝተው ሦስት ሄክታር መሬታቸውን በቆሎ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ በርበሬ እና በሌሎች ሰብሎች ሸፍነዋል። ከዚህ ውስጥ አንድ ሄክታር መሬታቸው  በበቆሎ ሰብል ብቻ መሸፈኑን ገልጸዋል። አርሶ አደሩ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ  የዘሩትን የጤፍ ሰብል አሁን ላይ አጭደው ዝናብ እንዳያበላሸው ከፍ ባለ ቦታ እና በጥንቃቄ ከምረዋል። “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንደሚባለው  አቶ መስፍን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር   በደቦ (በሕብረት) ሰብላቸውን እየሰበሰቡ ነው፡፡ ሰብልን በደቦ መሰብሰብ ዘንድሮ ከቀድሞው በተሻለ መጠናከሩን የገለጹት አርሶ አደሩ፤  አንድነት ኀይል በመሆኑ ጊዜን፣ ጉልበትን ከመቆጠቡ በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎች  ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ሳይደርስበት ለመሰብሰብ  ያግዛል ነው ያሉት።

አርሶ አደሩ በቀጣይ  የደረሱ የበቆሎ   ሰብሎችን ጨምሮ  ሌሎችን  ለመሰብሰብ ተዘጋጅተዋል። ይሁንና አሁን ላይ በአካባቢው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት ፈጥሮባቸዋል። በመሆኑም የቀረውን ሰብል ፈጥኖ በዘመናዊ መንገድ ለመሰብሰብ መንግሥት የማጨጃ እና መውቂያ ማሽን (ዘመናዊ ቴክኖሎጂ) በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል።

አርሶ አደሩ የመኸሩን ሰብል  ባነሱበት ማሳ  በእርጥበቱ  ሽምብራ  መዝራታቸውን ነው የገለፁት። በቀጣይም ከሰብል ስብሰባው ጎን ለጎን በመስኖ ለማምረት የእርሻ  መሬታቸውን አርሰው ዝግጁ አድርገዋል።

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሠራ መሆኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያ አቶ በላይነህ ጌትነት ለበኵር በስልክ ተናግረዋል፡፡ የሰብል ባለሙያው እንዳሉት በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ እና ዳጉሳ በምርት ዘመኑ በስፋት  የተመረቱ  ናቸው።

በዞኑ በ2017/18 የምርት ዘመን 264 ሺህ 649 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 268 ሺህ 331 ሄክታር በተለያዩ የሰብል አይነቶች ተሸፍኗል። ከዚህም 13 ሚሊዮን 675 ሺህ 644 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የሚጠበቀውን ምርት ለማግኘትም ባለፉት ጊዜያት ሰብልን በወቅቱ የማረም፣ የመኮትኮት፣ ግብዓት የመጨመር፣ የመጠበቅ፣ የተባይ አሰሳ ማድረግ፣ የመንከባከብ እና መሠል ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። በዘር ከተሸፈነው ሰብል ውስጥ  ለገበያ በጣም ተፈላጊ የሆኑ (የኮሞዲቲ) ሰብሎች ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ያሉት ባለሙያው፤ በዚህም 160 ሺህ 63 ሄክታር መሬት  እንደተሸፈነ አስረድተዋል።

የዘንድሮው የመኸር  ሰብል ቁመና ሲታይ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን የጠቀሱት ባለሙያው፤ ለዚህም በቂ የግብዓት አቅርቦት በወቅቱ መቅረቡ፣ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የእርሻ ድግግሞሽ መከናወኑ፣ የተሻሻሉ አሠራሮች ተግባራዊ መደረጋቸው፣ ተስማሚ የአየር ፀባይ መኖሩ፣ በቂ የዝናብ መጠን መኖሩ፣ የበሽታ እና የተባይ ክስተት ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡  አሁን ላይ የደረሱ ሰብሎች በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውንም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ በመሰብሰብ በደረቅ እና በንፁህ ቦታ ማስቀመጥ፣ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና መሰል ችግሮች ምርቱ እንዳይባክን እና እንዳይበላሽ ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብሰብ እና ወቅቶ ወደ ቤት ማስገባት እንዳለባቸው አቶ በላይነህ አስገንዝበዋል።

የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እና በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን ለመቀነስ  እየተሠራ ስለመሆኑም የተናገሩት ባለሙያው፤ አርሶ አደሩም ሰብሉን በወንፈል (በደቦ) እና በቀን ሠራተኛ ጭምር ታግዞ እየሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከሰው ጉልበት በተጨማሪ በዞኑ 27 ኮምባይነሮች (የመሰብሰቢያ ማሽን) በድርጅቶች እና በግለሰቦች ያሉ ሲሆን ከወረዳዎች እና ከኮምባይነር ባለቤቶች ጋር በመነጋገር ከአድሎ በፀዳ ሁኔታ አገልግሎት እንዲሰጡ የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሕዳር መጀመሪያ ሳምንት ድረስ 37 ሺህ  696 ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ  ሰብል እንደተሰበሰበም አመላክተዋል። አርሶ አደሩ የተሰበሰበው ሰብል በዝናብ እንዳይበላሸም በአግባቡ አናፍሶ እና አድርቆ በመከመር ምርቱን ከብልሽት ሊታደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አርሶ አደሩ ሰብሉን በወቅቱ መሰብሰብ፣ ሲከምር ደረቅ ቦታ መምረጥ፣ በአግባቡ አገላብጦ ማድረቅ፣ በጥንቃቄ ማጓጓዝ፣ ደረጃውን በጠበቀ አውድማ መውቃት እና ምርቱን ከገለባው (ከባዕድ ነገሮች) መለየት፣ ደረጃውን የጠበቀ የእህል ማከማቻ መጋዝን መጠቀም፣ ከፕላስቲክ የተሠሩ የእህል ማከማቻ ከረጢቶች (ዘመናዊ ጆንያዎች) እና ከተባይ የሚከላከሉ ከብረት የተሠሩ የእህል ማከማቻ ጎተራን መጠቀም አስፈላጊ ነው ብለዋል። ምርቱ ጊዜው ሳያልፍ እንዲሰበሰብ እና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በየአካባቢው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

አርሶ አደሮችም የደረሱ ሰብሎችን የምርት ብክነት እንዳይኖር በፍጥነት እና በጥንቃቄ የመሰብሰቡን ሥራ በትኩረት እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል። የደረሱ ሰብሎች ከተነሱ በኋላ አርሶ አደሩ ማሳውን ለበጋ መስኖ ልማት ለማዋል የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመላክተዋል ፡፡

በአማራ ክልል በ2017/18 የምርት ዘመን አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል፡፡ በመኸር እርሻ ከለማው አጠቃላይ ሰብል 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑም ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በክልሉ በመኸር እርሻ በሰብል ከተሸፈነው እስካሁን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወ/ሮ እንዬ አሰፋ ለበኵር ተናግረዋል። በተለይም አሁን ላይ የሰሊጥ ሰብል በስፋት መሰብሰቡን ነው ባለሙያዋ ያብራሩት። 550 ሺህ 465 ሄክታር መሬት በሰሊጥ ዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህ ውስጥ እስካሁን ከ537 ሺህ  ሄክታር በላይ ሰብል ተሰብስቧል፡፡

የሰብል አሰባሰቡ በኮምባይነር እና በተለያዩ አነስተኛ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ  እየተከናወነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ብክነትን በመቀነስ መሰብሰብ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ለውጤታማነቱም የግብርና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በሰብል አጨዳ፣ በመከመር እና ውቂያ ወቅት ሊደርስ የሚችልን የምርት ብክነት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ምክረ ሐሳቦችን አጋርተዋል፡፡

ሰብሉ የሚከመርበት ቦታ ደረቅ መሆኑን መለየት፤ በእንጨት ርብራብ ሠርቶ መከመር፣ ፈጥኖ በደረቁ ወቅቶ ወደ ቤት በማስገባት ምርትን ከብክነት መታደግ እንደሚገባ ባለሙያዋ አስገንዝበዋል። ምርቱ ለገበያ እና ለምግብነት እስኪውል ድረስም በጥራት እና  በብዛት ለማምረት ከእርሻ እስከ ጉርሻ ድረስ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ  ሥራን ማከናወን ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚገኘው ምርት ውስጥ በአማካኝ እስከ 30 በመቶ የሚሆነው  በዋናነት የሚባክነው  በድህረ ምርት ወቅት ሙያዊ ምክረ ሐሳቦችን ባልተከተሉ አሠራሮች እና በአያያዝ ጉድለት መሆኑን የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት መረጃ አመላክቷል።

 

ዜና

ከ42 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለመሸፈን ታቅዷል

 

በዘንድሮው የበጋ ወቅት ከ42 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በነባር እና በአዲስ በተለያዩ ሰብሎች  ለማልማት መታቀዱን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ የመስኖ ውኃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አዲሱ አለሙ ለበኵር በስልክ እንደተናገሩት በመስኖ ከሚለማው  መሬት ውስጥ 28 ሺህ ሄክታር   ስንዴ  ይሸፈናል። ከዚህም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ምርታማነትንም በሄክታር 40 ኩንታል ለማድረስ ታቅዷል።

በዓመቱ በነባር መስኖ 37 ሺህ 49 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ እስካሁን /ሕዳር መጀመሪያ ሳምንት/ 24 ሺህ 174 ሄክታር የታረሰ ሲሆን ከዚህም አራት ሺህ 860 ሄክታር በዘር ተሸፍኗል። በአዲስ መስኖ ለማልማት አምስት ሺህ 928 ሄክታር ታቅዷል። እስካሁንም 3 ሺህ 217 ሄክታር  መሬት ተለይቶ 822 ሄክታር ታርሷል። 42 ሄክታሩ ደግሞ በዘር ተሸፍኗል።

ቡድን መሪው እንዳሉት የመስኖ ልማት ዕቅዱን ለማሳካት የእርሻ ሥራ እና የቦይ ጠረጋን ጨምሮ ሰፊ ዝግጅት ተከናውኗል። እንዲሁም ሰፊ የገጸ ምድር እና የከርሰ ምድር የውኃ ጸጋዎች፣ በቂ የምርጥ ዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት መኖሩንም አረጋግጠዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የህዳር  8  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here